Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ የምርት ገበያ አገልግሎቱን ጀመረ
የኢትዮጵያ የምርት ገበያ አገልግሎቱን ጀመረ Print E-mail
Sunday, 06 April 2008
Imageየባህላዊውን የግብርና ምርት ግብይት ሥርዓት ለመቀየር የሚያስችል ዘመናዊ የግብርና ምርት ገበያ መዘርጋቱ፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተገለፀ፡፡

 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በይፋ መጀመሩን ለማብሰር ከዓርብ መጋቢት 26 እስከ 27 ቀን 2000 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የስብሰባ አዳራሽ አገር አቀፍ የውይይት ፎረም በተከፈተበት ወቅት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እንደተናገሩት፣ የግብርና ምርት ግብይት ሥርዓታችን በርካታ ውስብስብ ችግሮች አሉበት፡፡ ዘመናዊ የግብርና ምርት ገበያ መፍጠርም ችግሩን ለማቃለል ትልቅ እርምጃ ነው፡፡

አገልግሎቱን ተግባራዊ ለማድረግ የምርት ገበያ ፕሮጀክት መስከረም 1998 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዓለም አቀፍ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ዓለም ባንክ፣ ዩኤስ አይዲ ኢፋድ፣ ዩኤን ዲፒ፣ ሲዳ ካናዳ እና ዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም ድጋፍ እንዳደረጉ ተገል"ል፡፡

በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ በበኩላቸው የምርት ገበያ ሥራውን የሚጀምረው በውሱን ምርቶች ላይ በመሆኑ በቀጣይ ሁሉም ምርቶች ለማስገባት በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የገበያው መመስረት የአመራረት ጥራትንና በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ችግሮችን በማቃለል ሻጭና ገዢን የሚያገናኝ ስለሆነ በትክክል ተግባራዊ ከሆነ የግብርና ምርት ግብይት ሥርዓቱን እንደሚቀይር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የምግብ ኢንስቲትዩት ቴክኒካዊ የአመራር ድጋፍ ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ግብረ ሃይል በማቋቋም ከተለያዩ አገሮች ልምድ መረጃዎችን በማሰባሰብና በመተንተን ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን በውይይቱ ላይ ባደረጉት ገለፃ በባህላዊው የገበያ ልውውጥ ሂደት አምራቾች ትክክለኛ ዋጋ እንደማያገኙ ጠቁመው ገዢና ሻጭን ፊት ለፊት በማገናኘት የገበያ ውድድር በመፍጠር በኩል የምርት ገበያው ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡ የምርት ገበያ አገልግሎቱን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፋቸውን በቀጣይም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚኖር የጠቆሙት ዶ/ር እሌኒ ገበያው ሰፊ ግንዛቤንና ጊዜን ወስዶ በመሠራቱና ዘመናዊው የምርት ገበያ ችግር ያለበትን ባህላዊው የገበያ ስርዓት የሚፈታ በመሆኑ፣ ከመንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ ድጋፍ በመደረጉና ችግሩን በይበልጥ የሚያውቁትን የግሉን ዘርፍ ተዋናዮች ማቀፉ ለውጤታማነቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በምርት ገበያ አገልግሎት ተሳታፊ እንዲሆኑ በመጀመሪያው ዙር መስፈርቱን አሟልተውና በሲስተሙ ተመልምለው ልምምድ ያደረጉ 62 መሥራች አባላት ያሉ ሲሆን አገልግሎቱ አነስተኛ አቅም ባላቸው አርሶ አደሮች የተገነባ በመሆኑም ሁሉንም አርሶ አደሮችን የማሳተፍ አቅም እንደሚኖረው ዶ/ር እሌኒ ጠቁመዋል፡፡

አገልግሎቱ በተወሰኑ የግብይት ቦታዎችና በጤፍ፣ በስንዴ፣ በበቆሎ፣ በሰሊጥና በቡና ንግድ ላይ እንደሚያተኩር ተጠቅሷል፡፡

በምርት ገበያ አባል የሆኑ ሻጮች በአቅራቢያቸው ለሚገኝ መጋዘን ምርታቸውን በማስረከብ የምርት ደረጃና ዓይነቱን በማረጋገጥ የምርት ማረጋገጫ ሰርተፊኬትና የባለቤትነት ደረሰኝ እንደሚሰጣቸው በዚህም በሚፈልጉበት ጊዜ ሽያጩን ማካሄድ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

የምርት ገበያ አባል የሆነ ገዢ አገልግሎቱን ከሚሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ዳሽን ባንክ ትዕዛዝ በመስጠት በጨረታው ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን በጨረታው ስምምነት ላይ ሲደርሱ በምርት ገበያ አማካይነት የምርት ማረጋገጫ ደረሰኝና የባንክ ቼክ የርክክብ አፈፃፀም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡

ያነጋገርናቸው ተሳታፊ አርሶ አደር እንደገለፁት የገበያው መጀመር ገበያ ተኰር የሆነ ምርት ለማምረት፣ በምን ያህልና በምን ዓይነት ደረጃ የሚለውን እንዲያውቁና ምን ማምረት አንዳለባቸው ለመተንበይ ያስችላቸዋል፡፡ ሕብረት ሥራ ማህበራት በበኩላቸው ሻጩ ማሟላት ያለበትን ደረጃ፣ የምርት ዓይነትና ክፍያ ወቅታዊ መረጃ ለማስተላለፍ ከአርሶ አደሩ ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በቡና ወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ ላኪዎች በበኩላቸው በገበያ ላይ የጥራት ችግር እንዳለና ባዕድ ነገር ሳይደባለቅ ደረጃውን የጠበቀ ምርት በሚፈለገው መጠን ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡


በጨረታ ሂደቱ ተሳታፊ የሚሆኑት የገበያው ሕጋዊ አባላት ሲሆኑ ፍትሃዊ የሆነ ውድድርና መሠረታዊ የቢዝነስ ቁርኝት እንዲፈጥሩ ተከታታይ ስልጠናና ምክክር እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡

የነፃ ገበያ አሠራርን በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ የገበያ ክትትል ቡድን ክትትል እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ የጨረታ ተሳታፊ የሚያደርገውን የአባልነት ወረቀት በጊዜያዊነት፣ በቋሚነት መጠቀምና በቀላሉ ለሌሎች ማስተላለፍ እንደሚቻል የአባልነት ወረቀት የሌላቸው ሻጪዎችም ሆኑ ገዢዎች ተሳታፊ እንደማይሆኑ ሆኖም የአባል ደንበኛ በመሆን ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡

 አገር አቀፍ ፎረሙ ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን አምራቾች፣ ማህበራት፣ የአገር ውስጥ ነጋዴዎች፣ ላኪዎች፣ የኢንዱስትሪ ሸማቾች፣ ከፋይናንስ ትራንስፖርት፣ ኢንሹራንስ፣ ከመረጃ ዘርፎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ለጋሾችና ሌሎች ባለሙያዎች ተሳታፊ ተሳትፈዋል፡፡
በቤዛዊት ሥዩም

 
< Prev   Next >