|
Wednesday, 09 January 2008 |
- ክቡር ሚኒስትር እውነቱን እንናገር ከተባለ የሚያስንቁን እርስዎ ነዎት - እንዴት? - ፀረ ሕዝብ የሆነን ሃይል እናጥራው እንቀይረው ስንል እርስዎ ቆዩ፣ ረጋ በሉ፣ ሰው እንዳይጎዳ ተጠንቀቁ እያሉ መስሪያ ቤቱ የሌቦች መፈንጫ ሆነ፡፡ - አስተውሉ አልኩ እንጂ አታጥሩ አትስሩ አልኩ? - ክቡር ሚኒስትር እርምጃ በወቅቱና በቦታው ካልተወሰደ ምን ዋጋ አለው? አልሰራም ያለ መባረር አለበት፡፡
- አልሰራም ብለሃል ውጣ ማለት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ሠራተኛው ደግሞ አላሰራ አሉኝ ብሎ እየወቀሰ ነው፡፡ - ውሸት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ የሚሰራውማ እየተሻለው ነው፡፡ ይልቁንስ አላሰራ ያሉኝ እኔን ነው፡፡ - እሺ መወሰድ አለበት ስለምትለው እርምጃ አጥንተህ አቅርብልኝ፡፡ - አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እንደ ኤክስፐርትና እንደ አማካሪ አጥንተህ አቅርብልኝ ሲሉኝ ሞራሌ ከፍ ይላል የሥራ ፍላጎቴም ይነሳሳል፡፡ - ገና ላየው ነው እንጂ አፀደቅኩት ማለት እኮ አይደለም፡፡ - ካዩትማ እንሚያፀድቁት እርግጠኛ ነኝ፤ በሙያዬ እተማመናለሁ፡፡ - ከአሁን በፊት አጥንተህ ያቀረብክልኝ መቼ ትክክለኛ ነበሩና? - የትኞቹ ክቡር ሚኒስትር? - ሁለት ሶስቱ ጥናቶችኮ የተበላሹ ነበሩ፡፡ - ያ ሌባ ነዋ.. - የትኛው ሌባ? - ከእኛ መሥሪያ ቤት ወጥቶ አሁን የራሱን የከፈተው፡፡ - እሱ ምን አደረገ? - እኔ በኮምፒውተር ፃፈው ብዬ ስሰጠው ያልሆነ ነገር አስገብቶበት ነዋ፡፡ - በል በል አሁን አጥናና አቅርብልኝ፡፡ - እሺ፡፡ ረከሳምንት በኋላ ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ውጭ መሄድ ነበረባቸውና ወደ አውሮፕላን ማረፊ እየሄዱ ነው፡፡ አማካሪያቸው ደወለ፡፡ ሾፌራቸው ስልኩን ሰጣቸውሪ - እሺ ምን ሆንክ? - ክቡር ሚኒስትር ወደውጭ ከመሄድዎ በፊት ጥናቱን አይተው ይፈርሙልኝ፡፡ - አሁን ኤርፖርት እየሄድኩ ስለሆነ የት ሆኜ ነው የማጸድቀው? - ችግር የለም፡፡ እኔ እዚያው ኤርፖርት ነኝ፡፡ - ስደርስ እንነጋገራለን፡፡ ቻው፡፡ ረሾፌራቸው ራሱን ያካልሪ - ምን ሆነህ ነው? - ክቡር ሚኒስትር ይቅርታ ያድርጉልኝ በማይመለከትህ ገባህ አይበሉኝ እና አንድ ነገር ልናገር፡፡ - ተናገር፡፡ - ይህ አማካሪ የተባለው በሚያቀርብልዎ ሰነድ ላይ ባይፈርሙ ጥሩ ነው፡፡ - ለምን? - ሰራተኛው ሁሉ ይጠላዋል፡፡ - ለምን ይጠላዋል፡፡ - ዋና አጭበርባሪና ሌባ ነው ይለዋል ደግሞም ያወራል፡፡ - ምን ብሎ ነው የሚያወራው? - እኔ ባልኖር ኖሮ ይህ መሥሪያ ቤት ገደል ይገባ ነበር ይላል፡፡ - ሌባ የሚሉትስ ለምንድን ነው? - ያቺን ሆቴል ካቋቋመ ወዲህ ሌባ ይሉታል፡፡ - ሆቴል አቋቋመ እንዴ? - ትንሽ ናት እንጂ አዎን፡፡ - እም... ከእሱ ጋር ትንሽ ላውራ፡፡ አንተ ሻንጣውን አስገባልኝ፡፡ - እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ረከአማካሪያቸው ጋር ያወራሉሪ - ጥናቱ ይኸው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ተግባር ላይ ይዋል ብለው ይፈርሙልኝ፡፡ - ሳላነበው እንዴት ነው የምፈርመው? ለአንድ ሳምንት ነው የምሄደው ስመለስ እፈርመዋለሁ፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ማጠናከሪያ እርምጃችሁን ላኩልን ብለውን የለ፡፡ በሁለት ቀን ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡ የማጠናከሪያ ሃሳብና እርምጃ የለንም ብለን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ማቅረብ ውርደት አይሆንም? - አላነበብኩትም ብየኮ ነው፡፡ - እኔና እርስዎ አብረን ስንሰራኮ ታላቁ ጸጋ እርስ በርስ መናበባችን ነው አያምኑኝም ማለት ነው? - ማመንማ አምንሃለሁ፡፡ - እኔም እርስዎን አምኘ ነው እንጂ ስኮላርሺፕ አግኝቼ እንደነበር ያውቃሉ፡፡ - አውቃለሁ፡፡ እሺ በል አምጣው፡፡ ይኸው ፊርማ ማለት ይህ ነው አይደል? ደስ አለህ? - ስለፈረሙልኝ አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - የመግቢያ ሰዓት ደርሷል፡፡ ቻው፡፡ - የሰላም መንገድ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ቻው፡፡ ረክቡር ሚኒስትር ከሳምንት በኋላ ተመለሱ፡፡ መሥሪያ ቤቱ ብጥብጥ ብሏል፡፡ ፀሐፊያቸውን ይጠይቃሉሪ - አንቺ ምን ሆኖ ነው ይህ መሥሪያ ቤት? ሰዎች ስልክ እየደወሉ አንድ ነገር አድርግ እያሉኝ ናቸው፡፡ - አማካሪ ኤክስፐርት ተብዬው በጥብጦ ነዋ፡፡ - እንዴት? - ሌቦቹ ተሸፋፍነው ደህና ደህና ሰዎች አባረራችሁ፡፡ - ሾፌሩኮ በቀደም አስጠንቅቆኝ ነበር አልሰማ ብዬ ነው እንጂ፡፡ - የትኛው ሾፌር? - የእኔው ሾፌር ነዋ፡፡ - ሌባ ነው፡፡ ጫት ከማመላለስ ሌላ እሱ ደግሞ ምን ያውቃል? እኔ ሁልጊዜ እፈራለሁ፡፡ - ምን ሆነሽ ነው የምትፈሪው? - እሱ እንዴት የእርስዎ ሾፌር ይሆናል ብዬ ነዋ፡፡ - እሺ በኋላ እናወራለን፡፡ አሁን የሞቀ ቡና ላኪልኝ፡፡ - እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ማን ናት ያቺ ቆንጆ ቡና ለምታመጣልኝ ልጅ ንገሪያት፡፡ - እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ረፀሀፊዋ ወጣች፤ ቡና አቅራቢዋ ገባችሪ - እኔኮ ያንቺን ቡና ነው የምወደው፡፡ - አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ሆን ብዬኮ አንቺ እንድታመጪ ለፀሐፊዬ ነግሬ ነው፡፡ - አውቃለሁ እርስዎ እንደዚያ ባይሉማ እሷ አትጠራኝም፡፡ - ለምን? - እሷ እዚህ መሥሪያ ቤት ውስጥ ቅባቶች፣ ልብሶችና ሌሎችም ዕቃዎች ትሸጣለች፡፡ የሚኒስትሩን ቢሮ ሱቅ አታድርጊው ስላልኳት ትጠላኛለች፡፡ - ህ... ም ረሰራተኛዋ ወጣች ፀሐፊዋ ገባችሪ - ክቡር ሚኒስትር ቅሬታችንን ማሰማት እንፈልጋለን የሚሉ ሰራተኞች አሉ ላስገባቸው? - ቡና አቅራቢዋም ቅሬታ አላት፡፡ ታውቂ ነበር? - ይህች ሌባ፡፡ - ማን ሌባ? - አሁን ቡና ያቀረበችው፡፡ - እንዴት ሌባ ሆነች? - የመስሪያ ቤቱን ሳሙና ወደ ቤትዋ ትወስዳለች፡፡ - እስቲ አስተዳዳሪውን ጥሪልኝ፡፡ - የትኛውን አስተዳዳሪ? - የአስተዳደር ኃላፊውን ነዋ፡፡ - አማካሪው ልኮታል፡፡ - የት? - አብረው ሆቴል እየሰሩ አይደል፡፡ የሚያስገቡት ዕቃ አለ መሰለኝ - ምክትሉን ጥሪልኝ፡፡ - ምክትሉማ ከተባበሩት አንዱ ነው፡፡ - በይ ያቺ ማን ናት ስሟን ጥሪልኝ፡፡ - ያችን አጋሰስ ማለትዎ እንዳይሆን? - ኧረ ተይ ጥሩ ሰው ናት፡፡ - ጅል ናት፡፡ - በቃ ተይው ሌላ ጊዜ ይሁን፡፡ - እና እነዚህ ቅሬታ አለን የሚሉት አስገቢያቸው፡፡ - ይግቡ፡፡ ረገቡሪ - ምን ነበር? - አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ቅሬታ አላችሁ? ልትናገሩ ነው የመጣችሁት መሰለኝ? - እኛ ቅሬታ የለንም ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ቅሬታ የላችሁም? አላግባብ ተቀጣን፣ አልተስማማንም የምትሉት ነገር የለም? - እኛ አልተስማማንም፣ ደህንነትም አልጠራንም፣ አልተቀጣንምም? - ታዲያ ለምን መጣችሁ? - ክቡር ሚኒስትሩ ሊያናግሩዋችሁ ይፈልጋሉ ተብለን ነውኮ የመጣነው፡፡ - ይቅርታ ሂዱ ሌላ ጊዜ እጠራችኋለሁ፡፡ የክፍል ኃላፊያችሁን አነጋግራለሁ፡፡ - ያንን ሌባ፡፡ - እንዴት? - ክቡር ሚኒስትር እሱን ከሚያነጋግሩ ዝም ቢሉ ይሻላል፡፡ - ለምን? - እሱኮ ደላላ ነው፡፡ ቢሮም አይገባም፣ ሲደልል ነው የሚውለው፡፡ ስለ እሱ ብዙ አናውቅም፣ እሱም ስለእኛ ብዙ አያውቅም፡፡ - ማነው ሂዱና ተናገሩ ወይም ሚኒስትሩ ያነጋግሯችኋል ያላችሁ? - የፋይናንስ ኃላፊው፡፡ ለነገሩ ሰውየው የራሱ ችግር አለበት፡፡ - የምን ችግር? - ከእርስዎ አማካሪ ጋር ጥለኛ ናቸው፡፡ አማካሪውን እንድንወቅስለት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ መሰለን የላከን? - አማካሪው መጥፎ ነው እንድትናገሩ? - አማካሪውምኮ ሌባ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሁለት ዝሆኖች ሲጣሉ ሳሩ ይጎዳል ብለን እኛ እነሱ መሃል አንገባም፡፡ - አማካሪውን የምትጠሉት ለምንድነው? - አንጠላውም፡፡ እኛንም ይጠቅመናል፡፡ ሆቴሉን ሲያሰራ ቅዳሜና እሑድ ያሰራን ነበር፡፡ ጥሩ ከፍሎናል፡፡ አሁን ሆቴሉን ሲሸጠውም ገዢ ፈልጉ ብሎ ጠቁሞናል፡፡ - ሆቴሉ ተሸጠ እንዴ? - ትናንት ሸጠው፡፡ - ለምን? ውጭ አገር ሊሄድ ፈልጓል መሰለኝ፡፡ - እሺ ቻው፡፡ ረፀሐፊያቸው ጋር ደወሉረሪሪ - ኦዲተሩን ጥሪልኝ፡፡ - የለም፡፡ - እንዴት የለም? - ተባሯል እኮ፡፡ በእርስዎ አማካሪ ከተባረሩት አንዱ ነው፡፡ - ለምን? - ገንዘብ ሰርቀሃል፣ አላወራረድክም ብሎ አማካሪውን ወጥሮ ስለያዘው አባረረው፡፡ - እስቲ ጥሪልኝ፡፡ - የለም፡፡ - የት - አልገባም? - ትናንት ገብቶ ነበር? - ትናንትማ ነበር፡፡ እርስዎም አልገቡም ነበር፡፡ አራት ቀኑ ነው፡፡ - እንደው እስቲ ቤቱ ደውይልኝ፡፡ - ደውዬ ነበር፡፡ ውጭ አገር ሄዷል አለችኝ ሠራተኛው፡፡ - አመንሻት? - እሷን ሳይሆን እዚህ ሰራተኞች ሲያወሩ ሰምቼ አመንኩ፡፡ - የሰማሽው ምንድነው? - ትናንት ውጭ አገር ሆኖ በሬዲዮ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ - ምን የሚል መግለጫ? - ከአገር የወጣበትን ምክንያትና ሥራውን የለቀቀበት ምክንያት፡፡ - ምክንያቱ ምንድነው አለ? - መስሪያ ቤቱ አላሰራ ስላለኝ ነው፡ አለ፡፡ - እሱም? |