| የዳመና መሳሳት ሙቀትን አስከተለ |
|
|
| Sunday, 06 April 2008 | |
![]() አቶ አማረ ባቡ ኃላፊው አቶ አማረ ባቡ እንዳመለከቱት የሙቀቱ መጠን ሊጨምር የቻለው ባለፉት ሁለት ወራት የነበረው የዳመና መጠን በጣም የሳሳና አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የፀሐይ ብርሃን በቀጥታ ወደ መሬት ዘልቆ በመግባት የመሬትን አካባቢ ያሞቀዋል፡፡ ዳመና ካለ የፀሐይ ብርሃን ወደ መሬት ዘልቆ ሊገባ አይችልም፡፡ ዳመና ያልተፈጠረበት ምክንያት የአየር ግፊቶች በተለያዩ ምክንያት ሲዳከሙ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ድክመት ዳግም ወደ እኛጋ የሚመጣውን ርጥበት አየር ይቀንሳል፡፡ እርጥበት አየር ከቀነሰ ዳመና አይኖርም፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን ጨረር ወደ እኛ ጋ ይደርሳል፡፡ ከሀገሪቱ ክፍሎች መካከል ለምሳሌ ያህል በየካቲት አዲስ አበባ ላይ 0.4፣ ድሬዳዋ 0.6፣ አይሳኢታ አንድ፣ በመጋቢት አዲስ አበባ 1.6፣ ድሬዳዋ 2.9፣ አይሳኢታ 0.4 ዲግሪ ሲሊሼልስ መጨመሩን ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ፀሐይ እስከ መጋቢት 12 ቀን 2ዐዐዐ ኢኰዬተርን ታልፍና ሰኔ 14 ቀን 2ዐዐዐ ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ትደርሳለች፡፡ ከዚያም ተመልሳ ወደ ደቡብ ትንቀሳቀሳለች፡፡ መስከረም 14 ቀን እንደገና ኢኪዬተርን ሁለት ጊዜ ታልፋለች፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን ይኖራል፡፡ በተለይ በሀገራችን የክረምት ወቅት ስለሆነ ዳመና በሚኖርበት ጊዜ ላይሰማን ይችላል፡፡ በአንዳንድ ቦታ የሙቀቱ መጠን የሚጠናከርበትና የሚቀንስበትም ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ከሚያዚያ ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ዳመና እየጨመረ ይመጣል፡፡ በተለይ ምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ብዙ ጊዜ በዳመና ሊሸፈን ይችላል፡፡ ቀስ በቀስ እስከ ሰኔ ድረስ ዳመናው እየጨመረ ሊሄድ ይችላል፡፡ በሀገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ወይም ቆላ ዝቅተኛ ቦታዎች እንዲሁም በሁመራና በአፋር በሚያዚያ መጨረሻና በግንቦት መጀመሪያ ላይ ሙቀቱ ሊጨምር ይችላል፡፡ ከግንቦት በኋላ ግን በዳመናው ምክንያት እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችል ተተንብዮአል፡፡ በየካቲትና መጋቢት ወራት ላይ ፀሐይ ወደ ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ስለምትሄድ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ (ሞዛምቢክ፣ የደቡብ አፍሪካ አገሮች፣ ኢንዶኔዢያ) የዝናብ ወቅታቸው ነው፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ የዝናብ መጠን አላቸው፡፡ በምድር ሰቅ አካባቢ እስከ 15 ዲግሪ ሰሜን ድረስ (ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ሱዳን) ሙቀቱ ሊጨምር ይችላል፡፡ በበልግ ወቅት ሙቀታማ ከሆነ በክረምት ወራት ጎርፍ ይበዛል የሚሉ ወገኖች እንዳሉ አቶ አማረ ጠቁመው፣ ይህ አባባል ትክክል ሊሆንም ላይሆንም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ትክክል ሊሆን ይችላል የተባለበት ምክንያት በበልግ ዝናብ ላይ ተፅእኖ የሚያሳድሩ የተለያዩ በርካታ ክስተቶች እንዳሉ በመጠቆም ነው፡፡ ከእነዚህም ክስተቶች አንደኛው "ላኒና" እና "ኤሊኖ" ይባላሉ፡፡ ላኒና የሚባለው የምሥራቅ ፓስፊክ ውቅያኖስ ሲቀዘቅዝ ነው፡፡ ኤሊኖ የሚባለው ደግሞ ይኸው ውቅያኖስ ከተለመደው በላይ ሲሞቅ ነው፡፡ በኤሊኖ ጊዜ በልግ እርጥብ ይሆናል፡፡ ብዙ ዝናብም ይኖራል፡፡ በላኒና ጊዜ በልግ ይደርቃል፡፡ ስለሆነም የአሁኑ ወቅት ላኒና ያለበት ሂደት ነው፡፡ ላኒና እና ኤሊኖ የስፓኒሽ ቋንቋ ሲሆኑ ላኒና ማለት የእግዚአብሔር ሴት ልጅ፣ አሊኖ ደግሞ የእግዚአብሔር ወንድ ልጅ ማለት ነው፡፡ ከጥናቶች ለመረዳት እንደተቻለው የፓስፊክ ውቅያኖስ መቀዝቀዝ በእኛ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በዚህ ጊዜ በልግ ይደርቃል፡፡ ላኒና በክረምቱም የሚቀጥል ከሆነ ዝናቡን ደህና ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህም በክረምት በቂ ዝናብ ሊገኝ ይችላል ማለት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በሕንድና በአትላንቲክ ውቅያኖሶች ያሉትን ሁኔታዎች መከታተል ያስፈልጋል፡፡ በኤጀንሲው ሦስት ዓይነት የትንበያ አሰጣጦች አሉ፡፡ አንደኛው የአጭር ጊዜ ነው፡፡ ይህም ከሦስት እስከ 1ዐ ቀን ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ሁለተኛው የመካከለኛ ጊዜ ሲሆን ይህም ከ1ዐ እስከ 15 ቀን የሚሄድ ነው፡፡ ሦስተኛው የረጅም ጊዜ ትንበያ ነው፡፡ ይህም የወር፣ የበልግ፣ የወቅት፣ የክረምትና የበጋን ትንበያን ያካትታል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለአጭርና ለመካከለኛ ጊዜ የሚተነበዩበት የተለያዩ ሞዴሎች አሉ፡፡ ሞዴሎቹም የአየር ሲስተሞችን አስቀድመው ይተነብያሉ፡፡ የአየር ግፊቶችም ድርቅ ወይስ አነስተኛ ዝናብ ያስመጣሉ በሚል ይተነብያሉ፡፡ የወቅቶችን ትንበያ በሚተነብይበት ጊዜ በአሜሪካ ከሚገኘው የኢሊኖ ጥናትና የክላይሜት ኘሪዲክሽን ማዕከላት የአትላንቲክ፣ የሕንድና የፓስፊክ ውቅያኖሶች ሙቀት ያለበትን ደረጃና ይኸው ሙቀት እስከ አንድ ዓመት ድረስ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለኤጀንሲው ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ላይ መሠረት በማድረግ የሀገሪቱ የአየር ሁኔታ ይተነበያል፡፡ በታደሰ ገብረማርያም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |