| የማያዛልቅ ምክንያት |
|
|
| Sunday, 06 April 2008 | |
|
በመጋቢት 17 ቀን 2000 ሪፖርተር ጋዜጣ ዜና ላይ መብራት የሚጠፋው ያረጁ ምሰሶዎችን ስለሚቀየሩና ይህም እስከ ክረምት ድረስ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሰጡትን መግለጫ አንብቤአለሁ፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንም ውሃ በተደጋጋሚ የሚጠፋው ኤሌክትሪክ ስለሚቋረጥ መሆኑን በመጥቀስ በዚሁ ቀን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀን ስርጭት ላይ ማስታወቂያ አስተላልፎአል፡፡ መብራት የሚጠፋው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንዳሉት ሳይሆን የውሃ እጥረት ስለተከሰተ ለመጠባበቂያ በተዘጋጁ ጄኔረተሮች ስለሚጠቀሙ የፈረቃ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ የድሬዳዋ ጄኔሬተር በመሥራት ላይ መሆኑን በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ፡፡ እጥረት በማጋጠሙ እንጂ የምሰሶ ችግር አይደለም፡፡ በመብራት መጥፋት ምክንያት ድርጅቶች በጄነሬተር እየተጠቀሙ ባሉበት ወቅት (ከ2 ዓመት በፊት) የውሃ መቋረጥ አላጋጠመም ነበር፡፡ ተጠቃሚው እየበዛ መሄዱ ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን መሆን ያለበት በአዲስ ቦታ ሰዎች በሚሰፍሩበት ጊዜ ውሃም ይሁን ሌሎች መሠረተ ልማቶች በቅድሚያ አብረው እየተጠኑ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ የማያሳምኑ ምክንያቶችን መደርደር ከማስተቸት ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በአዲስ አበባ በአሁኑ ሰዓት ኅብረተሰቡ ጀሪካን ይዞ የውሃ ያለህ እያለ በመዞር ላይ ነው፡፡ በአንድ ትልቅ ከተማ ይህንን መመልከት በጣም ያሳፍራል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሚታየው ይኼ መከረኛ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ላይ እውነትነት የሌለው መግለጫ መስጠት ልምድ እየሆነ መጥቷል፡፡ በእቅድ ተሠርቷል፣ ከእቅድ በላይ ተከናውኗል፡፡ እየተባለ ተጠያቂነት የሌለበት መግለጫ መስጠት እየተዘወተረ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቶች በጠንካራ ባለ ሙያ የተደራጁ አይመስሉም፡፡ ጥናቱ ሁሉ ዘላቂነት የሌለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚሆን ወይም ደግሞ በአጭር ቀን ወደ ሥራ ሲተረጐም ደካማ ውጤት ማስመዝገቡ መሆኑ በየዕለቱ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ (ከበደ፣ ከጐተራ) በሌሎች ላይ ጣትን ከመጠንቆል በፊት ወደ ራስ በሪፖርተር ጋዜጣ ኪንና ባህል ገጽ መጋቢት 21 ቀን 2000 “ሰይፉስ ለምን ይዋሻል?” በሚል ርዕስ የወጣውን ጽሑፍ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ ጉድፎች ሲኖሩ ስህተትን ማረም የሚችሉ ጽሑፎች መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ሰይፉ ፋንታሁን በተለይ በኤፍ.ኤም ዘጠና ሰባት ነጥብ አንድ ቅዳሜ ምሽት ከ3፡00 እስከ 6፡00 ሰዓት የሚያቀርበው ዝግጅት ከሞላ ጎደል እከታተለዋለሁ፡፡ አቅራቢው ብዙ ሊታረሙ የሚገባቸው ሕፀፆችን በተደጋጋሚ ሲፈጽም አጋጥሞኛል፡፡ ለኪነ ጥበብ እድገት ተቆርቋሪ ነኝ የሚለው ሰይፉ ለጥበቡ መሟሸት አስተዋፆ በማድረግም እየታወቀ ነው፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቶቹን ለአብነት ያህል መጥቀስ እወዳለሁ፡፡ የሙሉቀን መለሰን ዘፈኖች አስመስሎ የዘፈነውን ብዙአየሁ ደምሴን በዝግጅቱ አቅርቦት ነበር፡፡ የሰውን ሙዚቃ ገልብጦ ..አሳምሮ በመዝፈኑ.. እጅግ አድንቆታል፡፡ አሳምሮ ዘፍኗል ብሎም ሽንጡን ገትሮ ተከራክሮለታል፡፡ ወጥ ሥራዎች እንዲሠሩ መገፋፋት ሲገባው ለብዙአየሁ ወግኖ ሙሉቀንን ለማጣጣል ሞክሯል፡፡ ሌላ ደግሞ ላቅርብ፡፡ ዘሪቱ ከበደ የተባለች ራሷን ሰማይ የሰቀለች በዝግጅቱ ቀርባ ነበር፡፡ የጥላሁን ገሠሠን ዘፈን በመዝፈኗ ከአንድ አድማጭ የቀረበባትን ቅሬታ በዘለፋ ነበር የመለሰችው፡፡ እኔ ከዘፈንኩ አስተያየት መስጠት የለባችሁም በሚል አድማጩን ክፉኛ ስትወርፈው ሰይፉ አጋፋሪ ነበር፡፡ የሰው ዘፈን እንዲዘፈን ሲያበረታታ የቆየ መሆኑ ራሱም የሚክደው አይመስለኝም፡፡ ሰይፉ በወገነለት ወገን ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ አስተያየት አይቀበልም፡፡ በቃላት ይናደፋል፡፡ አስፈላጊ ከሆነም በጭቃ ቃላት ሰውን ይመርጋል፡፡ የሚደውሉለትን አድማጮች እንዴት እንደሚያንጓጥጥ፣ እንዴት እንደሚሳደብ የተከታተለው ሁሉ ያውቀዋል፡፡ አንድ ሰሞን ነው ትዝ ይለኛል፡፡ አንዲት አድማጭ ትደውልና አስተያየቷን ትሰጠዋለች፡፡ ሙያዋን፤ ማንነትዋንና ስሟን ይጠይቃታል፡፡ መስከረም እንደምትባል ትነገረዋለች፡፡ ያለምንም ማቅማማት “ኦ መስከረም ላይ ነዋ የምትፈነጂው” ብሏታል፡፡ ሌላም ልጨምርላችሁ፡፡ ለጥበብ ሳይሆን ለራሱ ተቆርቋሪ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ፡፡ ታምራት ደስታ የተባለ ዘፋኝ ዝግጅቱ ላይ አቅርቦት ነበር፡፡ ሰይፉ ሲሰቅል ወሰን የለውም፤ ሲጥልም እንደዚያው እሱ ፊት ያላዞረባቸው ዘፋኞች ምንም እንከን ስለማይወጣላቸው ሲክበው አመሸ፡፡ ራሱን ወክሎ ቢያንቆለጳጵሳቸው ደግ ነበር፡፡ ክፋቱ ግን የእሱን ፍላጎት አድማጩ ላይ መጫኑ ነው፡፡ ታምራት በዝግጅቱ ከቀረበበት ጊዜ በኋላ በተላለፉ የሰይፉ ዝግጅቶች (ፕሮግራሞች) ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የታምራት ዘፈኖች የማይቀር ነው፡፡ ሌላ ዘፋኝ የለም ወይ እስኪባል ድረስ የጥቂት ዘፋኞች መስተናገጃ ነው፡፡ የሚፈልጋቸውን ዘፋኞች ሲፈልግ እየደወለላቸው ካልሆነም እንዲደውሉለት እያደረገ ይካካባሉ፡፡ እኔ ሁሌም የሚገርመኝ ሬዲዮ ጣቢያው የመንግሥት ሳይሆን የእርሱ መሆኑን ነው፡፡ ሲፈልግ ጋዜጠኛ፣ ሲፈልግ ጆከር፣ ሲፈልግ የስፖርት ኮሜንታተር፣ ሲፈልግ ሐያሲ፣ ሲፈልግ ተሳዳቢ፣ ሲፈልግ ደረጃ አውጪ ወዘተ. የማይሆነው የለም፡፡ ሰይፉ ሌሎችን ዜማ ኮረጁ ወይም ሰረቁ ለማለት የሞራልም የችሎታም ብቃት የለውምና ከድርጊቱ ቢታቀብ መልካም ነው፡፡ (ዘርዓይ ታደሰ፣ ከአስኮ) በሕዝብ ደስታ የሚቀና ጣቢያ ባለፈው መጋቢት 21 ቀን 2000 ዓ.ም በስኮትላንዷ ኤደንብራ ከተማ ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች በድል መድመቃቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውድድሮቹን በከፊልም ቢሆን ማስተላለፉ የሚያስደስት ነው፡፡ በምልዐት አለማስተላለፉ ግን ከፍተኛ ቅሬታ ማሳደሩ ሳይገለጽ መታለፍ የለበትም፡፡ በስፖንሰሮች አማካይነት የውድድሩ ስርጭት እንደሚያስተላልፉ እየታወቀ፣ በወጣቶች ምድብ በወንዶች ኢብራሂም ጂላ፣ በሴቶች “አዲሳ ኮከብ” ገንዘቤ ዲባባ አሸናፊ የሆኑበትን ውድድር፣ እንዲሁም ተተኪዎቻችን ድል ሲያደርጉ እንዳናይ ማድረጉ በሕዝብ ደስታ የሚቀና ጣቢያ ነው እንዴ? አሰኝቶኛል፡፡ (ሐዲስ ኪዳነማርያም፣ ከአራት ኪሎ) አፀፋው ጥሩ ነው የሰይፉ ፋንታሁን ለምን ይዋሻል? ፕሮግራም በቴዎድሮስ ካሳሁን ሥራዎች ላይ በሰጠው አስተያየት ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ውዝግቡንም የመገናኛ ብዙሃን ወገናዊነትን ባሳየ መልኩ ዘገባ እያቀረቡ ነው፡፡ ይህም የመገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ ላይ ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡ ሰይፉ ፋንታሁን ቴዎድሮስ ላይ በከፈተው ተኩስ አፀፋ እየተሰጠው መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ሰይፉ ፋንታሁን ከኤሜት ማርክ “ይፈለጋል” ፊልምን ኮርጆ ሳለ የሰውን የኩረጃ ሥራ ለማጋለጥ መሞከሩ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ሰይፉም ቴዲም የሰዎችን ሥራዎች ኮፒ ካደረጉ ጥፋተኞች ናችሁ፡፡ ሊባሉ ይገባል፡፡ (አበበ ጌታሁን፣ ከፒያሳ) ውጤታማ እርምጃ ያስፈልጋል ባለፈው ረቡዕ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ቢዝነስና ኢኮኖሚ ገፅ የዋጋ ቁጥጥር ጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ተጠቁሟል፡፡ አሁን ያለው የኢኮኖሚ እድገት በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ያተኰረ በመሆኑ የዋጋ ንረቱን ያባብሰዋል፡፡ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር የኢኮኖሚ እድገቱን ገድቦ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ ስለሆነም መንግሥት የዋጋ ንረቱ ከዚህ የባሰ ቀውስ ውስጥ ከማስገባቱ በፊት ውጤታማ የሆኑ የመፍትሔ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል፡፡ (ሩት ኪዳኔ፣ ከሳሪስ) የግዥ ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን የሥራ ብቃቱም ይፈተሽ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የግዥ ስርዓት መተቸቱን የሚያሳይ ዜና ባለፈው ረቡዕ ሪፖርተር ጋዜጣ ወጥቷል፡፡ ከዜናው እንደተረዳሁት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ጥናት መሠረት ኮርፖሬሽኑ የግዥ መመሪያ የለውም፡፡ ይህም አሰራሩን ለሙስና እንደሚያጋልጠው ዜናው ያትታል፡፡ የኮርፖሬሽኑ አሰራር በአገር ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ አለውና መፈተሹ መልካም ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መብራት በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ትክክለኛውን ግልጋሎት እያገኘ አይደለም፡፡ ለጎረቤት ሃገር የኤሌክትሪክ ሃይል እንሸጣለን መባሉን ሰምተናል፡፡ ከራሳችን አልፈን ለጎረቤት እንተርፋለን እየተባለ ባለበት ይህ ችግር ለምን ተከሰተ? (ቃልኪዳን ዳንኤል፣ ከቦሌ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |