| “የምርጫው ፍትሐዊነት ካልተስተካከለ... |
|
|
| Sunday, 06 April 2008 | |
|
“የምርጫው ፍትሐዊነት ካልተስተካከለ አንሳተፍም”
ኢዴኃኅ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት በሚያዚያ ወር በሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ለመሳተፍ የመጨረሻ ያለውን የምርጫ ፍትሃዊነት ጥያቄ በማቅረብ ጥያቄው በፍጥነት የማይመለስ ከሆነ በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚቸገር አስታወቀ፡፡ ኅብረቱ ከትላንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በሚያዚያ ወር የሚካሄደው ምርጫ በርካታ ጉድለቶች ያሉበት መሆኑን በመጥቀስ የምርጫው ቀን እንዲራዘምና የእርምት እርምጃዎች በአፋጣኝ እንዲወስዱ ሲል ጠይቋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ኅብረቱ ምርጫው ትርጉም አልባ ስለሚሆንበት ለመሳተፍ እንደሚቸገር ገልጿል፡፡ ፓርቲው በሰጠው መግለጫ በምርጫው አስፈፃሚነት የተመደቡ አባላት የገዢው ፓርቲ አባሎች፣ የአስተዳደር አካላትና ባለፉት ምርጫዎች ወንጀል ፈጽመው ከአስፈፃሚነት የታገዱ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ከዚህ አንፃር ነፃና ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚዎች በአስቸኳይ እንዲተኩ ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም 20ሺህ የፓርቲው እጩዎች ያለመመዝገባቸውን በመጥቀስ የእጩዎች የምዝገባ ስርዓት ችግር እንደነበረበት አስታውቋል፡፡ ኅብረቱ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደት ሆን ተብሎ የፓርቲውን የምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ወደ 12 ዝቅ እንዲደረግ ተደርጎ ዝቅተኛ የቅስቀሳ የአየር ሰዓት ተሰጥቷል የሚል ቅሬታ አቅርቧል፡፡ በዚህም ለገዢው ፓርቲ ከ14 ሰዓት በላይ የቅስቀሳ የአየር ሰዓት መስጠቱን ለኅብረቱ ግን አንድ ሰዓት ብቻ መስጠቱን በመጥቀስ ኢፍትሃዊ የቅስቀሳ የአየር ሰዓት ክፍፍል መኖሩን ጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም የፓርቲው ተወዳዳሪ እጩዎች፣ የፓርላማ አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች ላይ ወከባና እንግልት መኖሩን ፓርቲው አሳውቋል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የፓርቲውን ቅሬታ በተመለከተ ባለ አስራ ዘጠኝ ገጽ የቅሬታ ሰነድ ለምርጫ ቦርድ ቢያቀርቡም ተገቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ “በእንደዚህ አይነት ሁኔታ በምርጫው ውስጥ በአጃቢነት አንቆይም” ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር በየነ “ፓርቲያችን ከምርጫ ቦርድ ጋር ትግልና ውድድር እያደረገ ነው” ሲሉ የምርጫ ቦርድን አሰራር አማርረዋል፡፡ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና “በትንሹ 350 አባላቶቻችን ከምርጫ ጋር በተያያዘ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ጥይት ተተኩሶባቸዋል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም የምርጫ ሂደቱ በአጠቃላይ “የህፃን ጨዋታ ሆኗል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |