| ዕውቀት ያላቸውን ዲያስፖራዎች መጠቀም |
|
|
| Sunday, 06 April 2008 | |
![]() ሙሉጌታ አስመላሽ ኢትዮጵያዊው ከአገሩ ወጥቶ ብዙ ዓመት ቢቀመጥ እንኳን ቋንቋና ባህሉን እንዲሁም ኢትዮጵያዊነቱን ለመቀየር ይከብደዋል፡፡ እንደ እስያና ሌሎች አገር ዜጎች ቶሎ ከሌሎች ጋር አይዋሃድም፡፡ ኢትዮጵያዊ ውጭ ሲኖር እርስ በርሱ ቢጣላ በአገር ስሜቱ ጉዳይ ግን አንድ በመሆኑ ይህንን ፍቅር፣ ስሜትና ግንኙነት ለአገር ጥቅም ማዋል ይቻላል፡፡ የዲያስፖራው ጥቅም ባብዛኛው የሚታወቀው ለቤተሰቡ በሚልከው ገንዘብ፣ አገሩ ገብቶ በሚያለማው፣ አገልግሎት በሚሰጠውና በንግዱ ተሠማርቶ በመሥራቱ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች እውቀት ያላቸውን ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት እንደድልድይ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ለ3ዐ ዓመታት በሆላንድ የቆዩትና በአሁኑ ሰዓት የድር ፋውንዴሽን አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ አስመላሽ ይዘው የመጡት ብዙም በአገራችን ያልተሠራበትንና የመንግሥትንም ሆነ የኅብረተሰቡን ቀልብ ያልሳበውን የእውቀት ወይም የልምድ ልውውጥን ነው፡፡ ከሚሰሩባቸው ዘርፎች መካከል አካል ጉዳተኛው በስፖርት እንቅስቃሴ ምን ያህል ተሳትፎ አለው የሚለው በአገራችን ብዙም ያልተሠራበት ሲሆን ሆላንዶች በዚህ ጥሩ ልምድ ስላላቸው ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ የዘርፉን የስፖርት ተሳትፎ ለማጐልበት እውቀቱን ከሆላንድ እያመጡ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ኤክስፐርቶችም ከሆላንድ እየመጡ ልምዳቸውን ሲያካፍሉ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ሁለት ኤክስፐርቶች ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ስልጠና እየሰጡ ነው፡፡ እውቀትና ልምድን ለማስተላለፍ ከአፍሪካ አገራት የመጡ ሰዎች በተገኙበት ሆላንዳውያኑ መጥተው ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል ሶሻል ኢንተርኘራይዝ (ማኅበረሰብ አቀፍ የንግድ ተቋም) አሰራር በአገራችን የተለመደ ባይሆንም በአሜሪካና በአውሮፓ ግን እየተሠራበትና አዋጭነቱ እየተነገረለት ያለ ነው፡፡ ከአገልግሎት ሰጪው ለምሳሌ ከዳቦ ቤት፣ ከምግብ ቤት የሚገባኝ ገቢ ለአንድ ሰው ወይም ቤተሰብ ሳይሆን ኅብረተሰቡን ለማቋቋሚያ እንዲውል የሚያደርግ አሰራር ነው፡፡ በምግብ ቤት ወይም በሌላ ተቋም የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ በተለያየ ምክንያት ኅብረተሰቡ ያገለላቸው፣ ከእስር ቤት የወጡ፣ የፆታ ንግድ ሥራ የሚሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህንን አሰራር ወደዚህ በማምጣት ሦስት ..ቡና ቤስት.. የሚሉ ካፍቴሪያዎች ተከፍተው ከኅብረተሰቡ ተገልለው የነበሩና በቀላሉ ሥራ ሊያገኙ የማይችሉ ሰዎች በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ሶሻል ኢንተርኘራይዝ የሚለውን ሃሳብ ኢትዮጵያ አምጥተው ለማስፋፋት ትግል ላይ ነው ያሉት፡፡ ግብረሰናይ ድርጅት ሆኖ ይህንን መሥራቱ በአገራችን ያልተለመደና በሕግ ከለላ የሌለው በመሆኑ አዳጋች ቢሆንም የሶሻል ኢንተርኘራይዝን ሃሳብ የመንግሥትን አካልም ሆነ ኅብረተሰቡን ሊያስተምሩ እንደሚችሉ በማሰብ ሃሳቡን እያራመዱ ነው፡፡ ግብረ ሰናይ ድርጅት ገንዘብ ማፍራት አይችልም የሚለው የሚያስማማ ጉዳይ ቢሆንም ገንዘቡ ለምን ይውላል የሚለው ላይ ቁጥጥር ተደርጐ ሕጐችን ማሻሻል ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ የተለያዩ የንግድ ተቋማትን ከፍተው አካል ጉዳተኞችን፣ መንገድ ላይ ያሉ የቀድሞ ወታደሮች፣ የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከንግዱ በሚገኘው ገቢ ሌሎች ችግረኞችን ለማቋቋም እንዲውል የማድረግ እቅድም አላቸው፡፡ አውሮፓ በተለያዩ መስኮች ላይ የደረሰበትን ደረጃ ለኢትዮጵያ በሚስማማ መልክ በማምጣትና ሃላፊነት በመውሰድ እየሰሩበት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት 16 ሆላንዳውያን ወጣቶች ኢትዮጵያ መጥተው በአፓረንት ሺኘ (የሥራ ላይ ልምምድ) እየሰሩና የስራ ባህላቸውን እያስተማሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ከሆላንዳዊያን ጋር ማገናኘቱም ራሱን የቻለ ሌላው አላማቸው ነው፡፡ እስካሁን ድረስ 52 የሚደርሱ ወጣቶች ኢትዮጵያ መጥተው ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ወደ አገራቸው ሲመለሱም በኢትዮጵያ ስላለው ባህል፣ ሕዝብ፣ ኑሮ ለሆላንዳውያኑ ስለሚያስረዱ ሕዝቡ ስለኢትዮጵያ ያለውን ..ረሃብተኛ.. የሚል አስተሳሰብ የመቀየር ኃይል ይኖራቸዋል፡፡ የአገሪቱን ገፅታ ማስተዋወቅ አንዱ አላማቸው ስለሆነ ሆላንዳዊያኑ ከኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ተብለው ራሳቸውን ያደራጃሉ፡፡ የተለያዩ ኘሮጀክቶችን ቀርፀውም ይሰራሉ፡፡ ውጭ የኖሩበትን ጊዜና የነበራቸውን ግንኙነት ተጠቅመው አገርን ማበልፀግ ከዲያስፖራው የሚጠበቅ በመሆኑም እስካሁን ከ2 ሺህ በላይ ሆላንዳውያንን በኢትዮጵያ በማስተናገድ በሚዲያ፣ በጤና፣ በኢንጅነሪንግና በተለያዩ ዘርፎች እውቀታቸውንና ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ሆላንዳዊያኑ በፋውንዴሽኑ በኩል በመምጣት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኅህበረሰብ አቀፍ ..ሬዲዮ ጅማ.. የሚል እያቋቋሙ ነው፡፡ ዲያስፖራው ምን ሰራ ሲባል ገንዘብ ልኳል፣ ኢንቨስትመንት ውስጥ ተሳትፏል ከሚለው በተጨማሪ እውቀት ማምጣትም አስፈላጊ ነው፡፡ እውቀትና ልምድ የማምጣት ሥራ በመንግሥት በኩል ቢበረታታና ዲያስፖራው በዘርፉ ቢሰራ የዲያስፖራው ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ልምድንና እውቀትን ማምጣት ላይ ሲሰራ የውጭ ዜጐች የራሳቸውን ልምድ፣ ባህልና እውቀት ብቻ አይደለም ይዘው መምጣት ያለባቸው፡፡ የእነሱና የኢትዮጵያ ባህል የሚጋጭ ነው፡፡ ይህንን ለማስማማት ደግሞ ኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ እንደድልድይ ሆኖ የባህል ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ አለመግባባቶችን መፍታት፣ ለኢትዮጵያ የሚመች ሃሳብን በማፍለቅ ለውጭ ዜጐች አመቺ በሆነ ቋንቋ ማቅረብ የኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ ሥራ ነው፡፡ ለውጭ ዜጐች ጉዳዮቻችንን በምናስረዳበት ጊዜ ገንዘብ ለማግኘት ተብሎ ..የለንም፤ ምንም የለንም.. በማለት ራስን የማጣጣል ነገር በአገራችን ይታያል፡፡ ኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ ግን የውጪዎቹን ሃሳብ በቀላሉ መረዳት ስለሚችል ትውልድ አገሩን ዝቅ በማያደርግ መልኩ ሃሳብን በማቅረብ ሊያግዝ ይችላል፡፡ ዲያስፖራው የትውልድ አገሩንም ሆነ በውጭ የኖረበትን አገር ባህል ስለሚረዳ ተራ ድልድይ ሆኖ ሳይሆን በሚያስማማ፣ ሊያሰራ በሚችልና የኢትዮጵያን ገፅታ በሚያጐለብት መልኩ አገሩን ሊጠቅም ይችላል፡፡ የውጪዎቹን ለማሳመን ዲያስፖራው አገር ውስጥ ካለው በተሻለ እድሉ አለው፡፡ ለዚህም የሚረዳው ደግሞ የትውልድ አገሩንም ሆነ በውጭ የሚኖርበትን ባህል ማወቁ ነው፡፡ ፋውንዴሽኑም የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽንን ሆላንድ ከሚገኝ ግብረሰናይ ድርጅት አገናኝቷል፣ ለአይነ ስውራን ማህበር ከሆላንዳዊያኑ ጋር ኔት ወርክ እንዲፈጥሩ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ ይህ የሆነው የፋውንዴሽኑ አመራር የሁለቱንም አገር ባህል በማወቁ ነው፡፡ ዲያስፖራው ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ከዚህም በላይ ሊሰራ እንደሚችል እምነቱ አላቸው፡፡ ለዚህም መንግሥት የዲያስፖራውን ገንዘብና እውቀት ለማምጣት ሁኔታዎች ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ ሞሮኮና ጋናን የመሳሰሉ አገራት የዲያስፖራ ሚኒስትር አላቸው፡፡ ይህን ያደረጉት ዲያስፖራው በገንዘብ የማይተመን ሃብት ስለሆነ ነወ፡፡ በአገራችን ተሰሚነት ያለው ዲያስፖራ ነው እየሰራ/እየተጠቀመ ያለው፡፡ ገንዘብና እውቀት ያለው ዲያስፖራ የመናገር ኃይሉ ላይኖረው ይችላል፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ እነዚህኛዎቹን ጭምር ለማምጣት ያለመ መሆን አለበት፡፡ በአገራችን ዲያስፖራውን አሳታፊ የሆነ የዲያስፖራ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በትውልድ ኢትዮጵያውያን ለሆኑ የሚሰጥ መታወቂያ ..ቢጫ ወረቀት.. ለማግኘት 5ዐዐ ዶላር መክፈል ያስፈልጋል፡፡ 500 ዶላር የሚያወጣ የመታወቂያ ወረቀት በዓለም ላይ የለም፡፡ መታወቂያ የማግኘት ሃሳቡና መንፈሱ ለዲያስፖራው ጥሩ ነው፣ መታወቂያው የኢትዮጵያዊ ስሜቱን ያጠናክርለታል፡፡ ሆኖም 5ዐዐ ዶላር ማስከፈል ተገቢ አይደለም፡፡ አብዛኛውን ዲያስፖራ ለመሳብ ዋጋው ዝቅ ማለት አለበት፡፡ በውጭ ጉዳይ ማኒስቴር የሚገኘው የዲያስፖራ ዴስክም አበረታች አይደለም፡፡ ዲያስፖራው ያለውን ሃሳብ ሲገልፅ ..አዋጅ ወይም ህግ ነው.. በሚል ሰበብ የማሻሻያ ሃሳቦችን አያስተናግድም፡፡ ያለው መንግሥታዊ መዋቅር የዲያስፖራውን ቋንቋ አይናገርም፡፡ ዲያስፖራውን ለመጠቀም ከተፈለገ የዲያስፖራውን ቋንቋ የሚናገር ፖለሲና የዲያስፖራ ልምድ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በሚሊዮን ስለሚቆጠረው ዲያስፖራ ስናወራ የተማረ፣ ያልተማረ፣ ሃብታም ደሃ፣ ታማኝ ያልሆነ ቅዱስ፣ ለመስራት አቅም ያለው የሌለውን ጭምር ነው፡፡ ሆኖም እነዚህን ሁሉ በአንድ አስገብቶ የሚቀረፅ ፖሊሲ ዋጋ አይኖረውም፡፡ የተለየና ሊሰራ ከሚችለው ጋር ማውራት የሚችል ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በሆላንድ የነበሩ ዲያስፖራዎች አገራቸው መጥተዋል፡፡ ለመስራት ይፈልጉ ነበር፡፡ ሆኖም አመቺ ሁኔታ አልተፈጠረላቸውም፡፡ ቢሮክራሲው ሊያሰራቸው አልቻለም፡፡ ከነበሩበት አገር ልምድ ጋርም ይጋጭባቸዋል፡፡ ይህ ከሆላንድ ለመጡት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዲያስፖራ ችግር በመሆኑ ዲያስፖራውን አሳታፊ የሆነ ፖሊሲ አስፈላጊ ነው፡፡ በምሕረት ሞገስ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |