| ከ(78) ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
|
ስለ ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዕረፍት
ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በኢትዮጵያ ነግሠው፣ 13 ዓመት ከ6 ወር ገዝተው በ54 ዓመት ዕድሜያቸው መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ረቡዕ በ8 ሰዓት ዐረፉ፡፡ የሞታቸው ዜና እንደተሰማ በከተማው የሐዘን ጥላ አጠላበት፡፡ ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በ1868 ዓ.ም ሚያዚያ 22 ቀን ቅዳሜ ከሸዋ ንጉሥ ከዳግማዊ ምኒልክና ከወረኢሉ ተወላጅ ከወይዘሮ አብቺው በእነዋሪ ከተማ ተወለዱ፡፡ ሐምሌ 11 ቀን ሰኞ ሥርዓተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸው፣ የክርስትና ስማቸው አስካለ ማርያም ተባለ፡፡ ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ለዳግማዊ ምኒልክ ሦስተኛ ልጅ ናቸው፡፡ መኳንንትና ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ በምርጫ የተቀመጡ ብቸኛዋ ንግሥት ናቸው፡፡ በግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን ከተፈጸሙ ተግባራት (ሀ) የዓለም ማኅበር አባልነት (የዓለም ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ)) ጠቅላላው ጉባኤ በ28 ሴፕቴምበር በ1923 (መስከረም 17 1916) ስብሰባውን ቀጠሉና የስድስተኛውን ኮሚሲዮን ማስታወቂያ ተደግፎ ኢትዮጵያ ማኅበርተኛ እንድትሆን ፈቃዱ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በዚህ ጊዜም ከፍ ያለ ጭብጨባ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ዋናው መልእክተኛ ደጃዝማች ናደው የደስታ ስሜታቸውን ለመግለጥ ንግግር ማድረጊያው ስፍራ ላይ ቆመው የሚከተለውን ዲስኩር ተናገሩ፡፡ ክቡራን ሆይ፤ ጠቅላላው ጉባኤ በበጎ ፈቃደኝነትና በትክክለኛ ፈራጅነት፣ በጥልቅ አስተሳሰብ መርምሮ ወደ ማኅበሩ ስለመግባት ያቀረብነውን ጥያቄ ስለ ተቀበለው፣ የኢትዮጵያ መልእክተኞች በግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ስም፣ እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ የሰውን ልጅ ወንድማማችነት የመመሥረት ዓላማ ባለው ውሳኔያችሁ የተሰማንንም ልባዊ ደስታ እንድገልጽላችሁ ይፈቀድልኝ ዘንድ እለምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው የጀግንነት ታሪክና በከፍተኛ ሥልጣኔዋ የምትኮራ አገር መሆንዋ፣ የዘመናዊ ድርጅቶች ከሚያስገኙላትም ፍሬ ተካፋይ ለመሆን ብርቱ ጥረትና ሙሉ ፈቃደኛነት እንዳላት የታወቀ ነው፡፡ መንግሥታችንም ይህን ጥረት ወደ መልካም ግብ ለማድረስ የዓለም መንግሥታትን አንድነትና ኅብረት የሚያስፈልግ መሆኑን በጥብቅ ያምንበታል፡፡ (ሁ) ስለ ባሮች የነፃነት ደንብ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መጋቢት 16 ቀን 1916 ዓ.ም በግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ፈቃድ ስለ ባሮች ነፃነት አንድ ደንብ አወጡ፡፡ ደንቡ “ስለ ባሮች አስተዳደርና ነፃነት የቆመ ደንብ” የሚል አርእስት ተሰጥቶትና እንደ መጽሐፍ ሆኖ በልዑል አልጋ ወራሽ ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጣ፡፡ መጽሐፉ ባለ 10 ገጽ ሲሆን የደንቡ ቃል በ45 ቁጥሮች ተመድቧል፡፡ ይህ መጽሐፍ ለሕዝብ ይሸጥ ነበርና መጽሐፉን ገዝቶ ያነበበው አብዛኛው ሰው “የሥልጣኔ እርምጃ ነው” እያለ አልጋ ወራሽን አመሰገነ፡፡ ባለብዙ ባሮች የሆኑት ሰዎች ግን በልባቸው ቅሬታ ገብቶ አዘኑ፡፡ ለምሳሌ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በዚያው ሰሞን የልባቸውን ቅርታ በጨዋታ ላይ ሲናገሩ “እንግዲህ ምን አለ አልታየ ወርቅ (ሚስታቸው) ወደ ወንዝ እየወረደች ውሀ መቅዳት ነው፣ እኔም እንጨት እየፈለጥሁ አቀርብላታለሁ” አሉ እየተባለ ሲወራላቸው ከረመ፡፡ (ሂ) የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ ስለ መመለሱ ከእንግሊዝ አገር የመጣው የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ ሐምሌ 4 ቀን 1917 ዓ.ም ቅዳሜ ለግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ተመለሰ፡፡ በዚህም ጊዜ የተፈጸመው ሥነ ሥርዓት እንደሚከተው ነበር፤ ከጧቱ በ4 ሰዓት የግቢ ሚኒስትር ደጃዝማች ወልደ ገብርኤል በሻህ በጦር ልብስ ያጌጡ ጭፍሮች አስከትለውና በአራት ፈረሶች የሚሳብ ሠረገላ አሲዘው ከአቶ ሣህሌ ፀዳሉ ጋር ወደ እንግሊዝ ሌጋሲዮን ሄዱ፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ሚኒስትር ሚስተር ቻርልስ ቤንቲንክም ዘውዱን በሠረገላው ላይ አስቀመጡትና ሁሉም ዘውዱን አጅበው ወደ ቤተ መንግሥት መጡ፡፡ ግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱና ልዑል አልጋ ወራሽ በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በተለይ በተሰናዳው ስፍራ ከመኳንንት ጋር ተቀምጠው ይጠብቁ ነበር፡፡ የግቢ ዘበኞችም በግቢው ውስጥ በቀኝና በግራ ተሰልፈው ነበርና ሠረገላው በሰልፉ መካከል አልፎ ከመንግሥት ፊት ደረሰ፡፡ እዚያም አንድ ጠረጴዛ ተዘጋጅቶ ነበርና ሚስተር ቤንቲንክ ዘውዱን ከሠረገላው አውርደው በጠረጴዛው ላይ አስቀመጡትና ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ቃል ተናገሩ፤ ግርማዊት ሆይ በንግሥት ቪክቶሪያ መንግሥት በ1860 ዓ.ም ከመቅደላ የተወሰደውን የአፄ ቴዎድሮስን ዘውድ የታላቂቱ ብሪታንያና የአየርላንድ፣ ከባሕር ማዶ ያሉት ግዛቶች ንጉሥና የህንድ ንጉሠ ነገሥት በሆኑት በግርማዊ ጌታዬ በንጉሡ ትዕዛዝ ለግርማዊት ንግሥት በማክበር መለስሁ፡፡ (መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ፣ የሐያኛ ክፍለ ዘመን መባቻ፣ 2000) የውሃ ወራጅ ዳኛ ስለጥንቱ የክስ አቀራረብና የዳኝነት አፈጻጸም ከሙሉ በከፊሉ ለማስረጃ ያህል የሚከተለውን ማብራሪያ እናቀርባለን፡፡ አንድ ሰው ሌላውን ገንዘብ አለብህ ወይም መሬቴን ይዘህብኛል በማለትና በሌላም ይኸንን በመሳሰሉ ክስ ለማቅረብ በአሰበ ጊዜ፤ ለዳኛ ያመለክትና ተከሳሹ በቀላጤ እንዲጠራ ወይም በንጉሡ ስም ተፈጥሞ በዚህ ቀን እንድትቀርብ ተብለሃል ብሎ የዳኛውን ቃል ይነግረዋል፡፡ እንደዚሁም አንድ ሰው ባለዕዳውን በድንገት ያገኘው እንደሆነ ማንኛውንም መንገደኛ ከዳኛ አድርሰኝ ብሎ በንጉሡ ስም ያማጥነዋል፤ መንገደኛውም ቁም ወዴት ትሄዳለህ በንጉሥ ሲሉት እንኳን ሰው ውሃ ይቆማል፤ ይልና በቀጥታ ወደቀበሌው ዳኛ እንዲሄዱ ያፈጠጥማቸዋል፤ ወይም ራሱ ያደርሳቸዋል፤ ይህም ሰው የውሃ ወራጅ ዳኛ ይባላል፤ ዳኛውም ዋስና እማኝ ይዘው እንዲቀርቡ ይቀጥራቸዋል፡፡ ከዳኛ ሲቀርቡ ከሳሽና ተከሳሽ የሥርዓት ዋስ ይጠራሉ፤ ክርክሩ ሊሰማ ሥነ ሥርዓቱ የተሟላ ሆኖ ሲገኝ ከሳሽ እግዚአብሔር ያሳይዎ በማለት ለቀረበበት ክስ መልስ ይሰጣል፤ ባልተስማሙ ጊዜ፤ ከሳሽ እንዳለብህ እንደሰጠሁህ ወይም እንደወሰድክብኝ በቅሎ እሰጥ ሲለው፤ ሌላው የለብኝም አልሰጠኸኝም ለበቅሎህ አገባ ይለዋል፤ ተከሳሽ ክዶ ከሳሽ በቅሎ እሰጥ በማለት ውርርድ ከተከለ በኋላ፤ እረታለሁ የማለት ጥርጣሬ ያለው እንደሆነ ውርርድህን ዝቅ አድርግልኝ ሲለው፤ ፈረስ እሰጥ በማለት ይለውጣል፡፡ አሁንም ዝቅ አድርግ ሲለው ውርርዱን በማር ይለውጥለትና አገባ ብሎ ሲመሰከርበት ይረታል፤ ነገር ግን ተከሳሹ አጉራህ ጠናኝ በማለት፣ ክሱን ከአመነ “በአጉራህ ጠናኝ የተረታ ማህል አገዳውን የተመታ” እንደሚባለው ሁሉ፤ የመጨረሻ እርት ይሆናል፡፡ (ማኅተመ ሥላሴ ወ፡መ፣ ባለን እንወቅበት፣ 1961) የፈላስፋው ምክር አንድ ፈላስፋ በሚሞትበት ዘመን ለልጁ ይኸን ምክር ሰጠ፡፡ እዚያ ማዶ ወርቅ ቀብሬአለሁና ቆፍረህ አውጣ፡፡ ጥቁር ላም ወፈረ ብለህ አትረድ፤ ነጭ ላም ከሳች ብለህ አትተው፣ ከመንገድ ዳር እህል አትዝራ፣ ከድንጋይ ላይ አትሽና አለ ይባላል፡፡ እዚያ ማዶ ወርቅ ቀብሬአለሁና ያለው ሁሉ ነገር ከመሬት ነውና መሬትን እረስ ሲል ነው፡፡ ጥቁር ላም ወፈረች ብለህ አትረድ ያለው ምንም በአለጸጋ ወይም መልኳ አማረኝ ብለህ ያለአቻህ አታግባ፣ ያለዘርህ ሲል ነው፡፡ ነጭ ላም ከሳች ብለህ አትተው ያለው አቻህና ጋብቻህ ከሆነች ከሣች፣ ደኸየች፣ ጠቆረች ሳትል አግባት ሲል ነው፡፡ ከመንገድ ዳር እህል አትዝራ ያለው፣ ወደጋለሞታ ሴት አትሂድ ሲል ነው፡፡ ከድንጋይ ላይ አትሽና ያለው ወደመሐን ሴት አትሒድ ሲል ነው ሲባል ተተርጉሟል፡፡ (አበበ አይቼህ፣ ጉራማይሌ፣ 1948) የቅኔ ዓምድ ቦሬሳው ካሣ መካር አጡ እንዳይሆን ሆነው ቀበጡ ብዙ እያወቁ እንደጅል የማይሆን ነገር መከጀል ለድኃ እንዳይሆን እያወቁ ዘውድ አምጡ ብለው ደረቁ፡፡ - ዋለልኝ መኰንን ኘ ባውዳመቱ ዋዜማ ስሰማ አምሽቼ ላህየ ዜማ በመጨረሺያ ሲደክመኝ ጓደኞቼ መከሩኝ ሊነጋ ነው አሉኝ አሮጌ ዘመን ልንሸኝ፡፡ - ደንድር ዳንሳሞ - (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሕያው ድምፆች፣ 1993) ገራገር አደገኛ እፅን በዊልቸር የተጓጓዙት ተያዙ የአደገኛ እፅ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች እፅ በዊልቸር ሲያንቀሳቅሱ ተያዙ፡፡ ግለሰቦቹ የአካል ጉዳተኛ በመምሰል በሰዓት 4 ማይል በሚጓዝ ዊልቸር እፅ ሲያዘዋውሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ፖሊስ እንዳለው ዊልቸር የተጠቀሙት በመኪና ለማጓጓዝ በበርካታ ካሜራዎች ከሚደረገው ቁጥጥር ለመዳን ነው፡፡ የአደገኛ እፅ አዘዋዋሪዎቹ ዊልቸሩ አይፈተሽም በሚል እምነት ቢሞክሩም ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ መያዛቸው ተገል..ል፡፡ የሮኬት ስብርባሪዎች ግቢዬ ላይ ወደቀ ያለ ገበሬ ክስ መሠረተ ሮስኮማስ ከተባለ የጠፈር ማዕከል የተተኮሰ ሮኬት ስባሪና 10 ጫማ ርዝመት ያለው ብረት በቅጥር ግቢዬ ወድቋል በማለት ቦሪስ አርማቶቭ የተባለ ሩሲያዊ ገበሬ በጠፈር ማዕከሉ ላይ ክስ መስርቷል፡፡ ለዚህም 2 ሺህ 2 መቶ ፓውንድ ካሳ ጠይቋል፡፡ “ምሽት ላይ የሆነ ነገር ቀሰቀሰኝ፡፡ የፍንዳታ ድምፅም ተሰማኝ፡፡ ወንድሜ በወቅቱ ብረቱን አላየውም ነበር” በማለት የቦሪስ እህት ተናግራለች፡፡ ሮኬቶች በአየር ላይ ከተጓዙ በኋላ የመውደቃቸው ሂደት የዕለት ተዕለት የጠፈር ጣቢያው ሂደቶች መሆናቸውን የማዕከሉ ቃል አቀባይ ገልፀዋል፡፡ የሮኬቶቹ ስብርባሪዎች በርግጥም ከገበሬው ቅጥር ግቢ ውስጥ መገኘታቸውን ፍርድ ቤት ካረጋገጠ ገበሬው ካሳ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል፡፡ አዳዲስ ጡቶች የተሰራላት ዶክተሮችን ከሰሰች አንዲት ጀርመናዊት የተሸበሸበ ቆዳዋን ለማስተካከል ካደረገችው ቀዶ ሕክምና ስትነቃ አዳዲስ ጥንድ ጡቶች በማግኘቷ ዶክተሮችን ከሰሰች፡፡ ኢንግሪድ ብሩሊንግ የተባለችው የ33 ዓመት ወይዘሮ በጀርመን ሲቲ ኦፍ ካሴል በተባለ ቦታ ቀዶ ሕክምና ማድረጓ ተገል..ል፡፡ ብሩሊንግ 101 ኪሎ ግራም ትመዝን እንደነበርና ክብደቷን ለመቀነስ በወሰደችው መድኃኒት ሳቢያ የሰውነት ቆዳዋ መሸብሸቡ ሲገለጽ ቆዳዋ በሰውነቷ ውፍረት ልክ እንዲስተካከል ዶክተሮች የጡቶቿን መጠን በሲልካን በማሳደጋቸው ክስ መስርታለች፡፡ ዶክተሮች በበኩላቸው ሴትየዋ ቅሬታ ማቅረብ እንደማይገባት፣ ቆዳን ለማስተካከል የጡቶቿን መጠን መጨመር ከሌሎች የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮዋ የጡት ጌጥዋን እንድታወልቅ ተገደደች በአሜሪካ አንዲት የ37 ዓመት ወይዘሮ ለፍተሻ በጡቶቿ ጫፍ ላይ ያደረገችውን ጌጥ እንድታወልቅ በመጠየቋ የትራንስፖርት ደህንነት ቢሮ ይቅርታ እንዲጠይቅ ጠየቀች፡፡ አንዲ ሀሚን ወደ ቴክሳስ በምታደርገው ጉዞ የደህንነት ሠራተኛው በፌዝ ታጅቦ ጌጣጌጦቿን እንድታወልቅ ስላስገደዳት ክስ ለመመስረት አቅዳለች፡፡ ሀሚን ለጋዜጦች በሰጠችው ገለፃ በሁኔታው መደነቋን፣ መሸማቀቋንና መበሳጨቷን ጠቁማለች፡፡ የደህንነት ሠራተኞች በበኩላቸው ሽብር ፈጣሪዎች አደገኛ መሳሪያዎችን ለፍተሻ በማይመች ቦታ ላይ ሊያስቀምጡ ስለሚችሉና በተጠራጠሩት ቦታ ላይ ፍተሻ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡ ሴት ሽብርተኞች በጡት መያዣ ውስጥ ቦንብ አስቀምጠው የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ እንዳገኙም ተናግረዋል፡፡ ሀሚን ጌጦቿን ለማውለቅ አሻፈረኝ ብትልም በኋላ ላይ ማውለቋ ተገል..ል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |