|
Sunday, 06 April 2008 |
|
የፀረ ሙስና እርምጃ በበሬ ሳይሆን በእንቁላል ደረጃ ይጀመር
በብሔራዊ ባንክ ስለተካሄደው የወርቅ ማጭበርበር ወንጀል በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየሆቴሎች፣ በየታክሲዎች፣ በየትምህርት ቤቶች (በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች በሚገኙ ሕፃናት ሳይቀር) የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በከተማችን የሚታተሙ ጋዜጦች በተለይም የግል ጋዜጦች ለተከታታይ ሳምንታት በዜናና በርዕሰ አንቀጾቻቸው ቀዳሚ ርዕስ አድርገውታል፡፡ የሥነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ችግሮች ሳይጠናከሩ በእንጭጩ ለማስቆም አልቻለም፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አሰጣጥ ላይ ተፈጸመ የተባለ ሕገወጥ አሰራር አለ፡፡ ድርጊቱ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ለሁለት ዓመታትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ሕዝቡ ምሬቱን ሲገልጽበትና በገሃድ ዝርፊያ ሲፈጸምበት የቆየ ነው፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይህንን የሕዝብ ሮሮ ሲሰማ የግድ በማስረጃ የተደገፈ ጥቆማ እስኪደርሰው ሳይጠብቅ ማጣራት ነበረበት፡፡ ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ የተንቀሳቀሰው ለልማት ቢውል ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችል በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት ከተመዘበረና ጥቂቶች ከከበሩበት በኋላ ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ጉዳይም ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡
ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ እስካሁን ሰሚ ያጣው፣ የብዙ አቅራቢዎች ምሬት የሚሰማበትና አንዳንዶቹም በዚህ መ/ቤት ጨረታ ላይ መሳተፍ ትርፉ የተያዘውን የጨረታ ማስከበሪያ ገንዘብ ለማስመለስ ለወራት መጉላላት ነው በማለት ዳግም ላለመጫረት የወሰኑበት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት የአሰራር ብልሹነትና የሙስና ተግባር ነው፡፡
በዚህ መሥሪያ ቤት የሚወጡ ጨረታዎችን በሕጉና በደንቡ መሰረት ተወዳድሮ ማሸነፍ ሕልም ነው፡፡ አንዳንድ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ቀድመው በምስጢር ያዘጋጇቸው አቅራቢዎች ካላሸነፉ የጨረታው ውጤት እንዲጓተት ተደርጎ ሕጋዊው አሸናፊ ተጫራች በመበሳጨት እንዲተው ይደረጋል ወይም ጨረታው በቂ ባልሆነ ምክንያት ይሰረዛል፡፡ ለዚህም መንግሥት በቤቶች ልማት ላይ የያዘውን የልማት አቅጣጫ በሽፋንነት ይጠቀማሉ፡፡ ልማቱ እንዳይቆም በማሰብ በእነርሱ ላይ እርምጃ እንደማይወሰድ አድርገው ይገምታሉ፡፡
ስለሚፈጸመው ኢ-ፍትሃዊ የጨረታ አካሄድ አቤቱታ ሲቀርብላቸው በበላይ አካል የተሰጠ አመራር ለማስመሰል መሞከር የተለመደ ተግባራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ ያለአግባብ ይባክናል፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሁሉ አግባብ የሌለው ወጪ ቤቱን በሚረከበው በድሃው የቤት ዋጋ ላይ የሚጨመር መሆኑን ነው፡፡ ሥራው የሚካሄደው በፕሮጀክት በመሆኑና ፕሮጀክቱንም በታለመለት ጊዜ መጠናቀቅ ሲገባው፣ በመንግሥት ሕግና ደንብ መሠረት መሥራት እንደማይጠበቅባቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ሰሞኑ ደግሞ ከመ/ቤቱ የውስጥ አዋቂዎች እንደምንሰማው ከሆነ እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ የተቃኘ የተለየ የግዢ መመሪያ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያሉ መሆኑን ነው፡፡ በሌላ በኩል ፕሮጀክቱ እንኳን በታለመለት ጊዜና በአነስተኛ ወጪ ሊጠናቀቅ ቀርቶ በአንድ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው ሥራ በሁለትና በሶስት ዓመት ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በ1997 በአንድ ዓመት ይጠናቀቃሉ የተባሉ ቤቶች እስካሁን ተጠናቅቀው ለተጠቃሚው አለመተላለፋቸው ሲሆን ለመጓተቱ እንደ ምክንያትነት የሚቀርበውም ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ተከስቶ የነበረው የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትና በወቅቱ ከተማዋን በባለቤትነት ተረክቦ የሚያስተዳድር አካል ስላልነበረ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት ነው፡፡ ይህ ችግር ከተቃለለ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ ሥራውን ጀምሮ ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ይፈጃል የተባለለት ሥራ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ከበቂ በላይ ነው፡፡
በ1999 ዓ.ም ተጀምረው በዚያው የበጀት ዓመት ይጠናቀቃሉ የተባሉት የ33"000 ቤቶች ግንባታም በዚያው የበጀት ዓመት ሊጠናቀቁ ቀርቶ በያዝነው የበጀት ዓመት የካቲት ወር ድረስ እንኳ የተከናወነው ከጠቅላላው ሥራ 40 በመቶ አይሞላም፡፡ በ2000 የበጀት ዓመት እንዲሁ ከ38"000 ቤቶች በላይ በበጀት ዓመቱ ሰርቶ ለማጠናቀቅ የተያዘው እቅድም ምኑም ሳይያዝ ዓመቱ ሊጠናቀቅ ከሶስት ወር ያልበለጠ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ በ2001 የበጀት ዓመት ሐምሌ ወር መጀመር ያለባቸው ከ40"000 በላይ የቤቶች ግንባታ በእቅድ የተያዘ ቢሆንም መሬትና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች እስካሁን አልተዘጋጁም፡፡
በአንድ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለ አንድን የመጀመሪያ ፕሮጀክት በአራት አመት (አንድ ዓመት በወቅቱ ለተፈጠረው ችግር ብንቀንስ ሶስት ዓመት) መጨረስ ያልቻለ አራት ተደራራቢ ፕሮጀክቶችን (በድምሩ ከ120"000 ቤቶች በላይ) በጥቂት ወራት ያጠናቅቃል ማለት የማይታለም ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የአሰራር ድክመት የሚያሳየን ማኔጅመንቱ ምን ያህል ሥራውን በብቃት ለማካሄድ እንዳልቻለ ነው፡፡ ይልቁንም ትኩረት ያደረገው የድሃውን ችግር ለመፍታት የተመደበውን ሀብት የጥቂት ኃላፊዎችን ኪስ በማደለብ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ፀረሙስና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ጥፋት ደርሶ ሕዝብ ጉድ እስከሚልና እንደሰሞኑ የተወካዮች ምክር ቤት የመነጋገሪያ አጀንዳ እስከሚሆን ሳይጠብቅ ከወዲሁ በእንጭጩ ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡
የፕሮጀክቱ ሠራተኞችም እያዩ ከንፈር ከመምጠጥ ባሻገር ለኮሚሽኑ ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም በሥነ ምግባራቸውም ሆነ በታታሪ ሠራተኝነታቸው በአብዛኛው ሠራተኞች ዘንድ የሚታወቁ ሆነው ነገር ግን በጽ/ቤቱ ለሚካሄዱ የሙስና ተግባራት ተባባሪ ባለመሆናቸው ብቻ በአስተዳደሩ ከቦታቸው እስከመነሳት የሚደርስ ተደራራቢ በደል ደርሶባቸው ጉዳዩን ለእግዚአብሔር ሰጥቻለሁ ሲሉ የሚደመጡ ሠራተኞች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ራሳቸውንም ሆነ አገርን እየበደሉ ስለሆነ ከሌላው በተሻለ በሥራቸው ቅርበት የሚያውቋቸውን የሙስና ምስጢሮች ለሚመለከተው አካል የማጋለጥ የሕግ የሞራልና የዜግነት ግዴታ አለባቸው፡፡
መንግሥትም አብዛኛውን የከተማ ድሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የቀየሰው የቤቶች ልማት ፖሊሲ በታለመለት ጊዜ፣ ወጪና ጥራት ይከናወን ዘንድ የማኔጅመንቱን ብቃት በመፈተሽ ከወዲሁ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡
"እናቴ በእንቁላሉ ብትቀጣኝ ኖሮ ወደ በሬ ስርቆት አልሄድም ነበር" እንዳለው ሰው ከመሆኑ በፊት፣ ፀረሙስና ኮሚሽንም በበሬው ሳይሆን በእንቁላሉ እርምጃ የመውሰድ ባህል ያዳብር፡፡ ሰማኸኝ ማሞ፣ ከአዲስ አበባ |