Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow የአስተዳደሩ ሊዝ ጽ/ቤት...
የአስተዳደሩ ሊዝ ጽ/ቤት... Print E-mail
Sunday, 06 April 2008
የአስተዳደሩ ሊዝ ጽ/ቤትየሸጠው ቦታ ለባለሀብቱ ሳያስረክብ አሥር ዓመት ሞላው

የአዲስ አበባ ከተማ ሊዝ ጽህፈት ቤት ከአሥር ዓመት በፊት በቀድሞው ወረዳ 2ዐ ቀበሌ 23 (ንፋስ ስልክ ላፍቶ ቀበሌ 09/14) ክልል ውስጥ የሚገኘውን 770 ሜትር ካሬ ቦታ አቶ አዋሽ ዘጐ ለሚባሉ ባለሀብት በሊዝ የሸጠ ቢሆንም ቦታውን እስካሁን እንዳልተረከቡ ባለሀብቱ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ ቦታውን መረከብ እንደሚገባቸው ብናውቅም፣ ውስብስብ ጉዳይ ስለገጠመን ልናስረክባቸው አልቻልንም ሲል ክፍለ ከተማው ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ባለሀብቱ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09/14 ከጐፋ መብራት ኃይል ፊት ለፊት የሚገኘውን ቦታ (ቀደም ባለው ጊዜ ራሳቸው ይጠቀሙበት የነበረ) ለአፓርትመንትና ሱቅ አገልግሎት የሚውል ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ለመገንባት ኘሮጀክት አቅርበው ይፈቀድላቸዋል፡፡

በተፈቀደላቸው 77ዐ ሜትር ካሬ ቦታ፣ በሜትር ካሬ 600.00 ብር ቅድሚያ ክፍያ 50 በመቶ ከፍለው፣ ቀሪውን ክፍያ ወለዱን ጨምሮ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቁ የሊዝ ጽህፈት ቤት በቁጥር አመ/አከ7/ዘ2/7/1ዐ9 ማያዚያ 5 ቀን 199ዐ በተፃፈ ደብዳቤ ወስኖላቸዋል፡፡

ባለሀብቱ አቶ አዋሽ ዘጐ ሊዝ ጽህፈት ቤቱ በወሰነላቸው መሠረት ቅድሚያ ክፍያ 1ዐዐ ሺ ብር ለአስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ በደረሰኝ ቁጥር 422225 መክፈላቸውን ይናገራሉ፡፡

ተገቢውን የሊዝ ክፍያ መክፈላቸውን፣ ነገር ግን ክፍለ ከተማው ቦታውን ለሌሎች ሁለት ግለሰቦች ሰጥተውት ስለነበር በወቅቱ ሊያስረክቧቸው እንዳልቻሉ የሚናገሩት አቶ አዋሽ፣ አንደኛው ግለሰብ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ተደርጐ ለሁለተኛው ግለሰብ እንዴት ቦታው እንደተሰጣቸውና መቼ እንደተሰጣቸው ለቀበሌ 09/14 ቀርበው እንዲያስረዱ ቢጠየቁም ባለመቅረባቸው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ጥር 27 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በፃፈው ደብዳቤ ካርታው እንዲመክን መደረጉን ገልፀዋል፡፡

“ከነገ ዛሬ ቦታውን እረከባለሁ ስል መሰናክሎች በመፈጠራቸው አሥር ዓመት ሙሉ ልሰራበት የምችልበት ጊዜና ገንዘቤ ላይ ጉዳት ደርሶብኛል” የሚሉት አቶ አዋሽ፣ የጉዳዩ ተጠቂ በቀጥታ እሳቸው ቢሆኑም በተዘዋዋሪ በመንግሥት የልማት ፖሊሲ ላይ ኢንቨስተሮች እምነት እንዳይኖራቸው እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቱ ላለፉት አሥር ዓመታት ለመሬት ልማትና አስተዳደር ባለሥልጣን ለሊዝ አስተዳደር መምሪያ፣ ለክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ ለሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ለእንባ ጠባቂ ተቋም ለሥራና ከተማ ልማት ቢሮ፣ ፍትሕ ፍለጋ በደብዳቤና በአካል በመሄድ ቢጠይቁም፣ ላለፉት አሥር ዓመታት ምንም ምላሽ አለማግኘታቸውንና መንግሥት ይኸንን ጉዳይ ተከታትሎ ፍትህ ያስገኝልናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

“አቶ አዋሽ ዘጐ በዚህ መሬት ጉዳይ ዘጠኝ ዓመት እንዳለፋቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቦታውን መረከብ እንደሚገባቸው ብናውቅም፣ ውስብስብ ጉዳይ ስለገጠመን ልናስረክባቸው አልቻልንም” ያሉት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብዱል ዋሂድ መሐመድ ናቸው፡፡

አቶ አብዱልዋሂድ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ገልፀው፣ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚያገኝና ቦታውን ለአቶ አዋሽ እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡

“ጥፋቱ በመጨረሻ እጃችን ላይ ያረፈው በረፈደ ሰዓት ላይ ነው” ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፣ እሳቱን (የእኔ ነው የእኔ ነው ውዝግቡን) አብርደው ጉዳዩን የሚያዩበት መንገድ እየፈለጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ባለሀብቱ ምንም ይሁን ምንም በሊዝ ጽህፈት ቤቱ የተፈቀደላቸውን ቦታ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርጉ፣ ካልሆነም ተለዋጭ ቦታ ማግኘት አለባቸው የሚል አቋም መያዙን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

በታምሩ ጽጌ
 
< Prev   Next >