Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow “የመሪዎች የአመለካከት ልዩነት...
“የመሪዎች የአመለካከት ልዩነት... Print E-mail
Sunday, 06 April 2008
“የመሪዎች የአመለካከት ልዩነት ሰላማዊ ትግሉን እየጎዳው ነው”
የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ)

በቅርቡ የተመሰረተው ኢፍዴሃግ ፓርቲ፣ የግንባሩን ምስረታ ቀን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ በፓርቲ መሪዎች አመለካከትና ፍላጎት የሚፈጠሩ ልዩነቶችና ችግሮች ለአጠቃላይ የሰላማዊ ትግሉ መዳከም ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡

የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት ግንባር (ኢፍዴሃግ) በ25/7/200 ዓ.ም. በእንጦጦ የምግብና የመዝናኛ አዳራሽ የምስረታ ቀኑን አስመልክቶ ባወጣው ባለሰባት ነጥቦች መግለጫ የግንባሩ መስራች ድርጅቶችም ሆነ የሌሎች በርካታ የትግል ድርጅቶች ባለፉት 17 ዓመታት ያደረጉት ሰላማዊ ትግል መገምገማቸውን በመግለፅ፣ “ተለያይተን በመታገላችን ለህዝቡና ለሃገሪቷ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ አግኝተናል የምንለው ተጨባጭ ነገር እምብዛም የለም” ብሏል፡፡

“ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ አሁንም ገና ረጅም መንገድ ይቀረናል፣ ብርቱ መስዋእትነትም ይጠበቅብናል” የሚለው የግንባሩ መግለጫ፣ ረጅም መንገዱ በተናጠል ከመጓዝ የተበታተነውን የትግል ኃይል ወደ አንድ የትግል መድረክ በመለወጥ ድካሙን ማቃለል እንደሚቻል የአባል ፓርቲዎቹ እምነት እንደሆነ ያትታል፡፡

የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ግርማይ ሃደራ ይህንን አስመልክተው፣ “ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣትና የህዝብ የበላይነት ለማረጋገጥ፣ ለፍትህና ለሰብአዊ መብቶች መከበር በፅናት መቆም ካለብን አነስተኛ የሆኑ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በሚያስማሙን በሚያግባቡንና ተቀራርበን ለሃገርና ለህዝብ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተን አብሮ የመስራት ጉዳይ . . . ምርጫ የሌለው ወቅታዊ ግዴታ ነው” ብለዋል፡፡

መግለጫው እንደሚለው “እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው” የሚለውን የአበው ተረት በመጥቀስ፣ “ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአንድ በኩል ፣ዲሞክራሲ እኔ የሰጠኋችሁ ነው፣ እያለ በሌላ በኩል ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ከላይ እስከታች የራሱን መዋቅር እንደሸረሪት ድር በማስተሳሰር የሐገሪቷን የኢኮኖሚ አውታርና የመገናኛ ብዙኃን ብቸኛ ሃብቱ አድርጎ ቆይቷል.. ይላል፡፡

“ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች በወረቀት እንዲኖሩ ከመፍቀድ ውጭ ሃሳባቸውን መቀበልም ሆነ ድምፃቸውን መስማት ፈፅሞ አይፈልግም፤ ተቃዋሚዎች በሄዱበት ሁሉ ነገሮች እሾህና ጋሬጣ አድርገዋል፡፡”

መግለጫው በአገሪቱ ያለውን ሰፊ ችግር ለመፍታት የሁሉም ወገን በተለይ የገዢው ፓርቲ ቁርጠኝነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ታማኝነት በመጠየቅ በመላው ሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ቂም በቀልና ጥላቻ ተወግዶ፣ ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር እንዲሰፍን በኢትዮጵያውያን ሁሉ ብሔራዊ እርቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ዓላማ መሳካትም ኢህአዴግ ከፍተኛ ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል ብሏል፡፡ አያይዞም በሃገራችን ከመቼውም ግዜ በላይ እየተንሰራፋ የመጣው ሙስናንና ብልሹ አስተዳደርን ለማስወገድና ለማስቆም ኢህአዴግ ስር ነቀልና ቆራጥ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ በድህነት፣ በሥራ አጥነትና በኑሮ ውድነት የተመሰቃቀለ ህይወት እየመራ ያለውን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻልና ለመለወጥ ኢህአዴግ ያደረገው ከልብ የመነጨ ጥረት አለመኖሩ እጅግ የሚያሳዝን ሲሆን አሁንም ቢሆን የህዝብን እሮሮና ለቅሶ ከልብ እንዲያዳምጥ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡

መንግሥት ከተለያዩ ሃገራትና ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች የሚበደረው ገንዘብ በዚሁ ከቀጠለ አሳሳቢ ስለሆነ በሀገሪቱ ላይ ያለውን ጠቅላላ ዕዳ ለህዝብ እንዲያሳውቅና ሃገሪቱን ከተጨማሪ ዕዳ እንዲታደጋት እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከቂመኝነት፣ ከበቀለኝነትና ከአኩራፊነት ወጥተው ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ እንዲሆኑ በመግለጫው ጠይቋል፡፡

በመግለጫው ተጋብዘው ከተገኙት እንግዶች መካከል ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የግንባሩን መፈጠር ያደነቁ ቢሆንም፣ ህብረቶችና ግንባሮች እየተመሰረቱ ያለ ውጤት መፍረሳቸው አሳዝኗቸዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በኢትዮጵያ የሚመሰረቱ የተቃዋሚዎች ህብረትና ግንባሮች መፈረካከስ ዋና ምክንያት በግለሰቦች ላይ ማምለክና እምነት መጣል መሆኑን አስገንዝበው አዲሱ ግንባር በአላማና ኘሮግራሙ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ መክረዋል፡፡ በአገሪቱ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት በጋራ ተደራጅቶና ተባብሮ ከመስራት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለም አስገንዝበዋል፡፡

የብርሃን ለአንድነት ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙላት ጣሰው በበኩላቸው ለተመሰረተው አዲሱ ግንባር፣ ፓርቲያቸው ድጋፍ እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡

አቶ ሙላት አባል ድርጅቶቹ ወደዚህ ምዕራፍ መድረሳቸውን አድንቀው፣ በዲሞክራሲ ማእከላዊነት አሰራር የኢትዮጵያ እምብርት ጥያቄዎች “በኢትዮጵያዊነት ድባብ”  ውስጥ መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ “የኢፍዴኃግ አባል ድርጅቶች አንዳንዶቹ ከሰሜን ጫፍ ሌሎቹ ከደቡብ ጫፍ የመጡ መሆናቸውና አንድ የጋራ መድረክ መመስረታቸው ልዩ ያደርጋቸዋል” በማለት ድጋፍ ሰጪው ተናግረዋል፡፡

ግንባር የፈጠሩ አባል ፓርቲዎች አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ  ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት የወጡ መሆናቸው ተጠቅሶ፣ “ለምን ወጣችሁ?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ግርማይ፣ ፓርቲዎቹ ከህብረቱ የወጡት በመጨረሻ እንደሆነና ለዚህም ህብረቱ የአባል ፓርቲዎችን መብት የሚጥስና በእኩልነት የማያስተናግድ በመሆኑ ከድርጅቱ ለመውጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ “ብሔራዊ ዕርቅ” መጥራት ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሰፋ ያለ መልስ ሰጥተዋል፡፡

“በቋንቋ ተለያይተን እየተራራቅን ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየጠፋ ነው፣ አገራዊ የሆኑ ችግሮች በጋራ ተቀራርበን ለማስወገድ ብሔራዊ ዕርቅ ማድረግ ያስፈልገናል” ብለዋል ሊቀመንበሩ፡፡

ግንባሩ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ በመግለጫው ተጠርተው ሳይገኙ በመቅረታቸው ወቅሷል፡፡ እነዚህ የመንግሥት ሚዲያዎች ሁሉንም በእኩል ማገልገል የሚገባቸው ቢሆንም ኢህአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይፈጠር ካለው ፍላጎት የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴሃግ) አባል ድርጅቶች የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ዲሞክራሰያዊ ኃይሎች አንድነት፣ የኦሮሚያ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ናቸው፡፡


በየማነ ናግሽ

 
< Prev   Next >