Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow “ረቂቅ የፕሬስ ሕጉ መከላከያን...
“ረቂቅ የፕሬስ ሕጉ መከላከያን... Print E-mail
Sunday, 06 April 2008
Image“ረቂቅ የፕሬስ ሕጉ መከላከያን እንዳለ አትንኩት የሚል ይመስላል”
አቶ ደበበ ሀ/ገብርኤል የሕግ ባለሙያ

አቶ ደበበ ሀይለ ገብርኤል በ1988 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ ተመርቀዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የፕሪቶሪያ ዩንቨርስቲ በሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ በአፍሪካ የማስትሬት ዲግሪ ይዘዋል፡፡ በከፍተኛ ፍርድ ቤትና በመጀመሪያ ፍርድ ቤት በዳኝነት፣ በአክሽን የባለሙያዎች ማህበር ለሕዝብ በሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተርነት ሰርተዋል፡፡
አሁን ደግሞ በግላቸው አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተሻሻለው የመገናኛ ብዙሀን የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ሕግ ዙሪያ ኃይሌ ሙሉ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ የመገናኛ ብዙሀን የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ሕግ ቀደም ሲል በተለያዩ ሕጎች ተበጣጥሶ የወጣ በመሆኑ ስጋው ተቦጭቆ አጥንቱ ነው የቀረው የሚሉ ወገኖች አሉ፤

አቶ ደበበ፡-
አሁን የወጣው የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ሕግ ስለመረጃ በተለይም ደግሞ ስለመገናኛ ብዙሀን በምንናገርበት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ብቻውን ተፈፃሚነት የለውም፡፡ የተለያዩ ሕጎች አብረው አንድ ላይ መታየት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የብሮድካስት ሕጉ አንዱ ነው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ደግሞ ሌላኛው ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ሕጉ ሳይቀር ሌላ እይታ አለው፡፡ በተወሰነ መልኩ ከዚህ በኋላ የሚቋቋሙ የመገናኛ ብዙሀን ድርጅቶች በኩባንያ መልክ የሚቋቋሙ ስለሚሆን እነሱንም እንደዚሁ ይመለከታል፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስትርን በሚመለከትም ከአዋጅ ቁጥር 430/1996 የተሰጠው ስልጣን አለ፡፡ የተለያዩ የሕግ ክፍሎችን ይነካካል፡፡ አንድን ጉዳይ የሚመለከት ሕግ በሚወጣበት ጊዜ ወጥ ሆኖ ቢወጣ በሕግ ለሚተዳደሩ ሰዎች ይቀላል፡፡ ሕጉን ለሚያስፈፅሙ ሰዎችም አያስቸግርም፡፡ ሕጉ በተለያየ ክፍል ተበጣጥሶ መውጣቱ የራሱ ጉዳቶች አሉት፡፡

ከመገናኛ ብዙሀን ወይም ከፕሬስ ሕግ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ የፕሬስ ሕግ ብዙ ነገሮችን አንድ ላይ አጠቃልሎ መያዝ አለመቻሉ ነው፡፡ አሁን ወደ ቀረበው ረቂቅ ሕግ በምንመጣበት ጊዜ ረቂቅ ሕጉ ሲጀምር ሁለት ነገሮችን አንድ ላይ ይዟል፡፡ አንደኛው የመገናኛ ብዙሀንን የሚመለከተው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የመረጃ ነፃነትን ይመለከታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተወሰነ መልኩ ስለብሮድካስትም የሚናገረው ነገር አለው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ወደ መደበኛ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የሚያመላክት ነገሮች አሉት፡፡ በሀላፊነት የሚያስጠይቁ ብዙ ነገሮች ወደ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሄደዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን የሚመለከተው የብሮድካስት ሕጉም ራሱን በቻለ መልኩ ተቀምጧል፡፡ ያም ሆኖ ግን ይህ ሕግ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመውጣቱ ስጋ የለውም፤ አጥንቱ ነው የቀረው፤ ዋና ዋና ነገሩ ሄዷል የሚለው ጉዳይ አጨቃጫቂ ነው፡፡ መሰረታዊ የሆኑ መርሆዎችን በመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ሕግ ውስጥ እናገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመገናኛ ብዙሀን የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ሕግ ላይ መካተት የነበረባቸው ጠቃሚ ሕጎች በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ የተካተቱበት ሁኔታ ይታያል፡፡

የፕሬስ ረቂቅ ሕግ ሙሉ በሙሉ አጥንቱ ነው የቀረው ባንልም በጣም ወሳኝ የሆኑ መርሆዎች ወደ ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ተወስደዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመረጃ ነፃነት ሕግና የፕሬስ ሕግ ተለያይተው መውጣት ነበረባቸው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ?

አቶ ደበበ፡-
አለመለያየቱ ችግር አለው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ችግር የለውም የሚሉም አሉ፡፡ የመረጃ ነፃነት ሕግና የፕሬስ ሕግ ልዩ የሚያደርጋቸውና የሚያመሳስላቸው ባህሪያት አሏቸው፡፡ ለመገናኛ ብዙሀን ሥራ መረጃ የማግኘት ነገር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ መረጃ የማግኘት መብት የማንኛውም ሰው መብት ነው፡፡ የጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፡፡

በመገናኛ ብዙሀን ላይ ያሉት ችግሮች፣ ድክመቶች እና ጥንካሬዎች ጎልተው እንዳይወጡ በመረጃ ሕጉ ተይዘዋል፡፡ የመረጃ ሕጉም በመገናኛ ብዙሀን ሕጉ የመሸፈን ሁኔታ ይታይበታል፡፡ ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ የመረጃ የማግኘት መብት የማንኛውም ዜጋ መብት በመሆኑ ጋዜጠኛውን ብቻ ከሚመለከተው ነገር ጋር ሌላ ነገር ለምን አደበላልቀን እናወጣለን? የሚል ነው፡፡ ራሱን ችሎ ቢወጣ ኖሮ ለጥንካሬው ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ የመረጃ ሕጉ እንባ ጠባቂ የመሳሰሉትን ሌሎች አካላት ያካትታል፡፡ የእያንዳንዱን የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ጭምር ይዳስሳል፡፡ እንዲያውም ሕጉን ትልቅ አድርጎ እንዲወፍር ያደረገው የመረጃ ሕጉ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙሀንን የሚመለከተው ክፍል ውስን ነው፡፡ ሁለቱ ሕጎች ተለያይተው ቢወጡ ኖሮ ተመራጭ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ተለያይተው ባይወጡም ሕጉ ፈጽሞ አያሰራም ወደሚለው ድምዳሜ አያደርስም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የተዘጋጀውን ረቂቅ ሕግ የተፈፃሚነት ውስንነት እንዴት ያዩታል?  በአንድ ሕግ ላይ ጋዜጣን፣ መጽሄት፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ሙዚቃ፣ ፓምፕሌት ወዘተ መግዛት የሚችል ሕግ ማዘጋጀት ይቻላል?

አቶ ደበበ፡
- በረቂቅ ሕጉ ላይ ያለውን ትርጉም ስንመለከት እነዚህን ያነሳሀቸውን ነገሮች በሙሉ የሚጨምር ይመስላል፡፡ ነገር ግን ውስጥ ተገብቶ ሲታይ በርግጠኝነት የሚመለከተው በየጊዜው የሚወጡ የህትመት ሥራዎችን ብቻ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያን አያይም፡፡ ኢንተርኔትን አይመለከትም፡፡ ለዚህ ከአርቃቂዎች የተሰጠው ምላሽ ኢንተርኔትን በተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግ ወጥቶ ነው ሊታይ የሚገባው፡፡ አሁን ባለንበት የእድገት ደረጃ በኢንተርኔት ላይ ያሉ ችግሮች ያን ያህል ችግር ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡ አይደሉም የሚል ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ሕጉ የተለያዩ ነገሮችን ይበል እንጅ በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርገው በየጊዜው ታትመው በሚወጡ የህትመት ውጤቶች ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተዘረዘሩትን ጉዳዩች የማያካትት ከሆነ ለምን መጥቀስ አስፈለገ?

አቶ ደበበ፡-
አንዱ የሚነሳው ክርክር ይህ ነው፡፡ አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች የማይሸፍንና የማያካትት ከሆነ ለምን መጥቀስ አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ሕጉ በኢንተርኔት ላይ የማይሰራ ከሆነ ትርጉም መስጠቱ ለምን አስፈለገ? ኤሌክትሮኒክስ ነክ የሆኑ የህትመት ውጤቶችን የማይመለከት ከሆነ ለምንድነው ትርጉም እንዲሰጥ የተደረገው? የህትመት ስራ የሚለው ሲተረጎም መገናኛ ብዙሀን እንዲሁም ለሕዝብ እንዲደርሱ ታስቦ የሚሰራጩ የሙዚቃ ስራዎችን የኦዲዮ ቪዥዋል ስራዎችን፣ ስዕሎችን፣ ተውኔቶችን፣ ካርቶኖችን መፃህፍቶችን በራሪ ጽሁፎችን፣ ፊልሞችን ፖስተሮችን እንደሚያካትት ይገልፃል፡፡ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሲኬድ በየጊዜው ታትመው የሚወጡ የሕትመት ስራዎችን እንጅ እላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች አይመለከትም፡፡ ለህትመት ስራዎች የተሰጠው ትርጉም ሰፍቷል፡፡ የማያስተዳድራቸውን ነገሮች ሁሉ ጨምሯቸዋል፡፡

ይህ ረቂቅ ያላለቀለት ረቂቅ ነው፡፡ ወደፊት የመሻሻል ስራ እንደሚደረግበት አርቃቂዎቹም ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ማሻሻያው ሲሰራ እንደዚህ የተለጠጠውን ጉዳይ የመሰብሰብ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ በሕግ ማርቀቅ ስራ ውስጥ በትርጉም ላይ የሚቀመጡ ነገሮች በዋና ሕጉ ውስጥ የምናገኛቸውንና ተደጋግመው የሚመጡ ጉዳዮችን ነው፡፡ የማይሰራበትንና ተደጋግሞ የማይመጣን ነገር ትርጉም ላይ ማስቀመጥ አያስፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- የፈቃድ፣ የምዝገባና የብቃት ማረጋገጫን አስፈላጊነት በተመለከተም የተለያዩ ጥያዌዎች ይነሳሉ፡፡ ለሁሉም አይነት የመገናኛ ብዙሀን የፈቃድ የምዝገባና የብቃት ማረጋገጫ ያስፈልጋል ወይ? የሙያ ማረጋገጫ መስጫ ፈቃድ ቀነ ገደብ አለመኖሩም እንደ ችግር ይነሳል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ደበበ፡
- በሕጉ ውስጥ እንደ አንደ ድክመት ተደርጎ የሚነሳው ነገር ከምዝገባና ከምስክር ወረቀት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጉዳይ ነው፡፡ ስልጣኑ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር መሰጠቱም አግባብ  አይደለም የሚል ክርክርም ይነሳል፡፡ ስልጣኑ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ቢሰጥ እንኳን ሚኒስቴሩ በምን ያህል ጊዜ ነው ፈቃዱን መስጠት ያለበት? አልሰጥም ቢል ወዴት ነው መሄድ ያለበት? እነዚህንና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ለምሳሌ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከሚይዛቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ይሄ ነው፡፡ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ፈቃድ ካልሰጠህ እንደተሰጠህ ይቆጠራል፡፡ እምቢ ብትባል ይግባኝ መጠየቅ ትችላለህ፡፡ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን ይህንን አያካትትም፡፡ አርቃቂዎቹ ለዚህ የሚሰጡት ትንተና ለማስታወቂያ ሚኒስቴር የተሰጠው ስልጣን መረጃን የመስጠት ያህል ነው በሚል ነው፡፡ ከዚያ የዘለለ የመከልከልና ያለመከልከል ስልጣን የለውም ይላሉ፡፡ ነገር ግን የአርቃቂዎቹን ምክንያት እንዳለ እንዳንቀበል የሚያደርገን እውነት አለ፡፡ አንድ ድርጅት ሳይመዘገብ ስራ ቢጀምር በወንጀል ይጠየቃል፡፡ ከፍተኛ ቅጣትም ይጣልበታል የሚል በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ የምዝገባ ፈቃድ መስጠት ጉዳይ ዝም ብሎ መረጃ የመስጠት ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሄደው ከተመዘገቡ በኋላ በኩባንያ መልክ የሚቋቋሙት ድርጅቶች በቀጥታ ሥራ መጀመር ይችሉ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ በማንኛውም ጊዜ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚፈለገውን መረጃ መውሰድ ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ ድርጅቶቹ ንግድና ኢንዱስትሪ ከተመዘገቡ ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ ይህንን ማድረግ አለባቸው የሚል ነገር መኖር ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ አልሆነም፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሄዶ ተመዝግቦ ፈቃዱን አውጥቶ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ባይሰራ ፈቃዱ እንደተሰረዘ ይቆጠራል የሚል ሕግ አለ፡፡ ከምዝገባ ጋር ተይይዘው የተቀመጡ እነዚህንና የመሳሰሉትን አስገዳጅ ነገሮች ስናይ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚሰራው ስራ መረጃ የመስጠት ሥራ ብቻ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ የሥራ ፈቃድ ለአንድ ድርጅት የህልውናው መሰረት ነው፡፡ ፈቃድ ሳይዝ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሳይመዘግበውና ሰርተፊኬት ሳይሰጠው ሊሰራ አይችልም፡፡ አርቃቂዎቹ እንደሚሉት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥራ ቴክኒካል አይደለም፡፡ የመረጃ ጉዳይ ቢሆኑ ኖሮ ፈቃድ ሳትይዝ መስራት አትችልም ባልተባለ ነበር፡፡ ለመስራት ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሄዶ መመዝገብ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚከታተለው ምዝገባን ብቻ አይደለም፡፡ ሰርተፍኬትም መውሰድ እንዳለብህ ይገልፃል፡፡ ድርጅቱ ይህንን ሳያሟላ ስራ ቢጀምር ይቀጣል፡፡ በረቂቅ ሕጉ አንቀጽ 8/1 ..የተመለከተውን የምዝገባ ግዴታ የጣሰ ወይም በአንቀጹ የተመለከቱትን ግዴታዎች ያላሟላ በየጊዜው የሚመጣ የህትመት አሳታሚ ወይም ብሮድካስተር እስከ ብር 15 ሺ የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይከፍላል.. ይላል፡፡ ይህ የሚያሳየው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥራ መረጃ የመስጠት ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ ሰርተፍኬቱ ከሌለህ ህገወጥ ስለሆንክ ልትሰራ አትችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በምዝገባ ፈቃድ ሰበብ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል?

አቶ ደበበ፡
- የዜጎችን በነፃነት የመደራጀት መብት ወይም ደግሞ ወደፈለጉት የሥራ መስክ የመግባት መብትን በምዝገባ መከልከል ይቻላል፡፡ ብዙ አገሮች ምዝገባን መሰረት በማድረግ በመብት ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ምዝገባ የመከልከል አቅም አለው፡፡ አንድ ድርጅት ከማስታወቂያ ሚኒስትር ሰርተፊኬት ካላገኘ ወደ ሥራ መግባት አይችልም፡፡ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር የተሰጠው ሥልጣን መረጃን የመቀበል ብቻ ሳይሆን የመወሰን ጭምር ነው፡፡ ይህ የሕጉ አንዱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ረቂቅ ሕጉ በማስታወቂያ ሚኒስቴር አማካኝነት ሊፈጸሙ የሚችሉ የመብት ጥሰቶችን የሚከላከሉ አንቀፆች በውስጡ መያዝ አለበት፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሰርተፍኬቱን መስጠት አለበት፡፡ እስከዚህ ቀን ድረስ ሰርተፍኬቱን ባይሰጥ እንደተመዘገበ ይቆጠራል የሚል ነገር መካተት ነበረበት፡፡ ዝምታም መከልከል ነው፡፡  ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ከዚህ የሚጠብቅ ሕግ መኖር ነበረበት፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ የመገናኛ ብዙሀን ወይም የፕሬስ ውጤት ላይ ጥፋት በተሰራ ጊዜ በሀላፊነት መጠየቅ አለበት የሚባለው ሰው ከፕሬስ አዋጅ በፊት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ ከፕሬስ አዋጅ በኋላ በፕሬስ ሕግ፣ አሁን ደግሞ በ95ቱ የፕሬስ አዋጅ ተካቶ በነበረውና የ96ቱ የወንጀል አካል ሆኖ በጸደቀው ሕግ መሰረት ሆኗል፡፡ ይህ ወደኋላ መመለስ ነው የሚሉ አሉ፤

አቶ ደበበ፡
- ቀደም ሲል በነበረው በ1949 የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በየጊዜው በሚወጡ የህትመት ስራዎች ላይ ወይም በሚዲያ ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች ሀላፊ የሚያደርጉት ጸሐፊውን ነበር፡፡ ዋና አዘጋጁ ተጠያቂ የሚሆነው የጸሐፊውን ስም ለመግለጽ ካልፈለገ ብቻ ነው፡፡ ይህ ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከመሻሻሉ በፊት ሲሰራበት የቆየ ነው፡፡ አሁን በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይና ረቂቅ ሕጉ ላይ ግን ሌላ ሰው ፃፈውም አልፃፈውም በዋናነት ሃላፊነቱ የሚመለከተው ዋና አዘጋጁን ነው፡፡

አሁን በተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ አንቀጽ 5 ላይ ዋና አዘጋጁ ያላመነበት ነገር አይወጣም የሚል ለዋና አዘጋጁ የተሰጠ ሰፊ ስልጣን አለ፡፡ በተሻሻለው ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ሀላፊ ያደረገው ዋና አዘጋጁን ነው፡፡ ቀደም ሲል ዋና አዘጋጁ ምንጩን አሳልፎ እስከሰጠ ድረስ ተጠያቂ አይሆንም ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉንም ሀላፊነት የሚወስደው ራሱ ነው፡፡
በረቂቅ ሕጉ ላይ በተለይ ከሙስና ጋር በተያያዘ ማስረጃ ለሚሰጡ አካላት የሚደረግ ጥበቃ አለ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸው እንዳይገለጽ ለሚፈልጉ ሚስጥራዊ ለሆኑ የመረጃ ምንጮች በግልጽ የሚሰጥ ጥበቃ የለም፡፡ ለእነዚህ የመረጃ ምንጮች ጥበቃ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ስለአንድ ነገር መረጃ ያላቸው ነገር ግን ስማቸውን በአደባባይ አውጥተው መፃፍ የማይፈልጉ ሰዎች በመፍራት ያገኙትን መረጃ ማጋለጥ ሊያቆሙ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ማስታወቂያ ሚኒስቴር ማወያየትና ተቆጣጣሪ ሆኖ መስራት የሚያስችለውን ባህሪ እያጣ መጥቷል፤ ስለዚህ የዚህ ባለቤት እሱ መሆን የለበትም የሚሉ አሉ፤

አቶ ደበበ፡-
ማስታወቂያ ሚኒስትርን አስመልክቶ የሚነሳው ክርክር ከጥቅም ግጭት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በቅርበትም ይሁን በርቀት የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሀን ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሊሆን ይችላል፤ ኢቲቪ ሊሆን ይችላል፣ ሬዲዮ ሊሆን ይችላል፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንደሌላው ሚዲያ ድርሻ ያለው አካል ስለሆነ እርሱም እንደነሱ ሆኖ ከመወያየት በስተቀር የቁጥጥር ስልጣን ሊሰጠው አይገባም፡፡ ፉክክር ስለሚኖር የጥቅም ግጭትን ያመጣል የሚል ነው፡፡ ሌላው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪ አካል መሆኑ እሱ ጋር የሚሰሩ ሰዎችን ነፃነት ይጎዳል፡፡ ስለዚህ የማስተዳደር ስልጣኑ ሊሰጥ የሚገባው ገለልተኛ ለሆነ አካል ነው የሚል ነው፡፡ በርግጥ አሁን በቀረበው ረቂቅ ሕግ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ስልጣን ከምዝገባና ሰርተፊኬት ከመስጠት ጋር ተያይዞ ነው የቀረበው፡፡ ያም ሆኖ ግን እንደዚህ አይነት ስልጣን ሊሰጠው አይገባም፡፡ ከስራ ጋር በተያያዘ ለተጋጨው ሚዲያ ሁሉ ፍቃዳችሁን ሰርዣለሁ፣ አላድስም ሊል ይችላል፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴርና እሱ የሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች እንደማንኛው ተቋም በትችት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ አንድ የግል ሚዲያ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን የሚመለከት ነገር ቢያወጣና ቢተች ሰርተፍኬቱ ላይታደስለት ይችላል፡፡ በዚህም የጥቅም ግጭት ይፈጠራልና ይህ ስልጣን ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ሊሰጥ አይገባም የሚል ነገር ነው የሚነሳው፡፡ የሚነሳው ክርክር መሰረት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል በነበረው ሕግ ደህንነትን በተመለከተ የተዘጋጀ ግልጽ ሕግ ባለመኖሩ ሚዲያዎች ከደህንነት ጋር የተያያዘ መረጃ ለማውጣት ይሰጉ ነበር፡፡ በዚህ በኩል በአሁኑ ረቂቅ ሕግ የተሻሻለ ነገር አለ?

አቶ ደበበ፡-
በረቂቅ ሕጉ አንቀጽ 22 ላይ ከመከላከያ ጋር በተያያዙ ምን አይነት መረጃዎች ናቸው መውጣት ያለባቸው? እንዴት ነው የሚወጡት? በሚል የመከላከያ ደህንነትና አለም አቀፍ ግንኙነትን አስመልክቶ በዝርዝር የተቀመጠ አለ፡፡ ይህ አንቀጽ አጨቃጫቂ ከሆኑት አንቀጾች መካከል አንዱ ነው፡፡ የአንቀጹ አቀማመጥ አንድ ግለሰብ የመከላከያ አባል ከሆነ ምንም ሊጠይቅ እንደማይችል የሚገልጽ ይመስላል፡፡ አንቀጹ ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲፃፍ እንደሚደረግ አርቃቂዎቹ ተናግረዋል፡፡ ከደህንነት ጋር በተያያዘ የተረቀቀው የዚህ ሕግ አንዱ ጥቅም ሚስጥር ተብለው የሚለዩት ጉዳዮች ምንድናቸው ብለን መለየት የሚያስችለን መሆኑ ነው፡፡ ከመከላከያ ጋር ተያይዘው ሊወጡ የማይችሉ ጉዳዮች በግልጽ ይቀመጣሉ፡፡ የዚህ አንቀጽ ዋናው ችግር ግን የቋንቋ አገላለጹ ነው፡፡

መከላከያን እንዳለ አትንኩት የሚል ይመስላል፡፡ አንድ የመከላከያ አባል ሰው እንደመሆኑ መጠን ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ከሙስና ጋር በተያያዘም ሆነ በሌላ መልኩ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ እንደዚህ አይነት ክስተቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ይህ ሰው የመከላከያ አባል ነውና ሊጠቀስ አይገባውም ሊባል አይችልም፡፡ የመከላከያ ተቋም እንደማንኛውም የመንግሥት ተቋም ችግር ውስጥ በሚወድቅበት ጊዜ መከላከያ ስለሆነ ምንም ነገር ሊባል አይገባውም ተብሎ ከምንም አይነት ትችት ነፃ እንዲሆን አይፈለግም፡፡
መከላከያን አስመልክቶ ሊገለፁ የማይገቡ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው ተብሎ በግልጽ መቀመጥ አለበት፡፡ በመረጃ ሕጉ ይህንን ለማስተካከል መሞከሩ ለጋዜጠኛው ጥሩ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ያለውን ፍርሀት ይገድበዋል፡፡ ወሰኑ ሰፋ ወይም ጠበበ የሚለው ሌላ ክርክር ይሆንና ቢያንስ ግን ከዚህ በኋላ ይህንን ልትጽፍ ትችላለህ መባሉ ጥሩ ለውጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  የፕሬሱን ረቂቅ ሕግ የሚያወያዩ ባለሥልጣናት ብዙ ጊዜ ሲያወያዩ አንዱ ረቂቅ ሕግ የተወሰደው ከጀርመን ነው ይሄኛው ከፈረንሳይ፣ ያኛው ደግሞ ከስዊድን ነው በማለት ጥሩነቱን ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድን እየጠቀሱ የኢትዮጵያ ሕግ ከሌሎች ሀገሮች የማያንስ አለመሆኑን ለማሳየት የሚያቀርቡት መከራከሪያ የሚያስኬድ ነው?

አቶ ደበበ፡-
ከሀገራቱ ልምድና ተሞክሮን መውሰድ የራሱ ጥቅም አለው፡፡ ሌሎቹ የገጠማቸውን ችግር ማየት እኛ ወደፊት ሊገጥመን ከሚችለው ችግር ሊያድነን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሀገራት ልምድ በሚወሰድበት ጊዜ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ ፈረንሳይ፣ በዚህ አንቀጽ ስዊድን፣ በዚህ አንቀጽ ኢንዶኔዥያን፣ በዚህ አንቀጽ ካናዳን እያልን የምንሄድ ከሆነ ወጥ የሆነ ነገር አይሰጠንም፡፡ አንቀፆቹን በሙሉ የምናቋቁመው ለእያንዳንዱ አንቀጽ አንዳንድ አገር እየፈለግን ከሆነ ኋላ ላይ የህጉን አጠቃላይ መዋቅር ስናይ የሚሰጠን ስዕል የተለየ ነው የሚሆነው፡፡

መሠረታችን የካናዳ ነው ካልን አብዛኛው ክፍል የካናዳ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ የእኛን የሲቪል ኮድ ብንመለከት ከሌላ አገር ተገልብጦ የመጣ ነው፡፡ የፍትሀ ብሄር ስነ ሥርዓት ሕጉ የመጣው ከህንድ ነው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉም ከሌላ አገር ነው የመጣው፡፡ የሚረቀቀው ሕግ በዚህ መልኩ ሲሰራ በሕጉ ላይ ያለው ባህሪ ተመሳሳይ ይሆናል፡፡ አንዷን አንቀጽ ከአንድ አገር አንዷን አንቀጽ ከሌላ አገር የምናመጣ ከሆነ ሕጉ ይጠብቃል፡፡ በተለይ በተሞክሮ የምናመጣቸው ሕጎች በባህሪያቸው ገዳቢ በሚሆኑበት ጊዜ አጠቃላይ የሕጉ መዋቅር ገዳቢ ይሆናል፡፡ ገደብን መሰረት ለማድረግ የተለያዩ አገራትን እየጠቀስን፣ ይህንን መብት የገደብነው በእከሌም አገር ጋር ስለተገደበ ነው እያልን የገደብ መሰረቶችን ከተለያዩ አገሮች የምናመጣ ሲሆን አጠቃላይ ሕጉ ገዳቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የካናዳን ሕግ ሙሉ በሙሉ ስንወስድ አንዱ ጋር የሚገድብህ ከሆነ በሌላ በኩል የሚሰጥህ መንገድ ይኖራል፡፡ እንድትሰራ የሚያስችልህ መፈናፈኛ ይኖርሀል፡፡ ነገር ግን ከካናዳ ላይ ይህችን አንቀጽ እንውሰድና እናጠናክረው፤ ከካናዳ ላይ ያለውን ክፍት ቦታ ከፈረንሳይ እንውሰድና እንድፈነው፡፡ እዚህ ጋር ያለውን ክፍተት ደግሞ በዚህ እንድፈነው እያልን ስንሄድ አጠቃላይ ሕጉ ገደብ ይሆንብናል፡፡ ለእያንዳንዱ ገደብ የሀገራትን መሰረት እየጠቀስን የምናነሳ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ከሚሆን አብዛኛውን ሕግ ከአንድ አገር ወስዶ የተወሰነው ከሁለትና ሶስት ሀገሮች ቢጨመር የተሻለ ይሆናል፡፡ ይህንን ስናደርግ የሕግ መዋቅር ቅርጽ እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ከዚያም አጠረቃቅመን የምናቋቁመው አንድ ሕግ የገደብ መሰረቱ ይበዛል፡፡ ሕጉ ሊደርስበት የሚፈልገውን ነገር ያሳጣዋል፡፡ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ የሀገራትን ልምድ ማየቱ ችግር የለውም፡፡ ግን ቁጥሩ ባይበዛ ተመራጭ ነው፡፡ በአንድ ሕግ የበርካታ ሀገሮችን ልምድ ማስገባት (በተለይ ደግሞ ለገደብ) ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥትና በግል ሚዲያዎች የሚሰሩ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እንደሌሎቹ አገሮች ጋዜጠኞች ማህበር በማቋቋም ለመብታቸው የማይታገሉበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ደበበ፡-
ይህ የባለሙያ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር በሚዲያ ስራ የተሰማሩ ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆን በሌላ ሙያ ውስጥም ያሉ ባለሙያዎች ችግር ነው፡፡ አንድ ላይ ተሰባስቦ፣ ለአንድ አላማ ሙያን መሰረት በማድረግ፣ የፖለቲካ አመለካከታቸውን ትተው ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚሰሩ ጠንካራ ድርጅቶች ያለመኖር ችግር አለ፡፡ ባለሙያው ተሰባስቦ ድምጹን አንድ ላይ የሚያሰማ ቢሆን የሚታዩ ችግሮችን በቀላሉ መቅረፍ ይቻል ነበር፡፡ ከሚዲያ ጋር ተያይዞ በሌሎች አገሮች የፕሬስ ካውንስል ይቋቋማል፡፡ ይህ የፕሬስ ካውንስል አሁን በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘጋጀውን ረቂቅ ሕግ አይነት በማዘጋጀት ባለሙያዎቹን ራሱ ይቆጣጠራል፡፡ በመደበኛው የፍርድ ሥርዓት ውስጥ አለማለፍን ሁሉ ያመጣል፡፡ አሁን በፕሬስ ረቂቅ ሕጉ ላይ የምናያቸው አንዳንድ ቅጣቶች የፕሬስ ካውንስል ቢኖር ኖሮ በእሱ ሊያዝ ይችል ነበር፡፡ አሁን ባለው እውነት ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችልና የተደራጀ ማህበር የለንም፡፡ ራሱን በራሱ ማስተዳደር የሚችል ጠንካራ ማህበር ቢኖር ምናልባትም መንግሥት እንደዚህ አይነት ሕጎችን ላያወጣ ይችል ነበር፡፡ የሚወጡትም ሕጎች የላሉ ሊሆኑ ይችል ነበር፡፡ ጠንካራ ማህበር አለመኖሩ አሁን የታየው ችግር እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይሁን እንጅ ከአሁን በኋላም ቢሆን ራሱን በራሱ ሊያስተዳድር የሚችል የሙያ ማህበር ቢመሰረትና ከዚያም አልፎ የፕሬስ ካውንስል ማቋቋም ቢቻል ይህንን ሕግ ወደ ማስለወጥ ሊሄድና እንዲሻሻል ሊያደርግ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የረቂቅ ሕጉ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ምንድናቸው?

አቶ ደበበ፡
- ስለፕሬስ መቋቋም የሚገልፀው የድሮው ሕግ በመንግሥት በመቋቋም ቅርጹን እስከ መወሰን ድረስ ይሄድ ነበር፡፡ በአሁኑ ረቂቅ ሕግ ግን ይህ ጉዳይ ለባለሙያው ተትቷል፡፡ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ተሰጥቶት የነበረው ሰፊ ስልጣን ቀንሷል፡፡ ይህ እንደ አንድ ጥንካሬ የሚታይ ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የፕሬስ ረቂቅ ሕግ ቅጣትን ጨምሮ እስራት ነበረው፡፡ የአሁኑ ረቂቅ ሕግ ግን የገንዘብ ቅጣት ብቻ እንጅ የእስራት ቅጣት የለውም፡፡ በጋዜጠኞች ላይ የሚቀርቡ ክሶችን በተመለከተም በተቻለ መጠን በተፋጠነ ሥርዓት እንዲታይ የአሁኑ ረቂቅ ሕግ ይናገራል፡፡ በምርመራ ወቅት ጋዜጠኞች እንዳይታሰሩ የሚገልጸውም ነገር አለ፡፡ ይህም አንድ ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡ ከመረጃ ጋር በተያያዘ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሕግ መውጣቱም እሰየው ያስብላል፡፡

ረቂቅ ሕጉ የፕሬስ ሕጉንና የመረጃ ሕጉን አንድ ላይ አጣምሮ መውጣቱ አንዱ ድክመት ነው፡፡ የወጣቶችን ደህንነትን አስመልክቶ በረቂቅ ሕጉ ላይ ምንም ነገር አለመገለጹ ሌላው ድክመት ነው፡፡ ከመረጃ ጋር በተያያዘ  የሚጠየቀው ጊዜ እስከ 30 ቀን መሆኑም እንደ ድክመት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ 30 ቀን ለጋዜጠኞች ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ላይ የሚነሳው አንዱ ትችት የጊዜው ልዩነት እንደጠያቂው ማንነት እየታየ ሊቀመጥ ይገባው ነበር የሚል ነው፡፡ በአጠቃላይ የመረጃ ሕጉ ላይ የሚከለከሉ ነገሮች መብዛታቸውም ትልቅ ድክመት ተደርጎ የሚገለጽ ጉዳይ ነው፡፡   
 
< Prev   Next >