Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow ብሔራዊ ባንክ ለሠራተኛው...
ብሔራዊ ባንክ ለሠራተኛው... Print E-mail
Sunday, 06 April 2008
ብሔራዊ ባንክ ለሠራተኛው ያደረገው የደመወዝ ማስተካከያ ቅሬታ አስነሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሠራተኛው ያደረገው ጊዜያዊ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ቅሬታ መፍጠሩን አንዳንድ ሠራተኞች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ ቅሬታቸው "ጭማሪው ከሌሎቹ የመንግሥት ፋይናንስ ተቋማት ያነሰ ነው" የሚል ሲሆን ባንኩ ጉዳዩን እያየው መሆኑን ገልጿል፡፡

ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን የገለፁት ለሁለት በመከፈል፣ ነባርና አዲስ ተቀጣሪዎች በሚል ነው፡፡ አንዳንድ የብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች እንደገለፁት የደመወዝ ስኬል ማስተካከያው በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት እኩል መተግበር ቢኖርበትም ለብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች ግን በፐርሰንትና ጭማሪው የሚጀምርበት ወር አድልኦ መፈጠሩ ቅር አሰኝቷቸዋል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች የተደረገው ጭማሪ እ.ኤ.አ ከዲሴምበር 2007 ጀምሮ ከ25 በመቶ እስከ 36 በመቶ መሆኑን የገለፁት ሠራተኞቹ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 2007 ጀምሮ እስከ 50 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“ምክንያቱ ለሠራተኛው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ለምን ወራቱም ሆነ ፐርሰንቱ እንደተለያየ አልገባንም” ያሉት ሠራተኞቹ መንግሥት በአንድ ዓይን የሚያያቸውን የፋይናንስ ተቋማት በደመወዝ ጭማሪው ለምን ሊለያያቸው እንደፈለገ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል፡፡

አዲስ የተቀጠሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች በበኩላቸው፣ “አዲስ ተቀጣሪዎች በመነሻው ስኬል ይቀመጡ” የሚለውን ወደ ጎን በመተው 19 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ በማድረግ የተስተካከለ ማስመሰሉ ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል፡፡

መንግሥት ስኬሉን ከ25 እስከ 36 በመቶ አስቀምጦ እያለ ለምን 19 ነጥብ 9 በመቶ ለእኛ ተሰራ? በማለት ጥያቄያቸውን ለማኔጅመንቱ አቅርበው መልስ አየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባንኩ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አቤንኤዘር በወንጌል፣ የደመወዝ ማስተካከያው በሜኔጅመንት ወይም በማኅበሩ ትግል ሳይሆን በመንግሥት በጎ ፈቃድ የተደረገ በመሆኑ “መንግስትን እናመሰግናለን” በማለት በተፈጠረው የጭማሪ ልዩነት ግን ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡


..ቅሬታቸው ጭማሪው ከሌሎች የመንግሥት ፋይናንስ ተቋማት ያነሰ ነው.. የሚል በመሆኑ ማኔጅመንቱ እያየው መሆኑን የገለፁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰው ኃይልና አስተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ጥሩነህ ሚጠፋ ናቸው፡፡

በተቋማቱ ውስጥ ልዩነት እንዳለ የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ ከብሔራዊ ባንክ ውጭ ያሉትን የፋይናንስ ተቋማት ስኬል በማጥናት ለመንግሥት የሚያቀርበው ኤጀንሲው ሲሆን፣ የብሔራዊ ባንክን ስኬል የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አጥንቶ ለመንግሥት በማቅረብ እንደሚያፀድቅ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት እንደ ስኬል አጠናኑ ጭማሪውም እንደሚለያይ የገለፁት ዳይሬክተሩ ኤጀንሲው ቀደም ብሎ ባቀረበው ጥናት መሠረት የወሩና የፐርሰንቱ ልዩነት ሊኖረው መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በተለይ የጭማሪው ፐርሰንት ሊለያይ የቻለው የመቅጠሪያ ደመወዝ ስለሚለያይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጥሩነህ፣ የብሔራዊ ባንክ የመነሻ ደመወዝ ከፍተኛ በመሆኑ ጭማሪው ከሌሎቹ ሊያንስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

አዲስ የተቀጠሩ ያቀረቡት ቅሬታ መነሻ ደመወዛችን ከሌሎቹ ለምን የተለየ ሆነ? በሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ ማኔጅመንቱ እያየው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የመንግሥት ፋይናንስ ተቋማት በመባል የሚታወቁት ብሔራዊ ባንክ፣ ንግድ ባንክ፣ ቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ፣ ልማት ባንክ እና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በቅርቡ መንግሥት የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ ወስኖ ተግባራዊ መሆን መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

በታምሩ ጽጌ

 
< Prev   Next >