|
Sunday, 06 April 2008 |
 ዶክተር ግርማ አውግቸው ቤተሰባዊ ግንኙነት የሌላቸው ሕፃናትየኢትዮጵያ የሕፃናትና የቤተሰብ ግንኙነት በወግ አጥባቂነት፣ በፈላጭ ቆራጭነት፣ በቁጥብነት፣ መቀራረብ በሌለበትና በከፋ አካላዊ ቅጣት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም ግንኙነት ሕፃናት ለስብዕናና ለዕድገታቸው ክህሎትና በራስ መተማመንን ሳያዳብሩ እንዲያድጉ የሚያደርጋቸው መሆኑን በኢጣሊያን የልማት ትብብር የሕፃናትና የሴቶች ፖሊሲ ኤክስፐርት አስታወቁ፡፡
ከመጋቢት 22 ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ መጋቢት 28 ቀን 2000 ድረስ የተከበረውን የሚሌኒየሙን የሕፃናትና ቤተሰብ ሣምንትን ምክንያት በማድረግ ኤክስፐርቷ ወይዘሮ አምሳለ ንጋቱ ባዘጋጁት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንዳመለከቱት፣ ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙነት የሌላቸው ሕፃናት በአካላዊ፣ በስነ ልቦናዊ፣ በማኅበራዊ ግንኙነታቸውና በትምህርታቸው ላይ ችግር ይፈጥርባቸዋል፡፡
ከዚህም ሌላ የቤተሰብ አለመግባባት፣ ድህነትና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ለሕፃናት ጥቃትና በደል መጋለጥ ምክንያቶች እንደሆኑ፤ ጥቃት ሲባልም አካላዊ ብቻ ሳይሆን ቸል መባልን፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ ፍቅር፣ ምቾት፣ ደስታ ወዘተ አለማግኘትን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡
የቤተሰብና የሕፃናት ግንኙነት የሚጀምረው ሕፃኑ በእናቱ ማህፀን ውስጥ እንዳለ ነው፡፡ በዚህም ወቅት የእናቱንና የአባቱን ድምፅ ይለያል፡፡ እንደተወለደም እናቲቱ ስትንከባከበው፣ ስታጥበውና ስታጠባው ማውራት አለባት፡፡ ምክንያቱም ያዳምጣታል፡፡ አእምሮው እያደገ የሚሄደውም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ እነዚህን የዕድገት ደረጃዎች ቤተሰብ መረዳት እንደሚኖርበት የግድ ይላል፡፡
ከዜሮ እስከ ሰባት ዓመት ያለው የዕድገት ደረጃ ሕፃናት የመጀመሪያ ስብዕናቸው የሚመሠረትበት ነው ያሉት ኤክስፐርቷ፣ በዚህ ጊዜ ያስያዝናቸውን ነገሮች ሁሉ በሕይወታቸው ይዘው እንደሚሄዱ፣ ለወደፊቱም ብቃታቸውና ማንነታቸውም ወሳኝነት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
ሁለተኛው የጉልምስና ዘመን ኃይልና ግጭት የሚከሰትበት የዕድገት ደረጃ ነው፡፡ ስለሆነም ቤተሰብ በጥንቃቄና በትዕግሥት ይዞት መሄድ ይኖርበታል፡፡ ቤተሰብ ከልጆቻቸው ጋር ሃሳብ በመለዋወጥ፣ በመነጋገርና በመወያየት ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ቀዝቃዛና ግልጽነት የጎደለው ግንኙነት ግን አለመግባባትን ይፈጥራል፡፡
ሕፃናት ሲበረታቱ፣ በችግሮቻቸው ዙሪያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲወያዩ፣ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ዕድል ሲሰጣቸው፣ ሃሳባቸውን በነፃ ሲገልጹ፣ አብሮ የመጫወትና የመዝናናት ጊዜ ሲኖራቸው ካደጉ በኋላ በሕይወታቸው ዘመን አመለካከታቸው የሰፋ፣ ጠንካራ፣ ነጻና ብቁ ዜጋ ይሆናሉ፡፡
ወይዘሮ አምሳለ እንዳመለከቱት፣ ሕፃናት የስብዕና ዕድገታቸው የተሟላና የተስተካከለ እንዲሆን በቤተሰብ ውስጥ በደስታ፣ በፍቅር ወዘተ. ማደግ ይኖርባቸዋል፡፡ በቤተሰብ ቀውስ የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች ሕፃናት ሲሆኑ ቀጥሎም በሀገርና በሕብረተሰብ ላይም በርካታ ችግሮችን ያስከትላል፡፡ የቤተሰብ ቀውስ መንስኤውም ያልተጠና የጋብቻ ውጤትና የወላጆች በሞት መለየት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የቤተሰብን ጉዳይ ብቻ የሚከታተል አንድ አካል ማቋቋም፣ ከጋብቻ በፊትና በኋላ ወይም በትዳር ውስጥ እንዳሉ የምክር አገልግሎት የሚሰጥበትን መንገድ ማመቻቸትና ለሕፃናት እንደየዕድገታቸውና እንደየብስለታቸው መጠን ኃላፊነትን መስጠት የቤተሰብን ቀውስ ለመከላከል መፍትሄ መሆኑን የኤክስፐርቷ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
ለሕብረተሰቡ በሕፃናት አስተዳደር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማዳበሪያ መስጠት፣ ትምህርት ቤቶችም የሕፃናት መብትና ግዴታዎችን እንዲሁም የቤተሰብ ኃላፊነትን የሚያመላክት ትምህርት እንዲያስተምሩ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዶክተር ግርማ አውግቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን ተመራማሪና መምህር "ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ" በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጥናታዊ ጽሁፍ "አንድ ሕፃን ቋንቋ የሚለምደው ከአንድ እስከ ስድስት ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ነው፡፡ ከስድስት እስከ 12 ዓመት ባለው ዕድሜ ደግሞ መጀመሪያ በለመደው ቋንቋ ላይ ቃላትን የሚያዳብርበት ሲሆን ከ12 ዓመት በላይ ግን ጥሩ የቃላት ችሎታና ተናጋሪ ወይም የአፍ መፍቻ ቋንቋው በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝበት ነው" ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ከ86 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች እንዳሉ ከእነዚህም መካከል ወደ 24 የሚጠጉት ቋንቋዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋነት እንደሚያገለግሉ፣ እስከ 29 የሚጠጉ ቋንቋዎች ደግሞ ከ10 ሺህ በታች ተናጋሪዎች እንዳሏቸው፣ ከአንድ መቶ በታች ተናጋሪዎች ያሏቸው ቋንቋዎችም እንዳሉ ዶክተር ግርማ አስታውቀዋል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በአብዛኞቹ ቅድመ ትምህርት ቤት ወይም መዋዕለ ሕፃናት ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መናገር እንደወንጀለኛ የሚታዩበት ጊዜ እንዳለ፣ ይህ ዓይነቱም አካሄድ በሕፃናቱ ስነልቦና፣ አስተዳደግና አመለካከት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አስገንዝበዋል፡፡
አቶ ጌታቸው በለጠ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት በበኩላቸው "የሕፃናት የንባብ ባህል" በሚል ርዕስ እንዳመለከቱት ለልጆቻችን በቂና ዕድሜያቸውን የሚመጥን መጽሐፍ ተጽፏል ለማለት አያስደፍርም፡፡
በእያንዳንዱ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ለሕፃናት አገልግሎት የሚውል የንባብ ማዕከል እንዲቋቋም ቢደረግ ሕፃናት የንባብ ፍላጎታቸው እያደገ እንደሚሄድና የሕፃናት ፓርላማ ውይይት ለማድረግ እንደሚያስችላቸውም አስረድተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ በዓመት አንድ ቀን የመጻሕፍት ስጦታ ቀን ቢሆንና በዚህም ቀን ሕብረተሰቡ ለሕፃናት የሚሆኑ መጽሐፍትን በስጦታ በያቀርብ መልካም መሆኑንና ለዚህም እውን መሆን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡ በታደሰ ገብረማርያም |