| ከአዋጅ ውጪ የተወሰረሱ ንብረቶችን... |
|
|
| Sunday, 06 April 2008 | |
|
ከአዋጅ ውጪ የተወሰረሱ ንብረቶችን የማስመለስ አቤቱታ የሦስት ወራት ቀነ ገደብ ብቻ ተሰጠው
- ፍትህ ሚኒስቴር ፍርድ ቤቶችን ከስሷል ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ንብረቶችን ለማስመለስ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ከሦስት ወር በኋላ ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ በቅን ልቦና ከአጭበርባሪዎች ቤት የገዙ ዋስትና የላቸውም፡፡ ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ንብረቶችን በማስመለስ ሂደት አንዳንድ ፍርድ ቤቶች ጣልቃ በመግባታቸው ፍትህ ሚኒስቴር ክስ መስርቶባቸዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 25 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ንብረቶችን ለማስመለስ የተዘጋጀውን አዋጅ ባፀደቀበት ወቅት እንደተገለፀው ከሦስት ወራት ጊዜ በኋላ የተወረሱ ቤቶችን ጉዳይ ይዘው የሚቀርቡ አቤቱታ አቅራቢዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ በቅን ልቦና ከአጭበርባሪዎች ቤት የገዙ ግለሰቦችም ቤቱን ለኘራይቬታይዜሽንና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ እንዲያስረክቡ ይደረጋል፡፡ ከንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው መግለጫ እንደሚያመለክተው አዋጁ ከዚህ በፊት የተሰጡትን ሁሉንም ውሳኔዎች የሚሽር ሳይሆን በተሳሳተ ማስረጃና በተጭበረበረ መንገድ ወደሌላ ወገን የተመለሱትን ንብረቶች የሚስተናገዱበትን ስርዓት የሚፈጥር ነው፡፡ ከአጭበርባሪዎች በቅን ልቦና ቤት ለገዙ ግለሰቦች የታሰበ ነገር ስለመኖሩ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበላቸው የኮሚቴው ሰብሳቢ የኢትዮጵያ ንብረት ህግ ቅን ልቦናን የሚመለከተው ተንቀሳቃሽ ለሆኑ ንብረቶች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አንድ ግለሰብ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ሲገዛ ወደ ኋላ ተመልሶ ማየት እንደሚችል የጠቆሙት ሰብሳቢው በቅን ልቦና የተጭበረበረ ቤት የገዛ ሰው ምንም ዓይነት አስተያየት እንደማይደረግለት አመልክተዋል፡፡ ንብረቱን የሸጠለትን ግለሰብ ግን ተከታትሎ መድህን መጠየቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ቤቶችን የማስመለስ ስልጣን ያለው የኘራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ መሆኑን የገለፁት የኮሚቴው ሰብሳቢ ኤጀንሲው የሚመለከተውን ጉዳይ ከህግ አግባብ ውጭ ሲመለከቱ በነበሩ ፍርድ ቤቶች ላይ ፍትህ ሚኒስቴር ክስ መክፈቱን አስታውቀዋል፡፡ የአዋጁን መፅደቅ የተቃወሙት አቶ ተመስገን ዘውዴ ኤጀንሲው የፍርድ ቤትን ሥልጣን ወስዷል ሲሉ ኮንነዋል፡፡ ኤጀንሲው ከሳሽና ፍርድ ሰጭ ሆኖ መስራቱም ህገ መንግሥቱን የሚፃረር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አቶ ተመስገን እንደሚሉት ለአንድ የመንግሥት ተቋም ይህንን ያህል ስልጣን መስጠት ከህግ አግባብ ውጭ ነው፡፡ ጉዳዩን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የፓርላማ አባል በበኩላቸው አንድ አዋጅ ተግባራዊ የሚሆነው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ገልፀው ኤጀንሲው ወደ ኋላ 13 ዓመት ተመልሶ የሚያይበት ሁኔታ መኖር እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ለምክር ቤት በቀረበበት ሰዓት ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡት ጥያቄዎችም ለአስረጅዎች አልተንፀባረቀም ሲሉ ተችተዋል፡፡ የህብረቱ ሻለቃ መኮንን በበኩላቸው አዋጁ እንዲፀድቅ ተብሎ ከኤጀንሲው የቀረቡ ችግሮች በሙሉ የመሥሪያ ቤቱ ችግሮች እንጂ የህግ ችግሮች አለመሆናቸውን በመግለፅ የአዋጁን መፅደቅ ተቃውመዋል፡፡ አስረጂዎቹም ከምክር ቤቱ የቀረበላቸውን ጥያቄዎች መመለስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የቅንጅቱ አቶ ለገሰ ቢራቱ ደግሞ አዋጁ የማህበራዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ ሊፀድቅ እንደማይገባ ገልፀዋል፡፡ ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ቤቶችን የሚመለከተው ጉዳይ በታየበት ወቅትም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራና የከተማ ልማት ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ኤጀንሲና ሌሎችም መሳተፍ ይገባቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ የሰጠት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ከበደ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን የሚመነጨው ከአዋጅ መሆኑን ጠቅሰው የቀድሞ የኘራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በአዋጅ 110/87 ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ቤቶችን ጉዳይ እንዲያጣራ ስልጣን የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩም በፍርድ ቤቶች እንደማይታይ አመልክተዋል፡፡ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ይግባኝ የሚታየው በቦርድ መሆኑን የጠቆሙት ሰብሳቢው ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ቤቶች ጉዳይ አጭበርባሪዎችን ብቻ የሚጎዳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የአዋጁ ዋና አላማ መንግሥት ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ንብረቶችን ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቋጭቶ ወደ ሌላ የልማት ሥራ መግባት አስፈላጊ በመሆኑ እና የተጭበረበሩ ቤቶችን ለባለቤቶች በመመለስ ዜጐች በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |