|
Sunday, 06 April 2008 |
 ወ/ሮ ሙሉ ቀንዓ በቦታው ስንደርስ ምሳ ሰዓት በመሆኑ የመኪና ማጠብ ስራቸውን ጨርሰው ከመኪና ባለቤቶች በአደራ የተሰጣቸውን የመኪና ቁልፍ ለማስረከብ ዛፍ ጥላ ሥር ቁጭ ብለው አብረዋቸው ከሚሰሩ ወንዶች ጋር እያወሩ ነበር፡፡ የ49 ዓመት እድሜ ያላቸው ወ/ሮ ሙሉ ቀንዓ በመኪና ማጠብ ሥራ ከ15 ዓመታት በላይ ልጆቻቸውን አስተዳድረዋል፡፡
መኪና ተጠብቆ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል በመጀመሪያ ያስረዳቸው የስድስት ዓመት ልጃቸው ነበር፡፡ ..ፈረንጆች ጋር እየተከተለ ይሄድ ነበር፡፡ እነሱም ይረዱታል፡፡ ከፈረንጆቹ ጋር ሲሄድ መኪና እየጠበቁ ገንዘብ የሚሰጣቸው ሰዎች አይቷል፡፡ ማታ እቤት ሲመጣ እንዲህ አይነት ቦታ መኪና ብትጠብቂ ብር ይከፈልሻል፣ ፈረንጆችም ይረዱሻል አለኝ..
የልጃቸውን ምክር የሰሙት እናት የጉሊት ሥራቸውን እርግፍ አድርገው ትተው ወደተባለው ቦታ አመሩ፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ፊት ለፊት መኪናቸውን የሚያቆሙ የድርጅቱ ሠራተኞችና እንግዶች መኪናቸውን ለሚጠብቅላቸው ሰው በመኪና አንድ ብር ወይም 50 ሳንቲም ይከፍላሉ፡፡ እሳቸውም ጠጋ ብለው ሥራ ጀመሩ፡፡ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት በአገራችን ፓርኪንግ ሳይጀመረ ወ/ሮ ሙሉ ቀንዓ ሥራውን ተቀላቅለው ነበር፡፡
ወ/ሮ ሙሉ ተወልደው ካደጉበት ወለጋ ለአናፂነት ሥራ ወደ አካባቢው ብቅ ካሉት እንግዳ ጋር ተዋደው ትዳር ቢይዙም የቤቱን ሥራ ከማከናወን ውጭ ሌላ ሥራ ሰርተው አያውቁም ነበር፡፡ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ አድርገው ሰባት ልጆች እንዳፈሩም የወ/ሮ ሙሉ ባለቤት በሞት ተለዩዋቸው፡፡ ወ/ሮ ሙሉ በቀን ሥራ፣ በጉሊት ንግድና በኋላም መኪና በመጠበቅ ሥራ የተሰማሩትና የውጭውን ሥራ ያዩት ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲሉ ነበር፡፡
በአናጺነት ሥራ ቤተሰቡን ያስተዳድር የነበረ ባለቤታቸው በሞት ከተለያቸው በኋላ ሰባት ልጆቻቸውን ማሳደግ በእሳቸው ትከሻ ላይ ብቻ የወደቀ ሆነ፡፡ ከቤት ወጥተው የቀን ሥራ መስራት ጀመሩ፡፡ እንጀራ እየጋገሩ በወር አንድ ቤት ውስጥ እስከ 5 ብር ያገኛሉ፡፡ ይህ ብቻ ለኑሯቸው በቂ ስላልሆነ ቃሪያ፣ ጎመን፣ ቲማቲምና ሽንኩርት መቸርቸር ጀመሩ፡፡ ትርፉ ግን ይሄን ያህል ነበርና ልጃቸው የጠቆማቸው የሥራ መስክ ሳያዋጣቸው እንደማይቀር ገመቱ፡፡ በቀን እስከ 20 መኪና እየጠበቁ ከ10 ብር በላይ ቤታቸው ይዘው መግባት ጀመሩ፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ የመኪና ጥበቃውን ትተው መኪና ወደ ማጠብ ተሸጋገሩ፡፡ ..ጥበቃው ላይ የሚሰሩ ሰዎች ሲበዙ የማገኘው ገቢም ቀነሰ፡፡ በዛ ላይ አንድ መኪና ጠብቀሽ የምታገኚው 50 ሳንቲም ወይ አንድ ብር ነው፡፡ አንድ መኪና ብታጥቢ ግን እስከ አራት ብር ድረስ ይገኛል፡፡ ስለዚህ 50 ሳንቲምና አንድ ብር ከምለቃቅም የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብዬ ነጠላዬን ጥዬ መኪና ማጠብ ጀመርኩ፡፡..
በደንበኞቻቸውና በአካባቢው መኪና በማጠብ በተሰማሩ ልጆች ዘንድ እማማ ሙሉ በመባል የሚታወቁት እናት መኪና ማጠብ ቢጀምሩም ውሃ ቀድቶ ማምጣት ግን ፈተና ሆነባቸው፡፡ አንድ ባልዲ ውሃ ለመቅዳት በተለምዶ ቡልቡላ ወንዝ በመባል ከሚታወቀው ገብተው ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እድሜያቸውና የሰውነት አቋማቸው ይሄንን እንዲያደርጉ አላስቻላቸውም፡፡ ..እዛ ጉድጓድ ውስጥ ብገባ ወድቄ እቀራለሁ እንጂ አልመለስም.. ይላሉ፡፡ በመሆኑም አንድ መኪና አጥበው ከሚያገኟት አራት ብር ለአንድ ባልዲ ውሃ 50 ሳንቲም እየከፈሉ ውሃ በማስመጣት ያጥቡ ነበር፡፡
..አንድ መኪና ለማጠብ አንድ ባልዲ ውሃ አይበቃም፡፡ ደንበኞቼ የውስጥ መረጋገጫ ላስቲኮች ሁሉ እንዲታጠቡላቸው የመኪናቸውን ቁልፍ ሰጥተውኝ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ውስጡን ሁሉ ለማጠብ እስከ 3 ባልዲ ውሃ ይፈጃል፡፡ ደንበኛዬ 4 ብር ቢከፍለኝ ብር ከ50 ሳንቲም ውሃ ለማስመጣት እከፍላለሁ.. የመኪና አጠባ ሥራቸው ወጪ ቢኖርበትም የተሻለ ሆኖላቸዋል፡፡ በቀን እስከ ስድስት መኪና በማጠብ በጊዜው ..ጠቀም.. ያለ ገንዘብ ይዘው ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር፡፡
በእስጢፋኖስ በኩል ያለው በር ቀርቶ መኪኖቹ በካዛንቺስ ሱፐርማርኬቶች በኩል በሚገኘው በር መቆም ከጀመሩ በኋላ ግን ለውሃ ቀጂ የሚያወጡት ወጪ ቀርቶላቸዋል፡፡ በውሃ ወጪ የተቸገሩት እማማ ሙሉ አካባቢውን እየዞሩ ሲያስሱ በቅርብ አንዲት ምንጭ አገኙ፡፡ አሁን ከዚህችው ምንጭ በባልዲያቸው እየቀዱ በማመላለስ የደንበኞቻቸውን መኪና ያጥባሉ፡፡
ካዛንቺስ፣ ራስ ሙሉጌታ ሰፈር የሚኖሩት እማማ ሙሉ ከቤታቸው ለሥራ የሚወጡት 1፡30 ሰዓት ላይ ነው፡፡ በእግራቸው ተጉዘው ሁለት ሰዓት ወደ ድርጅቱ የሚገቡ የቢሮ ሰራተኞች ከመግባታቸው በፊት ይደርሳሉ፡፡ ከደረሱበት ሰዓት ጀምሮ የሚመጡ መኪኖችን እየተረከቡ እቃ እንዳይጠፋ መጠበቅ ይጀምራሉ፡፡ አብረዋቸው ከሚሰሩ አራት ወንድ ልጆች ጋር በመከፋፈል እንዲታጠብላቸው የሚፈልጉ ደንበኞቻቸውን መኪና ሲያጥቡ ይውላሉ፡፡ በግምት ከ100 በላይ መኪና የሚቆምበት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ፊት ለፊት በህጋዊነት መኪና እንዲጠበቁና እንዲያጥቡ እማማ ሙሉን ጭምሮ ለአራት ወንዶች ብቻ የተሰጠ መብት ነው፡፡ ለዚህም በ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ፈርመው በታማኝነት ሊጠብቁ ቃል ገብተዋል፡፡
እማማ ሙሉ መኪና ሲያጥቡ ሲጠብቁ ውለው የመኪናው ባለቤቶች 7፡00 ሰዓት ላይ ለምሳ ሲወጡ ቁልፍ ካስረከቡ በኋላ ነው ለምሳ የሚንቀሳቀሱት፡፡ በእግራቸው ቤታቸው ደርሰው በልተው ይመለሳሉ፡፡ አንዳንዴ ሲደክማቸው እዛው አካባቢ የቀን ሰራተኞች የሚመገቡባት ቤት ውስጥ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ምሳ በልተው እንደሚመለሱ ነው የገለጹልን፡፡ ምሳ ቋጥረው ግን ከቤታቸው አይወጡም፡፡ ለምን? ብያቸው ነበር ..እቤት ውስጥ የማሳድጋቸው ሁለት የልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ እኔ ብጎዳ ይሻላል ብዬ ለእነሱ ቋጥሬላቸው ነው ከቤት የምወጣው፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ እቤት የዋለ ልጅ ሁሉ ያለውን ነገር ምሳ ስለሚሰሩ ሄጄ እቀምሳለሁ፡፡ አሁን ኑሮ ትግል ነው፡፡ የሚበላ ሲጠፋ መዋልም ይኖራል፡፡..
ጉልበታቸው እየደከመ መሆኑን የሚናገሩት እማማ ሙሉ አብረዋቸው የሚኖሩ ሁለት የልጅ ልጆቻቸውንና አራት ልጆቻቸውን ለማስተዳደር የመኪና ማጠብ ሥራቸውን መቀጠሉ የግድ ነው፡፡ ..ቢያመኝ እንኳን ካልጣለኝ በቀር እቤቴ አልውልም፡፡ አምስት ብርም ይዤ ብገባ ተስፋ ነው.. ይላሉ፡፡
የኑሮ ውድነት ጣሪያ በነካበት በአሁኑ ወቅት የእነ እማማ ሙሉ ሥራ ..ደሞዝ.. አልጨመረም፡፡ የፈለገ 5 ብር ያዘነ 10 ብር ይሰጣቸዋል፡፡ ከዛ ውጭ የመኪና አጠባ ክፍያቸው በድሮው ዋጋ እንደቀጠለ ነው፡፡ ታዲያ ኑሮ እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር ..አሁን ኑሮው ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛል፡፡ በርካሹ ጊዜ ገንዘብ አጠራቅሜ የመጀመሪያ ልጄን ትንሽ ሱቅ ነገር ከፍቼላት ነበር፡፡ ሌላዋን አንድ ልጄንም ወደ አረብ አረር ልኬያለሁ፡፡ አንዱ ወንድ ልጄም ራሱን ችሎ ሌላ ቦታ ይኖራል፡፡ ሁለት የልጅ ልጆቼን ደግሞ አሳድጋለሁ፡፡ ኑሮው አስቸጋሪ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ያነጫንጨኛል፡፡ 10 ብር ይዘሽ ብትገቢ ከዳቦ አያልፍም፡፡ አንዳንዴ ራስ የቻሉት ልጆቼም ይደጉሙኛል እንጂ ለብቻዬስ አልቻልኩትም፡፡..
እማማ ሙሉ በመኪና አጠባ ሥራቸው ምክንያት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከቤት ውጭ ነው፡፡ ማታ 12፡00 ሰዓት ላይ ነው ቤታቸው የሚገቡት፡፡ የቤቱን ሥራ የሚያከናወኑት ልጆቻቸው ናቸው፡፡ ቤት ማጽዳት፣ እቃ ማጠብ፣ ምግብ መስራት፣ ልብስ ማጠብና ልጆችን አልብሰው ወደ ትምህርት ቤት መላክ የታላላቅ እህቶችና ወንድሞች ድርሻ ነው፡፡ እማማ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ልጆቻቸውን የሚንከባከቡት የረፍት ቀናቸው በሆኑት እሁድና ቅዳሜ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ ቀናትም ቢሆን ጊዜያቸውን ለልጆቻቸው ይስጡ እንጂ ልጆቻቸው እቤት ውስጥ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ አይፈቅዱላቸውም፡፡ የሳቸው የሥራ ድርሻ መሰራት ያለበትን ነገር ይሰራ ብለው ትዕዛዝ ማስተላለፍ ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ የመጨረሻ ልጃቸው በ10 ሰዓት ከት/ቤት ስትመለስ ሥራ ቦታቸው ድረስ በመምጣት መኪና ማጠብ ትረዳቸዋለች፡፡ እማማ ሙሉ በዚህ እድሜያቸው መኪና ለመጠበቅ ጎዳና ላይ ሲወጡ ..ሥራቸው የጎረምሳ ነው.. ብለው ያፌዙባቸው ባይጠፉም ብዙዎቹ በተለይ እሳቸው እንደሚሉት ..የተማሩ ደንበኞቻቸው.. ደግሞ አይዞዎት እያሉ ያበረታቷቸዋል፡፡ በሥራቸው በርትተው ቤታቸውን እንዲያቀኑም ማበረታቻቸው ድጋፍ ሆኗቸዋል፡፡
..ሌላ ባል ባገባ ያልወለደ አባት ልጆቼን ያንገላታብኛል.. ብለው በማሰብ እናትም አባትም ሆነው፤ መኪና አጥበው ያሳደጓቸው ልጆቻቸው እንዳሰቡት በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ላይ ባይደርሱም የተወሰኑት ራሳቸውን ችለው አንዳንዴም ታናናሾቻቸውን መደጎማቸው እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡ በትዕግስት ዘሪሁን |