| የነጩ ዘይት ፈተና |
|
|
| Sunday, 06 April 2008 | |
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የ2000 ዓ.ም የኃይል አቅርቦት ትንተና መግለጫውን ባለፈው ኅሙስ ዕለት ይፋ ሲያደርግ የኃይል እጥረቱ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ለብዙ ጋዜጠኞች እንግዳ ወሬ አልነበረም፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንዲህ በይፋ አይናገረው እንጂ ቀደም ብሎ ኃይልን በፈረቃ የማዳረሱ ጅማሮ መነሻ በቀጥታ ከዚሁ ችግር ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ለመገመት ብዙ ድካምን የሚጠይቅ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ግን የብዙዎች ሕሊና ኮርፖሬሽኑ እንዲህ በድንገት እንዴት ኃይል ሊያጥረው ቻለ? ከሚለው ጥያቄ ጋር የተቆራኘ ሆኗል፡፡አቶ ምህረት ደበበ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ በኃይል እጥረቱ ጉዳይ ከመናገራቸው በፊት ዘርፉ በኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ተቋማት ቁንጮው መሆኑን በኩራት ይገልፃሉ፡፡ የዘርፉ ዕድገት ፈጣን በሆነ መልክ ለማከናወን ከዓለም ባንክ በተገኘ ገንዘብ የ25 ዓመታት የፓወር ሴክተር ማስተር ፕላን መጠናቱን፣ እሱንም ተከትሎ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ውሏል ይላሉ፡፡ የኃይል እጥረቱ እንዴት ሊከሰት ቻለ? ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት የፓወር ሴክተር ዕድገቱ በአማካይ 17 በመቶ ነው፡፡ የ25 ዓመቱ ማስተር ፕላን በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ሲጠና በሶስት ደረጃ ማለትም ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ዕድገት ቢኖር በሚል ታሳቢ መሠራቱን አቶ ምህረት ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በወቅቱ በዘርፉ ከፍተኛውን በመውሰድ 17 በመቶ ዕድገት ሊኖር ይችላል በሚል ታሳቢ ያቀረበው ሃሳብ አበዳሪዎቹ “በዓመት ከአምስት በመቶ በላይ ልታድጉ አትችሉም፡፡ ስለዚህ ትልልቅ ኃይል ማመንጫ መገንባት አያስፈልጋችሁም” በሚል ሳይቀበሉት እንደቀሩ ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ዓመታዊ የዘርፉ ዕድገት ከ10 በመቶ በላይ መሆኑ በተግባር መታየቱን ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 1998 ዓ.ም ከተሠሩ ጣቢያዎች የሚመነጨው ኃይል በጠቅላላ 814 ሜጋ ዋት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኃይል ጉድለቱ 80 ሜጋ ዋት መሆኑን አቶ ምህረት ያስረዳሉ፡፡ ከሚገኘው ኃይል ውስጥ 99 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው ከውሀ የሚገኘው ኃይል ነው፡፡ የኃይል ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡ የበርካታ ኢንዱስትሪዎች (ኢንቨስትመንቶች) መከፈት፣ የሕዝብ የኃይል ፍላጎት በከተማም በገጠርም እያደገ መሄድ ትልቁ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ አንድ የኮርፖሬሽኑ ባለሙያ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ ከዓመት ዓመት በገጠር ከተሞች እያስፋፋ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ በከተሞች አካባቢ ደግሞ የሕዝቡ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከማደግ ጋር በተያያዘ ኤሌክትሪክ ነክ ቁሳቁሶችን (የቤት ውስጥ ማብሰያዎችና ማሽኖች) የመጠቀም ልምድ እያደገ መሄድ ጋር የኃይል ፍላጎቱ እያሻቀበ እንዲመጣ ትልቅ ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡ አቶ ምህረት በቅርቡ በኢትዮጵያ 90 በመቶ ኃይል እንዳልነበር ወይንም ሽፋኑም እጅግ ዝቅተኛ የነበረበት ሁኔታ መኖሩን ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኃይል ሥርጭት ሽፋኑ 22 በመቶ ማደጉን፣ በቅርቡም 30 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት በዓመት 20 ሺህ ያህል አዲስ ደንበኞችን ያገኝ የነበረው ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በዓመት 350 ሺህ ደንበኞችን የማፍራት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ደንበኛ ሲባልም አንድ ግለሰብ እና ባለፋብሪካ ያው እንደ አንድ ደንበኛ እንደሚቆጠር ነገር ግን አንድ ጥሩ ኑሮ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የኃይል ፍላጎቱ 3 ኪሎ ዋት ሲሆን አንድ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግን 20 ሜጋ ዋት መሆኑን በመግለፅ ፍላጎት የቱን ያህል እያደገ መምጣቱን በአብነት ያስረዳሉ፡፡ ቀደም ሲል የኢንዱስትሪውና የማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፉ በቁጥር አነስተኛ፣ በኢነርጂ አጠቃቀም ዝቅተኛ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪውና የቤት ውስጥ የኃይል ፍላጎት እያደገ ሄዶ ከጠቅላላ 69 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ከዚሁ ውስጥ ደግሞ 31 በመቶ የቤት ውስጥ የኃይል ፍጆታ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ይገልፃል፡፡ ምን ተስፋ አለ? በአሁኑ ወቅት ተከዜ፣ ግልገል ጊቤ 2ኛ፣ በለስ፣ የንፋስ ኃይለ ማመንጫ፣ ፊንጫ አመርቲ ኔሽ፣ ጊቤ 3ኛ በጠቅላላው 3270 ሜጋ ዋት ያመነጫሉ ተብሎ የታሰበ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በአማካይ በ4 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ አሁን ያለው 814 ሜጋ ዋት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ለጎረቤት አገራት ኤክስፖርት የማድረግ የቅርብ ጊዜ ሕልምን ዕውን ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በተለይ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ግብ መምታት ወሳኝ የሆነው የፋይናንስ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ በጠቅላላ 124 ቢሊዮን ብር የሚፈለግ ሲሆን ከዚሁ ውስጥ 60 በመቶ በውጪ ምንዛሪ ፍላጎት የሚሸፈን መሆኑ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ፋይናንሱ ደግሞ ከዕርዳታ፣ ከብድር፣ በመንግሥት አቅም፣ በኮርፖሬሽኑ አቅም የሚሸፈን ከመሆኑ አንፃር ፕሮጀክቶቹ በታሰበላቸው ጊዜ እንዳይከናወኑ ተፅዕኖ እንዳይጠነክር ተሰግቷል፡፡ የተከዜ ፕሮጀክት ዘንድሮ በሐምሌ ወይም በነሐሴ ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ይኸም ሲሳካ አሁን እየታየ ያለውን ችግር ያስተነፍሳል በሚል ኮርፖሬሽኑ ትልቅ ተስፋን ሰንቋል፡፡ በተጨማሪም 120 ሜጋ ዋት ይገኝበታል ተብሎ የተገመተው የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊው እየተለየ መሆኑን፣ በቅርቡ ወደ ግንባታ ይገባል ተብሎ እንደሚታሰብ ከአቶ ምህረት ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለጊዜው ምን አማራጭ ይኖራል? ኮርፖሬሽኑ ሁለት ትልልቅ አማራጮች መኖራቸውን ለደንበኞቹ ይገልፃል፡፡ አንደኛውና ዋና ሥራ አስኪያጁ ደጋግመው በአፅንኦት የሰጡበት ጉዳይ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሕብረተሰቡ በቁጠባ እንዲጠቀም የሚያስችለውን ባህል ያዳብር የሚለው ነው፡፡ በአሁኑ የኃይል አጠቃቀም ባህል 100 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ቢኖረንም እንኳን ከችግር አንወጣም ባይ ናቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ፡፡ ስለሆነም የኃይል ቁጠባ፣ ቁጠባ፣ አሁንም ቁጠባ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ተቋማት፣ ኢንዱስትሪዎች ተጠባባቂ ኃይል (ጄኔሬተር) የሚተክሉበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ የማስተማር፣ የመምከር፣ የሙያ እገዛ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ይኸው ጉዳይ አሳስቦት የሙያ እገዛ የሚሰጥ ቢሮ አቁቁሞ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችና የንግድ ተቋማት ተጠባባቂ ኃይል እንዲኖራቸው እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ምህረት ይናገራሉ፡፡ እናም ክረምቱ እስኪገባ፣ ተከዜም በነፍስ እስኪደርስልን የኃይል እጥረቱ፣ ፈረቃው ይቀጥላል፡፡ ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጎን ለጎን የነጩ ዘይታችን ወይም 99 በመቶ ከውሀ ሀብታችን የሚገኘው የፓወር ሴክተሩ አብሮ መሮጥ ካልቻለ እጥረቱ በቅርቡ የመፈታቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ይሆናል፡፡ በፍሬው አበበ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |