|
Sunday, 06 April 2008 |
|
ስለ ኢኮኖሚው ጤንነት ባለሙያዎች ቢናገሩ በኅሊና ቢ.
የተለያዩ ሪፖርቶች በተለያዩ ጊዜያት ይቀርባሉ፡፡ ሪፖርቶቹ ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ሁሉ ተቀባይነትም ሊያጡ ይችላሉ፡፡ በተለይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕዝብ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ የሪፖርቶቹ ይዘት ስህተት ወይም አጠራጣሪ ከሆነ አፍራሽነቱ ወሰን አይኖረውምና፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መጋቢት 9 ቀን 2000 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ስብሰባ በኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በቀረበው ሪፖርት ላይ በመደገፍና በመቃወም ከሁለት ወገኖች አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ክርክሮች ተካሂደዋል፡፡ የአንዳንዶች አስተያየት እውነታው ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን በፓርቲ አባልነት ብቻ የመደገፍና የመንቀፍ አባዜ ተፀናውቶታል፡፡ ደጋፊዎችም የተባለው ሁሉ ትክክል ነው ብለው ማጨብጨብ ሳይሆን የተሳሳተውን ማረም ይኖርባቸዋል፡፡ ተቃዋሚዎችም መሠረት የሌለውና ከእውነታ የራቀ ተቃውሞ ማቅረብ የለባቸውም፡፡
በኢኮኖሚው እንቅስቃሴያችን ላይ ጉድለቶች እንዳሉ ራሱ የኢኮኖሚው ውጤት ያስረዳል፡፡ አንፃራዊ ሰላም በሰፈነበር አገር የኑሮ ውድነቱ ዕለት በዕለት እንዲህ ሊያሻቅብ ይችላል? ጤነኛ ኢኮኖሚ ነው የሚለው በስፋት ያነጋግራል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይ ከተሜው የኑሮ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ፈተና ሲባል ከተሜውን ብቻ ሣይሆን ገጠሩንም ያካትታል፡፡ ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቶ መለስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ መለስ በምላሻቸው "የገጠሩ ኅብረተሰብ በአጠቃላይ ረበኢኮኖሚ እድገቱሪ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ 85 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ፍትሃዊ እድገት የትም የለም፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ፍትሃዊ የሆነ እድገት 85 በመቶ የኅብረተሰብ ክፍሉን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ዋነኛ ተጠቃሚ ያደረገ የእድገት አቅጣጫ የትም የለም. . ". ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነቱ ተጽዕኖ ያሳረፈበት የገጠሩም ይሁን የከተማው ሕዝብ ብዙ እንዳልሆነ ነው የጠቆሙት ወይም ያረጋገጡት፡፡ ይህ ማረጋገጫ በእርሳቸው በኩል ያለውን ነው፡፡ ጉዳዩ ወደሚመለከተው የኅብረተሰብ ክፍል ስናመራ ግን የዚህ ግልባጭ ወይም ተቃራኒውን ነው የምናገኘው፡፡ ትክክለኛውን የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልጽ ሪፖርት በእጃቸው ይዘዋል ለማለት ያጠራጥራል፡፡
የሙገር ሲሚንቶ ዋጋ መጨመርን በሚመለከት ከፓርቲያቸው አባል የተነሳውን ጥያቄ ሲመልሱ የተናገሩትን አስታውሳለሁ፡፡ የሙገር ሲሚንቶ ዋጋ የጨመረው የፈርነስ ኦይልና የማምረቻ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይኼ ትክክለኛ መልስ ነው ብዬ አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ከአንድ መቶ አሥራ ሁለት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በትልቅ አትራፊነት በአንደኛ ደረጃ የተመዘገበው የሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ ነውና፡፡ የሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ ከአራት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ ሙገር ዋጋ ሰቅሎ ተገቢ ያልሆነ ትርፍ ከሚያግበሰብስ ኅብረተሰቡን ቢመለከት አይሻልም ነበር?
ያልተሰራውን ተሠራ፣ ያላለቀውን አለቀ፣ ያልተጠናቀቀውን ተጠናቀቀ፣ ያልደላውን ደላ፣ ያልተበላውን ተበላ. . . እያሉ መረጃ የሚያቀብሉ ወገኖች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ በቀድሞ መንግሥትም ነበር፣ አሁንም አልጠፋም፡፡
ሕዝብ እየተራበ (ስላልሞተ) አገሩ ጥጋብ ነው፣ አርሶ አደሩ ኑሮውን በጥሩ ሁኔታ እየገፋ ነው፣ በኢኮኖሚ እድገቱ ተጠቅሟል እያሉ መረጃ የሚያቀብሉ ጨካኞች አሉ፡፡ ከታች ያሉ ግልገል ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ለላይኞቹ ያለውን እውነት ማቀበል አይፈልጉም፡፡ ሰላሙ ደፍርሶ እያለ ፍፁም ሰላም ነው፣ ኢኮኖሚ ተናግቶ የተረጋጋ ኢኮኖሚ፣ የኑሮ ውድነቱ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተ ምቾት በምቾት ነው በማለት በውሸት የታጨቀ ሪፖርት ያስተላልፋሉ፡፡
አቶ መለስ ስለ ገጠሩ ሕዝብ፣ ስለ አርሶ አደሩ አኗኗር ትክክለኛ መረጃ ያገኙ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የተወሰነውን የኢትዮጵያ ገጠር ተዘዋውሬ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ባየሁትና በሰማሁት መሠረት የገጠሩ ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ተጠቃሚ ሆኗል በሚለው አልስማማም፡፡ ኢኮኖሚው አደገ፣ ተሻሻለ እየተባለ አርሦ አደሩም ሆነ ከተሜው የኑሮ ውድነቱን ቀንበር መሸከም አልቻለም፡፡ ገበሬው ከብቶቹ በድርቅ መሞት ጀምረዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች እሱ ራሱም እየሞተ ነው፡፡ ወደ ገጠር ከተሞችና አዲስ አበባ እየተሰደደ ነው፡፡
ባለፉት ወራት በተለያዩ ቦታዎች በሺዎችና በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አፍርተዋል ተብለው የተሸለሙት ላይ ተጽዕኖ አላሳደረ እንደሆነ እንጃ እንጂ ሌላውማ ገበሬ ኑሮ ተራራ ሆኖበታል፡፡ ምን የተለየ ነገር አግኝቶ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ይችላል? እንዴት ነው ከኑሮ ውድነት የሚያመልጠው? ውኃ አቁሮ በምግብ ሰብል ራሱን የቻለ አርሦ አደር ምን ያህል ነው? በኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የተጠቀመውስ?
ገጠር ወርደን የገበሬውን ኑሮ ብናይ ቁስሉ ላይ እንጨት እየሰደድንበት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ አምሣ ኪሎ ማዳበሪያ ከአራት መቶ ብር በላይ መግባቱን፣ የትራንስፖርት ክፍያ መጨመሩን፣ ከገበያ የሚሸምታቸው ምርቶች ዋጋና እርሱ የሚሸጠው የሰማይና የምድር ያህል መራራቃቸውን ብንመለከት ኑሮውን ለመግፋት ምን ያህል መከራ እንደሆነበት እናስተውላለን፡፡
መረዳዳት ባህላችን ነበር፡፡ አሁን ግን ነፍስ ለነፍስ ሆነና መረዳዳቱ ሁሉ እየቀረ ነው፡፡ ገጠር ያለው ሕዝብ ከተማ ባለው ልጅ፣ ወንድም፣ እህት ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ወዳጅ ይረዳ ነበር፡፡ አሁን ያ መረዳዳት የኑሮ ውድነቱ በፈጠረው ጫና እየተበጠሰ ነው፡፡ ከተሜው እንኳን ሌላውን ሊረዳ የራሱንም ነፍስ ለማቆየት ፈተና ሆኖበታል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ያንኮታከተው እንደዘበት በመቶኛ እንደሚጠቀሰው ጥቂት አይደለም፡፡ በሺህ የሚቆጠር ደመወዝ የሚያገኙ እንኳ የኑሮ ውድነቱን ጫና መቋቋም ተስኗቸው እጅ ሊሰጡ ምንም አልቀራቸውም፡፡
ገቢያቸውን በብዙ አቅጣጫ ማሳደግ የሚችሉት ትላልቅ ባለሃብቶች ናቸው፡፡ ሌላው "የገቢ መጠኔን ማብዛት አለብኝ" ብሎ ቢተጋ፣ ቢወጣ ቢወርድ አይሆንለትም፡፡ የሚሠራውም በቀላሉ አያገኝም፡፡ አጋጣሚ ቢያገኝ እንኳ ለወሬ የሚበቃ አይደለም፡፡
የገጠሩ ሕዝብ ጩኸቱን እዚያ ያሉ ኃላፊዎች እየቀሙት ነው እንጂ፣ ጩኸቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ምን ያህሉ ገበሬ ነው የእርሻ መሬት በበቂ ሁኔታ ያለው? ለምን ያህሉስ ነው የአየሩ ሁኔታ ተመቻችቶለት በልቶ የሚያድረው? ምን ያህሉ ነው ተርፎት ለገበያ የሚያቀርበው? ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ አሠራር ተላቅቆ ገበያ መር ወደሆኑ እህሎች (ሰብሎች) የተሸጋገረው አርሦ አደር ቁጥር ምን ያህል ነው? አሁን በምቾት ላይ ያለው የደቡብ፣ የሰሜኑ፣ የምሥራቁ ወይስ የምዕራቡ አርሦ አደር ነው?
ከተማ ደግሞ እንምጣ፡፡ በአዲስ አበባ ምን ያህል ሥራ አጥ፣ ምን ያህል የጎዳና ተዳዳሪ፣ ምን ያህል ጡረተኛ፣ ምን ያህል ለማኝ አለ? ምን ያህሉስ ሠራተኛ ገቢው አስተማማኝ ነው? ከከተማ ነዋሪው በኑሮ ውድነት የቃሪያ ጥፊ የተመታው እንደ አቶ መለስ አባባል ጥቂቱ ብቻ ነውን?
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቀርቶ በኤክስፐርት ደረጃ ያሉትና ጥሩ ደመወዝ ያገኛሉ የሚባሉትም ገቢያቸው ከኑሮ ውድነቱ ጋር ፈጽሞ ሊጣጣም አልቻለም፡፡ ዕድለኛ ሆኖ የቀበሌና የራሱ ቤት ያለው መተንፈስ ይችል ይሆናል፡፡ ከግለሰቦች የተከራየ ከሆነ ግን ከሌሎች ወጪዎች ጋር ተደማምሮ ኔጋቲቭ ውስጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የምግብ እህሎችና የሌሎች ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ በአጭር ጊዜ በብዙ እጥፍ አድጓል፡፡
የመለስ ሪፖርትን ተከትሎ በምግብ እህል ላይ ተጥሎ የነበረው ተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ ተነስቷል፡፡ መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም መገንዘብ ያለብን የጨመረው የእህል ዋጋ ከታክሱ በብዙ እጥፍ መብለጡን ነው፡፡ ስለሆነም የተቃወሰውን ኑሮ ወደነበረበት ስለማይመልሰው አሁንም በአፋጣኝ ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
"ኢኮኖሚያችን በመሠረቱ ጤናማ ነው፣ የደም ግፊት ሳይሆን ጉንፋን ይዞታል" እያልን ባንዘናጋ መልካም ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያጠናገረው ብዙ ነው፡፡ ክፉኛ የተጠናገረውና ክፉኛ የተመታውን ሕዝብ እንዴት ማከም እንችላለን? በቀበሌ በኩል የተወሰነ መጠን ያለው ስንዴ ለተወሰኑ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው (ከገበያው ጥቂት ዝቅ ባለ ዋጋ) በማከፋፈል፣ የምግብ እህል ላይ የተጣለውን ተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ በማንሳት የምንጠብቀው ውጤት ላይ መድረስ አንችልም፡፡
ተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ መነሳታቸው ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል ትምህርት ቤት፣ ይህን ያህል ጤና ጣቢያ መሥራት የሚቻልበትን ታክስ ቀንሰናል እያሉ እንደ ውለታ መቁጠሩ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች ሰው ከሌለ ምን ያደርጋሉ? ሕዝቡ ሲኖር እኮ ነው የአገልግሎት መስጫ ተቋሞች የሚያስፈልጉት፡፡
ሰው እየሞተ፣ በኑሮ ውድነት ቀውስ ውስጥ እየገባ ተቋማት ምን ፋይዳ ይኖራቸዋል? ታክስ የሚሰበሰበው ከሰው ለሰው ነው፡፡ ከምንም በፊት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ መታደግ ነው፡፡
መንግሥት በምግብ እህሎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ ቀነሰለን ብለን እጃችን እስኪግል እንድናጨበጭብ መጠበቅ የለበትም፡፡ የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ ኢኮኖሚውን በአግባቡ መምራት የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡
በልምድ እንደታየው ሌሎች ተጨማሪ እርምጃዎችን ከመውሰድና መፍትሄዎችን ከማፈላለግ ይልቅ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ጊዜያችንን እናጠፋለን፡፡ ከውቅያኖስ የሰፋ ችግር ተደቅኖብን እያለ በምግብ እህሎች ላይ ተጥሎ የነበረው ተርን ኦቨር ታክስና ተጨማሪ እሴት ታክስ ተነሳልን እያልን ብናወድስ ለውጥ አይመጣም፡፡ ይልቅ መንግሥት ሌሎች ጥረቶችን እንዲያደርግ፣ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ መግፋት ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት የማስተዳደር አቅም የሚለካው ሕዝቡን በመምራት ችሎታው ነው፡፡ ሕዝቡ ከምንም በላይ ዳቦ ሊያገኝ የግድ ነው፡፡ ዳቦ ሳያገኝ ዴሞክራሲ፣ ዳቦ ሳያገኝ መልካም አስተዳደር ማጣጣም ይቸግረዋል፡፡ ለነገሩ ዴሞክራሲውና መልካም አስተዳደሩ ከተሳካ ዳቦ ማግኘት አይገድም፡፡ ስለሆነም አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነውና መንግሥት አዙሮ ማየት አለበት፡፡
በታክሶቹ መነሳት ሳቢያ ይቀንሳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የእህል ዋጋ ብዙም አበረታች አልሆነም፡፡ በአንዳንድ ምርቶች ላይ የጥቂት ብሮች ቅናሽ ማየት አልተቻለም አይባልም፡፡ ነገር ግን ቅናሹ አርተፊሻል ነው፡፡ ቀነሱ ሲባል ከሰዓት በኋላ ዋጋቸው የሚጨምር ምርቶች እያጋጠሙን ነው፡፡
ገበያው ፈጽሞ ሊረጋጋ አልቻለም፡፡ ከመሠረቱ የተናጋውን የኢትዮጵያ ገበያና የኑሮ ውድነት ፈጥኖ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ የሚበላው ሲያጣ ማጅራት ሊመታ ይችላል፣ ሥርዓት ሊንድ፣ ሕግ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ሌብነት (ቀማኛነት"፣ ማጭበርበር፣ ዘረፋ ወዘተ. ሊከሰት አይችልም ብለን መዘናጋት የለብንም፡፡ በዚህ ብቻም አያበቃም፡፡ የተራቡ በኑሮ ውድነት የሚፈናቀሉ ሰዎች ሲበዙ ለመምራትም ሆነ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
ነጋዴውን ከመቆጣጠር ይበልጥ ረዥም ርቀት የሚያስኬደው ውድድርን ማበረታታት ይመስለኛል፡፡ ነጋዴን ከነጋዴ እንዲወዳደር ስልት መንደፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥትም የቤት ሥራዎቹን በአጥጋቢ ሁኔታ በመሥራት የተበላሸውን ገበያ ማስተካከል ይኖርበታል፡፡
መረጃዎች በካድሬኛ ሳይሆን የሕዝብን ብሶት መሠረት የሚያደርጉ መሆን አለባቸው፡፡ ሕዝብ ዳቦ እያለ የሚያላግጡ ስላሉ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ ለዳቦ የተሰለፉትን አይታ ለምን እንደተሰለፉ ስትጠይቅ ለዳቦ መሆኑ ሲነገራት "ለምን ዳቦውን ትተው ኬክ አይበሉም" እንዳለችው የሚያሾፉ ብዙ ባይሆኑም አሉ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ባይሆኑብን መልካም ነው፡፡
በድርቅ የማይፈቱ አካባቢዎች በቀላሉ ተፈትተው ታይተዋል፡፡ ጎመን ለአዲስ አበባ ሲያቀብሉ የነበሩ፣ የተገላቢጦሽ ሆኖ ከአዲስ አበባ ሲጭኑ ነበር፡፡ ጎመን በእሥር ሳይሆን በቁጥር ሲቸረቸር ታይቷል፡፡ ዝናቡ በአሁኑ ጅምሩ ካልቀጠለ አደጋው የከፋ ነውና ብርቱ ጥንቃቄና ብርቱ ክትትል ሊደረግ የግድ ይላል፡፡
|