|
Sunday, 06 April 2008 |
|
ኢትዮጵያ የራሷ በሆነው የዘመን አቆጣጠሯ (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት መጋቢት 26 ቀን 2000 ዓ.ም ጸደይ ወይም በልግ ተብሎ የሚታወቀውን የዓመት ወቅትን ተቀብላለች፡፡ በበጋ (ሐጋይ) እና በክረምት መካከል ያለው ጸደይ ዐጨዳ፣ ያጨዳ ወራት እንደሆነ፣ ዘመነ በልግ በወዲያ መከር፣ በወዲህ በልግ የሚደርስበት፣ የሚታጨድበት፣ ወዲያውም የሚዘራበት ወርኀ ዘርዕ እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፋቸው ገልጸውታል፡፡ ከመጋቢት 26 ተነሥቶ እስከ ሰኔ 25 ቀን ድረስ የሚዘልቀው ጸደይ የበጋ ዝናም፣ የበጋ ቡቃያና መከር፣ የዘር ወራት ማለትም ነው፡፡
አራት ወቅቶች (ክፍለ ዓመት) በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ልዩ አገልግሎት ይሰጥባቸዋል፡፡ ለየክፍለ ዓመቱ የሚስማማ ንባብና ዜማ በስድስተኛው ምእት ዓመት ማህሌታይ ያሬድ ባዘጋጀው መጽሐፈ ድጓ አማካይነት ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ አራቱ ወቅቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ክረምት፣ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 መፀው፣ ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25 በጋ፣ ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25 ጸደይ፣ ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25
የበልጉንና የመከሩን ዝናብ ለምኑ፤ ለእያንዳንዱም በሜዳ ውስጥ ሣርን ያበቅላሉና፡፡ ዐውድማዎቻችን በእህል ይሞሉ፣ መጥመቂያዎቻችንም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፍሱ፡፡ በሔኖክ ያሬድ |