Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የአኙዋሃ ባህላዊ ዘፈኖችና ዳንኪራዎች
የአኙዋሃ ባህላዊ ዘፈኖችና ዳንኪራዎች Print E-mail
Sunday, 06 April 2008
የአኙዋሃ ብሔረሰብ፣ በጋምቤላ ክልል ከሚታወቁት ባሮ፣ ጊሎ፣ አኮቦ፣ አሌዌሮናቺሩ የወንዝ ዳርቻዎችና አካባቢዎች ኑሮውን የመሰረተ ነው፡፡

ብሔረሰቡ በአመዛኙ መተዳደሪያው እርሻ ቢሆንም በከፊል በከብት፣ በዶሮ እርባታና በማር ምርትም ተሰማርቷል፡፡

 

በወጣቱ ክፍል ባህላዊ ዘፈኖች እንደየወራቱ አመቺነትና ፍላጎት ይዘፈናሉ፡፡ ወደ ባህላዊ ዘፈኖቹ ከቀበሌ ቀበሌ በተያዘ የጊዜ ቀጠሮ በመሄድ፣ ችሎታውን ከአቻው ጋር በማሳየትና በመወዳደር ዘፈኑን ያዘወትራል፡፡ ባህላዊ ዘፈኖቹ በተለያዩ የፍቅር ዜማዎች የሚታጀቡና በከበሮዎች ድምፅ የሚቃኙ ናቸው፡፡

ባህላዊ ከበሮዎች በብሔረሰቡ ሥርዓት የተለየ ክብር የሚሰጣቸው ንብረትነታቸው የየቀበሌው ባላባት ሆኖ ከሕዝቡ ጋራ የሚዘጋጁና የሚሰሩ በመሆኑ በሙያው የተካኑ ሰዎች ተሳትፎ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ የተለያዩ መጠን ያላቸው እነዚህ ባህላዊ ከበሮዎች የሚዘጋጁት ከአንድ ወጥ የዱር እንጨት በባለሙያ ተጠርበውና ተቦርቡረው ነው፡፡ ከወደ አፋቸው ሰፋ፣ ከወደ መቀመጫቸው ሾጠጥ ብለው በተስተካከለ ቅርፅ የሚዘጋጁት እነዚህ ከበሮዎች በከብት ቆዳ የሚሸፈኑ እንደመሆኑ በጥበብ ሰፍቶና ወጥሮ ተገቢውን ድምፅ በሚያሰማ መልኩ ለማዘጋጀት ራሱን የቻለ የቡድን ሥራ ይጠይቃል፡፡ ለባህላዊ ከበሮዎቹ በአንድ ቀበሌ ክልል ውስጥ በተቻለ መጠን የተለያዩ ስያሜ የሚሰጣቸው ትላልቆቹ (ስያሜያቸው ከቀበሌ ቀበሌ ቢለያይም) ከሁለትና ከዚያ በላይ፤ መጠናቸው አነስ ያሉትና "ኚኔት" የሚባሉት ከሦስት በላይ፤ እንዲሁም ለባላባታዊ ሥርዓት ብቻ የሚያገለግሉ "ኡዶሌ" የሚባሉ ከበሮዎችም አሉ፡፡

በአኙዋሃ ባህላዊ ከበሮዎች ከዘፈን ሌላ ለተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ማሳሰቢያና መልዕክት ማስተላለፊያ እንዲሁም በአካባቢው ሥርዓት የሥልጣን ሽግግር መደረጉን ማስገንዘቢያ ሆነውም ያገለግላሉ፡፡ የሚቀመጡትም በባላባቱ ዘንድ ነው፡፡

የአኙዋሃ ባህላዊ ዘፈኖች "ኡካማ" እና "ኩሩማ" ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ከእነዚህ አብይ ባህላዊ ዘፈኖች ውጭ ብዙ ጊዜ የማይዘወተር "አኩርቦክ" የሚባል እንካ ስላንቲያ የሚበዛበት እንዲሁም "ኮሮ" ተብሎ የሚታወቀው ዝላይን ማዕከል ያደረገ ጭፈራም አለ፡፡
በባህላዊ ዘፈኖቹ ወጣቶች የሚተዋወቁበት፣ የሚተጫጩበት፣ ፍቅረኛሞች የጊዜ ቀጠሮ የሚለዋወጡበትና በቀላሉ የሚገናኙበት በመሆኑ በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡

ኩሩማና ኡካማ ለየቅል ሆነው በተለይ ኩሩማ ከኡካማ በተለየ ራሱን የቻለ የአዘፋፈን ስልት እና የከበሮዎች ምት አለው፡፡ ኩሩማ ብዙ ጊዜ የሚዘወተር ሳይሆን በተለይ በክረምትና በመፀው ወራት በጥጋብ ጊዜ የሚደረግ ነው፡፡ ጊዜው የተዘራው እህል ለምግብነት ደርሶ አዝመራው ተሰብስቦ ለጎተራ ዝግጁ ይሆናል፡፡ ምግብና ባህላዊ መጠጡም ይትረፈረፋል፡፡

ባህላዊ ዳንኪራው ራሱን የቻለ የአጠያየቅ ሥርዓት አለው፡፡ በመጀመሪያ የአንድ ሰፈር ጎረምሶች ተመካክረው በተለይም እጮኛዎቻቸውን በቀላሉ ለመገናኘት ሲሉ በባላባቱ መኖሪያ አካባቢ (ቡራ/አሙሃ) ሄደው ከበሮዎች ለኩሩማ ዘፈን እንዲሰጣቸው ያስፈቅዳሉ፡፡ ለኩሩማ ዘፈን ተፈላጊዎቹ ሦስቱ ከበሮዎች ሲፈቀድላቸው በግምቱ ከ11፡00 እስከ 12፡ዐዐ ሰዓት ገደማ ለመጨፈሪያ በተዘጋጀው ሜዳ "ቱሩ" መሃል በተተከለው "ዲኬሪ" የሚባለው ባላ እንጨት በመስቀል የኩሩማ ጨዋታ በምሽት ስለመኖሩ በማብሰሪያ የከበሮ ምት ለቀበሌው ነዋሪ ያሳውቃሉ፡፡ የከበሮው ድምፅ እንደተሰማም ጎረምሶች በጩኸት ካሉበት የምስራች ድምፅ በማሰማት እስከ እኩለ ሌሊት ለሚዘልቀው ጭፈራ ዝግጁ ይሆናሉ፡፡ ይህ ዝግጅት በጊዜ መታጠብን፣ ራት መብላትን፣ ሙሉ የጨረቃ ብርሃን አለመኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ዘፋኝ ጎረምሳ በተናጠልም ሆነ በጋራ ችቦ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ አለበለዚያ ተገቢውን ብርሃን አግኝተው ለመዝፈንም ሆነ የተበታተነ መንደር ከሆነም ወደየቄያቸው ለመመለስ አይቻላቸውም፡፡

ኩሩማ በሦስት ከበሮዎች የሚቃኝ ሆኖ የከበሮዎቹ ምትም ስልት ያለው ጥበብን የሚጠይቅ ነው፡፡ በተለይም ትልቁን ከበሮ የሚደልቀው ሰው ለዚህ የተለየ ችሎታና ልምድ ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ለኩሩማ ተስማሚ የሆነውን ምት ማወቅ ብቻ ሳይሆን የጨዋታውን ስልት ጠንቅቆ የተገነዘበ ሆኖ ለከበሮ መምቻ የተዘጋጀውን አጭር የእንጨት ብትር (ዲተጎ) በአንደኛው እጁ (ብዙውን ጊዜ የቀኝ) ይዞ ከበሮውን ከጥግና ከመሃል እያፈራረቀ በመምታትና በሌላኛው የግራ እጁ ደግሞ የከበሮውን መሃል በመደለቅና እንደየአስፈላጊነቱ ጣልቃ እያስገባ ክርኑን ወይንም አንጓውን በከበሮው መሃል ላይ በመጫን በሚያሰማው ከፍተኛ ድምፅ የኩሩማ ዘፈን ውዝዋዜን መቃኘት ይኖርበታል፡፡ ሁለቱ ትናንሽ ከበሮዎች በሁለት ሰዎች በተከታታይ እየተመቱ ከትልቁ ከበሮ ጋር መቀናጀት ይኖርባቸዋል፡፡

የኩሩማ ዘፈን የከበሮዎች ምት ከዜማና ከውዝዋዜው ጋር መጣጣም ሲኖርበት በተመሳሳይ ሁኔታም የተወዛዋዡ ስልትም ሆነ የድምፃዊው የዘፈኑን ዜማ አደራደር ከከበሮው ምት ጋር መቀናጀት አለበት፡፡

ለኩሩማ ዘፈን ከተወዛዋዦች ሌላ ድምፃዊ ያስፈልገዋል፡፡ በአንድ የኩሩማ ምሽት ከሁለትና ከዚያ በላይ ዘፋኝ ቢኖሩ ይመረጣል፡፡ እነዚህ ድምፃውያን ተከታታይነት ባለው መልኩ እየተቀባበሉ ዘፈኑን የሚያደምቁ ናቸው፡፡

የኩሩማ ዘፈን አጀማመርም ሆነ የአዘፋፈን ስልት ራሱን የቻለ እንደመሆኑ በቅድሚያ ኮረዳዎች ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ይኸውም ከበሮዎቹ ከተሰቀሉበት "ዲኬሪ" አቅጣጫ ፊት ለፊት መስመር ሰርተው በረድፍ በግምት በአምስት ሜትር ርቀት መስመር ይዘው ለሚሰለፉ (ለሚቆሙ) ወጣቶች ፊታቸውን በማዞር ለዘፈን መዘጋጀት ነው፡፡ ከበሮዎቹ ድምፃቸውን ሲያሰሙና ድምፃዊው የዘፈኑ መጀመር በሚያበስርበት በመጀመሪያ ልዩ ዜማ እነዚሁ ኮረዳዎች በተለየ ማራኪ የአዘፋፈን ስልት ተንደርድረው በመሄድ የመረጡትን ጎረምሳ ለይተው እግሩን በእግራቸው በመንካት ወይንም ፊት ለፊት ሄደው ተሽከርክረው በመመለስ ከማን ጋር ለመጫወት እንደፈለጉ ማመልከት ነው፡፡

ድምፃዊው መዝፈን ሲጀምር ኮረዳዎች እየተንደረደሩ ወደየመረጧቸው ጉብሎች በተለየ ውዝዋዜ በመሄድ ዳንሱን ይጀምራሉ፡፡ በተቃራኒው እያንዳንዱ ወጣትም ባለበት በማራኪ እንቅስቃሴ የቀኝ እጁን ከወደ ኮረዳዋ ወገብ በመስደድና ግራ እጁን ከወደ ቀኝ አንገቷ ላይ ወይንም ያዝ አድርጓት ካሽከረከራትና ወደ መጀመሪያ ቦታ አምጥቶ ቦታ ከመለሳት በኋላ እሷም በእቅፉ ውስጥ ሆና እግሯን እያፈራረቀች በማራኪ ውዝዋዜ በታጀበ የኋልዮሽ አካሄድ ስትመለስ እሱም እየተከተላት ወደ መነሻዋ አድርሷት ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ኮረዳዋ ዳንሰኛው ወደነበረበት መመለሱን ካረጋገጠች ወይንም በዝግታ በመከተል በቅጽበት ተንደርድራ በቀድሞ ሁኔታ እንዲቀበላት ውዝዋዜውና ዳንሱ ውበት ኖሮት እንዲቀጥል ታደርጋለች፡፡ ይህ ሂደት ድምፃዊው ዘፈኑ ማብቃቱን እስከሚያበስርና ለሚቀጥለው ባለተራ ድምፃዊ እስከሚያስረክብ ድረስ ይቀጥላል፡፡

በኩሩማ ምሽት ኮረዳዎች በየዘፈኑ የፈለጉትን ዳንሰኛ የመምረጥና በአንድ ዳንሰኛ ያለመወሰን መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ የከበሮ መቺዎች በፈቃደኛነት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎና አለመሰልቸት ለዳንኪራው ውበትና ቆይታ ወሳኝነት አለው፡፡ ጭፈራው እስከ እኩለ ሌሊት ገፍቶ በድምፃዊው የማብቂያ ልዩ ዜማ እስከሚጠናቀቅበት ድረስ የፍቅረኛሞች ግንኙነትም ሆነ የጊዜ ቀጠሮ ልውውጥ አይስተጓጎልም፡፡ ከዘፈኑ ጎን ለጎን የትውውቅ ሂደት ከመቀጠል የሚያግደው የለም፡፡

ኩሩማ ባህላዊ ዳንኪራ በአኙዋሃ ብሔረሰብ ተወዳጅነት ያለው ባህላዊ ጨዋታ ቢሆንም በተለይም እስከ 196ዐዎቹ መጨረሻ ድረስ "በሉል" የተፈጥሮ አካባቢ በአቦቦና በጎግ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች በሚኖሩ የማህበረሰቡ አባላት ቢዘወተርም በደርግ ዘመን የክልሉን የየቀበሌ ባላባታዊ ሥርዓት ከማውገዝ ጋር ተያይዞ ባህላዊ እሴቶች፣ ልምዶችና ወጎች በአድኃሪነት ተፈርጀው እንዲወገዱ በሚል አስተሳሰብ ሳቢያ ባህላዊ ዘፈኖቹ መዝናኛነታቸው እየቀነሱ ወጣቶችም በኪነት ቡድኖች እንዲደራጁና በአብዮታዊ መዝሙሮች እንዲተኩ መደረጉ ለመዳከሙ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኩሩማ የሚባለው ባህላዊ ዳንኪራ መቅረት የለበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባህላዊ ከበሮዎች በጥንቃቄ ያስቀመጡ ቢኖሩ በጣት የሚቆጠሩ ቀበሌዎችና ለብሔረሰቡ ባህል መጠበቅ የሚቆረቆሩ ናቸው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የዚህ ባህላዊ ዘፈን ውዝዋዜ፣ ስልትና የከበሮ ምት ጠንቅቆ ማወቁ ያጠራጥራል፡፡ የማንነቱ መገለጫ የሆነውን ባህላዊ ዘፈን ማየትና ማወቅ አለበት፡፡

ባህላዊ ዘፈኖቹም ሆኑ የከበሮቹ ምት የሚያውቁት የያኔው ኮረዳዎችና ጎረምሶች የዛሬው አረጋውያን ናቸው፡፡ እነዚህን ከወደሁ ፈልጎ አሰባስቦ ባህሉ ከመረሳቱም ሆነ ከመጥፋት መታደግ ይኖርባቸዋል፡፡
በኡዶል አጉዋ ኡጃዋቾ

 
< Prev   Next >