| የጤና ሕግ አጥኚ |
|
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ ቀደም ሲል የሳይንስ ተማሪ ነበር፡፡ የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያለ ግን ፍርድ ቤት በያዘው የቤተሰቦቹ ጉዳይ ኢፍትሀዊ ሁኔታ መመልከቱ ሕግ ለመማር ፍላጐት እንዳሳደረበት ወጣት ደረጀ ሽመልስ ይናገራል፡፡ /የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ሳይንስ ማጥናት አስብ ነበር፡፡ የቤተሰቦቼን የፍርድ ቤት ጉዳይ ከተመለከትኩ በኋላ ግን ሃሳቤን ቀይሬ ሕግ ለማጥናት ወሰንኩ፡፡ ቤተሰቦቼ ደግሞ በዚህ ደስተኞች አልነበሩም/
በአሁኑ ወቅት በቱሌን ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ፕሮግራም የጤና ሕግ አጥኚ ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡ አስራ አምስተኛ የመላው አፍሪካ ሰብዓዊ መብት ሙት ኮርት ውድድር ላይ የተሳተፈ ሲሆን በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎች ፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት የማግኘት ሕጋዊ መብትንና በዚህ ረገድ የመንግሥታት ግዴታ ምን ይመስላል በሚሉ ነጥቦች ላይ የሚያተኩር ውድድር ነበር፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ሰባ ከሚሆኑ የአፍሪካ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተወዳዳሪዎች የተካፈሉ ሲሆን ውድድሩም ጠንካራ ነበር፡፡ በመላው አፍሪካ ሙት ኮርት ውድድር ላይ መሳተፉ የመመረቂያ ፅሑፉን ከአገር አገር ከሚደረግ ዝውውር ጋር በተያያዘ የሚደረግ የግዴታ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ላይ ለመሥራት መሠረት እንደሆነው ይናገራል፡፡ ግለሰቦች ከአንድ አገር ወደ ሌላ የሚያደርጉትን ዝውውር አገራት መገደብ የሚችሉበት ሁኔታ በሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽኖች ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የግለሰቦችን ጉዞ ማገድ የሚቻለው የግለሰቦቹ ዝውውር የህብረተሰብ ጤና ላይ አደጋ የሚጥል ወይም ግለሰቦቹን የያዛቸው ሕመም ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ የሚጠይቅ ሲሆን ነው፡፡ እንደ ቲቢ፣ ኢቮላና ሳርስ በቀላሉ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን በሚመለከት አገራት የግዴታ ምርመራ ማስቀመጥና ዝውውር መግታት ይችላሉ ብሏል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መንግሥታት ዝውውርን ሲያግዱ የሚያስቀምጡት ምክንያት የህብረተሰብ ጤና አደጋ ላይ ይወድቃል አልያም ለተቀባዩ መንግሥት የኢኮኖሚ ጫና ይፈጥራል የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኤች.አይ.ቪ የግዴታ ምርመራ በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎችን ማግለል ሊሆን እንደሚችል ወጣት ደረጀ ከአገር ወደ አገር የሚደረግ ዝውውርና የግዴታ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የመመረቂያ ጽሑፍ አስረድቷል፡፡ በ1980ዎቹ እንደ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋምና ሌሎችም የተመድ ኤጀንሲዎች ኤች.አይ.ቪን የህብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ ሊያስከትሉ ወይም መንግሥታት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ ከሚባሉ በሽታዎች ተርታ መመደብን በማስመልከት ከዚህ ጋር በተያያዘ የግዴታ የምርመራና የዝውውር እገዳ መጣል እንደማያስፈልግ ለአገራት መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር፡፡ ነገር ግን አገራት እስከ አሁንም ይህንን መልዕክት ተግባራዊ እያደረጉ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን የዝውውር እገዳ የማንሳት አዝማሚያ እያሳዩ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ ፈረንሳይና ሉግዘምበርግን በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ አፓፕ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዘጋጀው የአፍሪካ ሙት ኮርት ውድድር ላይ በማሸነፍ ሠርተፍኬት ኦፍ ሜሪት አግኝቷል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ውድድር ላይም የመመረቂያ ፅሑፉን በማቅረብ አሸናፊ በመሆን ሽልማት ለማግኘት ችሏል፡፡ ኤች.አይ.ቪ ከሰብዓዊ መብትና ከሕግ ጋር ባለው ግንኙነት ዙሪያ በተለያዩ ውድድሮች ላይ መሳተፉ የመመረቂያ ጽሑፉን በዚሁ ጉዳይ ላይ እንዲሠራ እንዳስቻለውና በቱሌን ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍም ለመቀጠር ምክንያት እንደሆነው ገል..ል፡፡ የመመረቂያ ጽሑፍህን ስታዘጋጅ መረጃዎችን እንዴት አገኘህ ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ /ከአገር ወደ አገር በሚደረግ ጉዞና የግዴታ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት ቀላል አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ የቤልጂየም ኤምባሲና የደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል ከዓለም አቀፍ የጤና ሕግ ጋር በተያያዘ የተሠሩ ጥናቶችንና መረጃዎችን ረድተውኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅም የተለያዩ መረጃዎችና ጥናቶችን አግኝቻለሁ/ በማለት መልሶልናል፡፡ ደረጀ እንደገለፀው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ ዲግሪ የሕግ ትምህርት ሲሰጥ ከጤና ሕግ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ኮርስ አይሰጥም፡፡ የጤና ሕግን በሚመለከት የቱሌን ዩኒቨርሲቲ ፕሮግራም የመጀመሪያው ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ በአብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች ላይ የሚንፀባረቅ ሲሆን የኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ አገራት የግለሰቦች ዝውውር ላይ ገደብ መጣል ወይም የግለሰቦቹን የምርመራ ውጤት መመልከት የሚችሉባቸው ሁኔታዎች በሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽኖች ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አንፃር የግዴታ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ከአገር ወደ አገር ለሚደረግ ጉዞ አስፈላጊ አይደለም የሚል ድምዳሜ በጽሑፉ አስቀምጧል፡፡ ደረጀ በመመረቂያ ጽሑፉ ኤች.አይ.ቪ ህብረተሰብን በማስተማር ተፅዕኖ ሊደረግበት የሚችል በሽታ በመሆኑ የግዴታ የጉዞ የምርመራ እንዲኖር ማድረግ በተዘዋዋሪ በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎችን ማግለል እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ከዚህ በፊት ኤች.አይ.ቪና ሕግ በሚል ርዕስ ኤች.አይ.ቪና የቅጥር ሁኔታን እንዲሁም ሕግ የኤች.አይ.ቪን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሊኖረው የሚችለውን ሚና በሚመለከት የተሰሩ ጥናቶችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝቶ እንደነበር፣ ከዝውውር ጋር የተያያዘ የግዴታ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ላይ የመመረቂያ ፅሑፉን መስራቱ በጤና ሕግ ዙሪያ ለሚደረጉ ሌሎች ጥናቶች ጥሩ መረጃ እንደሚሆን አስረድቷል፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |