|
Sunday, 06 April 2008 |
ዓሣን በአዲስ ቴክኖሎጂ ለማምረት ጥረት እየተደረገ ነው የአገሪቱን የዓሣ ሃብት ለማሳደግና የዓሣ ግብርናን ለማስፋት አዲስ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የሙከራ ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡ የዓሣ ግብይት ስርዓት ጤናማ እንዳልሆነም ተመለከተ፡፡
ቦሞሣ የተባለው አዲስ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት በተደረገ የባለሙያዎች ውይይት ላይ እንደተጠቆመው፣ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ይህ ቴክኖሎጂ ጠቃሚ ነው፡፡
ቦሞሣ የተባለው ፕሮጀክት በኬንያና በኦስትሪያ ዩኒቨርስቲዎች የጋራ ጥምረት ከ7 ዓመታት በፊት በኬንያ የተጀመረ ነው፡፡ ስሙም የተገኘው ፕሮጀክቱን የጀመሩት ዩኒቨርሲቲዎች የስማቸው የመጀመሪያ ቃላት ጥምረት የተፈጠረ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ዋነኛ አላማ በሰው ሰራሽ በሆነ ዘዴ ዓሣን ማምረት ሲሆን ፕሮጄክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው፡፡
ቴክኖሎጂውን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠራ የተፈለገውም በኬንያ ውጤት በማስመዝገብ ላይ በመሆኑ እንደሆነ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሁለት ጣቢያዎች የሙከራ ሥራው ተጀምሮ አጥጋቢ ውጤት እየተገኘ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዘነበ ታደሠ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ልምዱ ከኬንያ የተወሰደ ሲሆን ቴክኖሎጂውም ወደ አገራችን ገብቷል፡፡ ዓላማ ያደረገው ደግሞ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ነው፡፡ የአመራረት ዘዴውም በ1.8 ሜትር ስኩዌር ከፍታና እና በ1.5 ሜትር ወደታች ርዝማኔ ባለው ሳጥን ውስጥ በአነስተኛ ቦታ የዓሣን ማምረት ያስችላል፡፡ እንደማንኛውም የጓሮ አትክልት ወይም በዶሮ ማርቢያ ሣጥን በግቢ ውስጥ ማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
በዚህ የአመራረት ዘዴ በአንድ አነስተኛ ሣጥን ውስጥ በዓመት 500 ኪሎ ግራም አሣ ማምረት ይቻላል፡፡
"ለገበሬው ተጨማሪ ገቢ ለማስገኘት ቴክኖሎጂው ጠቃሚ ነው፡፡ ገበሬዎች በቀላሉ ይጠቀሙበታል፡፡ በተፈጥሮ የውሃ ሃብት ላይ ያለውን የዓሣ አስጋሪዎች ችግር ይቀንሣል፡፡ በጥቂት ሰዎች የሚሰራ በተለይም ሴቶችንም ዓሣ አምራች እንዲሆኑ ያስችላል" ያሉት ደግሞ የብሔራዊ ዓሣና የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን አሳምነው ገበሬው በዚህ ቴክኖሎጂ የሚያመርተው አሳ ሸጦ ከሚያገኘው ጥቅም ሌላ ለቤተሰቡ ተጨማሪ የፕሮቲን ምግብ እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ 12 በሚሆኑ ትላልቅ ተፋሰሶችና የተለያዩ መጠን ባላቸው 30 ሐይቆች ውስጥ ሁለት መቶ የሚሆኑ የዓሣ ዝርያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ የዓሣ ዝርያዎች ውስጥ 30 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ቢነገርም የተፈለገውን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም፡፡
የአገሪቱ የዓሣ ሃብት በተመለከተም ከወንዞች በየዓመቱ 7ሺህ ቶን ከሐይቆቹ ደግሞ 40ሺህ ቶን ዓሣ የማምረት አቅም እንዳለ የሚገመት ቢሆንም በትክክል ቁጥሩን ለማስቀመጥ የሚቸግር እንደሆነም የቦምሣ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶ/ር ዘነበ አስረድተዋል፡፡
የአገሪቱ የዓሣ አመራረት ዘዴም ችግር እንዳለበትና የዓሣ አስጋሪዎች ዓሣን ለማጥመድ የሚጠቀሙበት መረብ በየጊዜው እየጠበበ ለምግብነት ያልደረሱ አሳዎችን ጭምር ስለሚይዙ በዘርፉ ላይ አደጋ እየተፈጠረ መሆኑንም ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡
አቶ ካሣሁን እንዳስረዱት ደግሞ እንደሚሉት በተለይ የዝዋይና የአዋሣ ሃይቆች ለምግብነት ያልደረሱ ዓሳዎች በስፋት የሚጠመዱ በመሆኑ የዓሣ ምርቱ እየቀነሰ ስለሆነ ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡
በዝዋይ ሐይቅ ያገኘናቸውና ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ ዓሣ በማስገር ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ መስቀሉ ጉቱ (የዝዋይ ሉቄ አሣ አምራቾች ማህበር ሊቀመንበር ናቸው) እንደገለፁት ደግሞ በዚህ ሐይቅ የሚመረት ዓሣ ቀንሷል፡፡ በሐይቁ ከ4ሺህ በላይ የሚገመት ዓሣ አስጋሪዎች ተሰማርተዋል፡፡ ዋነኛ ገቢያቸውም ከዓሣ ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ በሐይቁ ምርት ስለመቀነሱም በቂ ምሣሌ ማቅረብ ይቻላል ያመለከቱት አቶ መስቀሉ፣ ዱሮ የምናጠምዳቸው ዓሣዎች ትላልቅ ነበሩ፡፡ አንዱ አሣ ብቻውን አንድ ኪሎና ከዚያም በላይ ነበር፡፡ አሁን ይህንን ያህል ዓሣ ማግኘት አይቻልም፡፡ በአብዛኛው ትንንሽ ነው፡፡ ከ10 አመት በፊት በሁለት ጀልባዎች የሚገኘው ዓሣ ዛሬ በአስር ጀልባዎች ከሚገኘው ጋር እንደሚመጣጠን ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ችግር የምርቱ መቀነስ ብቻ ሳይሆን ምርቱን ለማግኘት ብዙ ድካም እየጠየቀ መሆኑ ነው፡፡
የአካባቢው ነዋሪ ሕጋዊ የሆነውም ያልሆነውም ዓሣ እያወጣ መሸጡም የችግሩ አንዱ መንስኤ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
በዋጋ በኩልም አምራቹ የተፈለገውን ያህል ተጠቃሚ አይደለም የሚሉት አቶ መስቀሉ፣ ከሰላሳ ዓመት በፊት አርባ የሚሆኑትን አሣዎች በአንድ ብር ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ያኔ ገበያው ብዙ ባይሆንም ጥቅም ያገኙ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን አንዱን መካከለኛ አሣ ለነጋዴዎች በአንድ ብር፣ ፆም በሚሆንበትና ተወደደ በሚባልበት ጊዜ ደግሞ እስከ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ይሸጣሉ፡፡
የዓሣ ዋጋን በተመለከተ ዶ/ር ዘነበ እንደገለፁት፣ በዓሣ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሸቀጦችም ላይ ይታያል፡፡ የንግድ ስልታችን ጥሩ አይደለም፡፡ ገበሬው ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ትክክለኛ የግብይት ሥርዓት አለመከተሉንም አመልክተዋል፡፡ ይህንን ለማስተካከልም ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያሻም አስረድተዋል፡፡ ለዋጋው መወደድ እንደምክንያት የሚቀርቡ ሃሳቦችም አሳማኝ አይደሉም ያሉት አቶ ካሣሁን ደግሞ አዲሱ ቴክኖሎጂ እንዲህ አይነቱን ችግሮች በማስቀረት ከፍተኛ ሚና አለው ብለው ያምናሉ፡፡ በአዲሱ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለውይይት ከኬንያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከቼክ፣ ከጣልያን፣ ከአውስትራሊያ የወጡ የዓሣ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ በዳዊት ታዬ |