Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ኢሕአዴግ ተቃዋሚ...
ኢሕአዴግ ተቃዋሚ... Print E-mail
Sunday, 06 April 2008

ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዴት ያለዝባል?

“እጩዎቻችንና አባሎቻችን በምረጡኝ ዘመቻው የሚኖራቸው ተልዕኮዎች አፈፃፀም እቅድ” በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ኮሚቴ መጋቢት 2ዐዐዐ ዓ.ም. ባወጣው ባለ 15 ገፅ ፅሁፍ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አስመልክቶ ያላቸው ነገሮች ከሰሞኑ የመወያያ ርዕስ ሆነዋል፡፡

 

እንደሚታወቀው በምርጫ 97 ፓርቲው አዲስ አበባን በጠቅላላ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሸንፎ ነበር፡፡ ስለዚህም የሀገሪቷን መዲና በድጋሜ በእጁ ለማስገባት ጠንካራና አሳማኝ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ከላይ በተገለፀው ፅሁፍ ላይ ግን ፓርቲው ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሰፈራቸው ነገሮች ከግልፅነት በዘለለ ግራ አጋቢ ናቸው፡፡

“በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ መወዳደር የሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራና በትብብር መስራት፤ እንዲሁም የአመጽ መንገድ በሚመርጡ አፍራሽ ኃይሎች ላይ ሕዝቡ በሚያሳድርባቸው ጫና በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ የውድድር መርህ ተገዝተው በዚህ አቅጣጫ እንዲንቀሳቀሱ፤ ህጋዊውንና ህገወጡን እየቀላቀሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝቡ ተጽዕኖ ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ ማድረግ” (ገፅ 1)

በድህረ ምርጫ 97 ህዝቡ ከፖለቲካ ተሳትፎው ወደ ኋላ እያለ በመጣበትና የሕዝቡን ስሜት ዳግም ለማነሳሳት አስቸጋሪ ከባቢ ሁኔታ በተንሰራፋበት ወቅት ላይ ኢሕአዴግ አሁንም የአመጽ መንገድ የሚመርጡ አፍራሽ ኃይሎች እንዳሉና ህጋዊውንና ህገ ወጡን እየቀላቀሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉ እየነገረን ነው፡፡ ፓርቲው ገዥ ፓርቲ በመሆኑ በመንግሥት አቅም ያገኛቸው መረጃዎች ይህን ሊጠቁሙት ቢችሉም በዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ፅሁፍ መፍትሔውን ለመራጩ ሕዝብ ትቶታል፡፡ ኢሕአዴግ አቅሙ ጎልብቶ አባላቱን በብዙ እጥፍ አብዝቶ ባለበት በአሁኑ ወቅት አባላቸው የተመናመነባቸውንና አቅማቸው የደከመባቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣ለተሳትፎ ያህል፣ በሚካፈሉበት ምርጫ ዋዜማ አፍራሽ ኃይልና ህገ ወጥ ናቸው ማለቱ ግራ ያጋባል፡፡

“. . . የምርጫ ስነ ምግባር ተከትለን በምናካሂደው የተግባር እንቅስቃሴ በሰላማዊና በህጋዊ አግባብ ከሚንቀሳቀሱ ተወዳዳሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ እንደምንሰራ አስቀምጠናል፡፡ ከነዚህ ኃይሎች ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ እንሰራለን ስንል ሃሳቦቻችንን እናስታርቃለን ማለታችን አይደለም፡፡ ልዩነቶቻችንን ይዘን ሃሳቦቻችንን በህጋዊና በሰላማዊ አግባብ መራጮች እንዲያውቋቸው እንንቀሳቀሳለን፣ ተቻችለንና ተከባብረን ህግና ስርአትን ጠብቀን እየተደጋገፍን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ህጋዊና ህገ-ወጡን መንገድ በማጣቀስ የሚንቀሳቀሱትን ኃይሎች ለይተን ህገ-ወጥ አካሄዳቸው ህዝቡን እንደሚጐዳ እያጋለጥን እንደጉዳዩ ክብደትም በህግ መሠረት እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየታገልን እንንቀሳቀሳለን ማለታችን ነው፡፡

ይህንን ማድረግ የምንችለው ግን እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎቻችን በምንንቀሳቀስበት አካባቢ የትኛው ፓርቲ ምን እያደረገ እንደሆነ በአግባቡ የምናውቅ ከሆነ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በቀበሌ ደረጃ እጩዎች አቅርበው እየተወዳደሩ ባይሆኑም ተቃዋሚ ነን የሚሉት ፓርቲዎች በህዝቡ ውስጥ ግን እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም እጩዎቻችን፣ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን የየትኞቹ ፓርቲዎች አባላት በምን ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አጥርተን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ . . .” (ገጽ 12 እና 13)

ከላይ በመጀመሪያው አንቀጽ በተቀመጠው መሠረት ኢህአዴግ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ልዩነቱን እንደያዘ በጋራ አጀንዳዎች ላይ አብሮ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ ሕገ-ወጦችንም ለማጋለጥና እርምጃ እንዲወስድባቸው ለማድረግ የሚያደርገው ትግልም እንደዚያው ነው፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ ተወዳዳሪ ፓርቲም መንግሥትም ነው፡፡ ስለዚህ እርምጃ ሲያስወስድም ሆነ ጥቆማ ሲያቀርብ አስፈፃሚ አካላትና ሕግ ተርጓሚው የኢህአዴግን ማስረጃዎችና ክሶች በጥርጣሬ ማየትና በጥንቃቄ ሊመዝኑ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሕገ-ወጥ እና አፍራሽ ኃይሎች የሚላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ተፅእኖ የመፍጠር አቅማቸው ከኢሕአዴግ ጋር ሲነፃፀር ደካማ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ላይ ፖለቲከኞች ክስ ሲያሰሙ ከጀርባ ሴራ የማቀናበርና ሂሳብና ስሌት ውስጥ እራሳቸውን ስለሚከቱ ..ህገ-ወጥ.. የሚለው ቃል ለሕጉና ለፖለቲከኛው የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጠው ማሰቡም ጠቃሚ ነው፡፡

በሁለተኛው አንቀፅ ላይ ደግሞ ኢሕአዴግ እጩዎቹ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ተግባሮችን እንዲከታተሉ ይጠይቃል፡፡ እንደውም ይህን ካላወቁ የፓርቲው ተልዕኮ በተሟላ ሁኔታ መፈፀም እንደማይቻል ይገልፃል፡፡ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየትኛውም ዓለም በፊት ለፊትና ከመጋረጃ ጀርባ በፖለቲካዊ ቀመር መክበብ ውስጥ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ፓርቲዎቹ ፊት ለፊት ከሚታየው ሰው፣ ክስተትና ሃሳብ ጀርባ የማይታዩ አንቀሳቃሽ ነገሮች አሏቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምሳሌ ራሱ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ሕዝቡ ስለኢሕአዴግ ከሚያውቀው የማያውቀው ይበልጣል፡፡ ታዲያ አባላቱ የሌሎች ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በመከታተል ስለላ ውስጥ እንዲገቡ ለምን ያዛል? በዚህ መልኩስ ያገኛቸው መረጃዎች ..ሕገ-ወጦችን.. ለማጋለጥ እንዴት ነው የሚውሉት? ከዚያ ይልቅ ራሱን በመግለፅና በማዳበሩ ላይ ቢያሳትፋቸው አይሻልምን?

በመጨረሻም ፓርቲው ባደረገው የቤት ለቤት ቅስቀሳ ያገኛቸውን ሰዎች በአስተሳሰብ ደረጃ በአራት ይከፍላል፡፡

“አራተኛዎቹ ከሞላ ጎደል የማይደግፉን ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ስንቀርባቸው ለምን በየቤቱ እየመጣችሁ ትቀሰቅሳላችሁ? የምትናገሩትን በሬዲዮ ሰምተናል፣ በቴሌቪዥን አይተናል፤ ከዚህ በላይ መስማት አንፈልግም፤ አሁንም ልታጭበረብሩ ነው ወይ? . . . ወዘተ በማለት በአጥቂ መንገድ የሚቀርቡንና የሚተናኮሉን ሰዎች ናቸው፡፡” (ገፅ 13)

ስለነዚህ ሰዎች ፓርቲው ሲያብራራ “. . . ሳያውቁ ተሳስተው ወይም በተለየ ምክንያት በትንሽ በነገር ተቀይመው የራቁንን ሰዎች ለማቅረብ ከምንሰራው ሥራ ውጪ እነርሱ ላይ ልናተኩር አይገባም፡፡ ለውጠን ላንለውጣቸው እነርሱ ላይ ጊዜያችንን በማባከን በሌሎች ላይ ለምንሰራው ሥራ ጊዜያችንን ማጣበብ የለብንም” ብሏል፡፡

በእርግጥም ምርጫውን በሚያጠራጥር መልኩ ያሳወቀን ሰው ሌላ ምርጫ ሊጭኑበት መሞከር ኢዴሞክራሰያዊ አሰራር ነው፡፡ ወይም ደግሞ እንዴ ኢሕአዴግ ገለፃ ‘ጊዜ ማባከን' አይኖርበትም፡፡ ኢሕአዴግ ሁሉን ደጋፊውና ተከታዩ አድርጎ ከመቁጠር ስሜት ወጥቶ ስለነዚህ ሰዎች ተቃውሞ በግልፅ ማስቀመጡ ሊበረታታ ይገባል፡፡

ከሁሉም በላይ የሚገርመው የፅሁፉ ክፍል ግን ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ይላል፡፡ “ሆኖም ግን እነዚህ ሰዎች ተለይተው መታወቅ አለባቸው፡፡ እኛን መምረጥ ካልፈለጉ ምርጫቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች እኛን እንዳይመርጡ ሆን ብለው በመንቀሳቀስ ስራችንን ሊያደናቅፉ እንደማይገባ በእርጋታ ልንገልፅላቸውና ልናለዝባቸው ይገባል”

መራጭ ማለት የምርጫ ካርድ ያወጣ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ተመራጮቹ ደግሞ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች፡፡ ታዲያ ተቃዋሚዎች “ኢሕአዴግን አትምረጡ!” በማለት ሆን ብለው መንቀሳቀስ ሥራቸው አይደለም እንዴ? ኢሕአዴግስ እኔን ምረጡ ሲል ተቃዋዎችን መራጩ እንዳይመርጥ ሆን ብሎ እየተንቀሳቀሰ አይደለም እንዴ? ከዚህ ተግባራቸውስ “የሚያለዝባቸው በምን መንገድ ነው? በውይይትና በክርክር ብሎም በመተማመን ወይስ በኃይል እርምጃ?

ኢሕአዴግ ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች አግባብ ያለው መልስ ሊሰጠን ይገባል፡፡


በሠለሞን ጐሹ

 
< Prev   Next >