| የዱከም አርሶአደሮችና አስተዳደሩ... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
የዱከም አርሶአደሮችና አስተዳደሩ በመሬት ጉዳይ እየተወዛገቡ ነው
በኦሮሚያ ክልል አቃቂ ወረዳ በጎቤቻ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች "የምንገብርበትንና ካርታ የተሰጠንን ቦታ የዱከም ከተማ አስተዳደር በግዳጅ እየወሰደብን ነው" ሲሉ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ "ቦታው የመንግሥት በመሆኑ ለልማት በፈለገው ጊዜ ይወሰዳል" ሲል አስተዳደሩ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ከዱከም ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በገደራ ሆቴል ገባ ብሎ ከኮራ ማርያም ሥር የሚገኙት የጎቤቻ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች "ቦታው ለልማት ተፈልጓል" በማለት ያለምንም ማስረጃ መሬታቸውን እንደወሰዱባቸው ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች በመደራጀት ፈቃድ ማውጣታቸውንና በ20ሺ ካሬ ሜትር ላይ የሚገኘውን ድንጋይ (ካባ) በማውጣት እየፈጩ ለመሸጥ ማሽኑን ከገዙ በኋላ መሬቱን መነጠቃቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስተዳደሩ ፈቅዶ የሰጣቸውን ቦታና ካርታ ደስ ባለው ጊዜ "ካርታውንና ፈቃዱን ሰርዤዋለሁ" ማለቱን የገለፁት አርሶ አደሮቹ፣ ቦታውን መንግሥት ለልማት የሚፈልገው ከሆነ ተገቢውን የካሳ ክፍያ ከፈፀመና ተለዋጭ ቦታ ከሰጠ በኋላ መሆን ሲገባው ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ቅድመ ዕውቅና ይህን መፈጸሙ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡ "ቦታው ለእኛ ተሰጥቷል፡፡ ባስቸኳይ እቃችሁን አንስታችሁ ከዚህ ሂዱ" በማለት አጥራቸውን በማፈራረስ በካርታና በፈቃድ የተሰጣቸውን ቦታ ሊነጥቃቸው የመጣውን አፍራሽ ግብረሃይል፣ "ይህ የእኛ ህጋዊ ቦታ ነው፡፡ ማፍረስም ሆነ ምንም ነገር መስራት አትችሉም፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችላችሁ ምን ማስረጃ አላችሁ?" ብለን በመጠየቃችን በዋስ መለቀቃቸውን አርሶ አደሮች አብራርተዋል፡፡ የድንጋይ ኢንቨስትመንት ለኢንቨስተር እንደማይሰጥ አቅም የሌላቸው አርሶ አደሮች በማኅበር ተደራጅተው እንዲሰሩ የሚፈቀድላቸው መሆኑ በማስገንዘብ የኦሮሚያ መንግሥት መከልከሉን የገለጹት አርሶ አደሮቹ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ይህንን አሰራር ሊያስተካክልላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ "ቦታው የመንግሥት በመሆኑ ለልማት በፈለገው ጊዜ ሊወስደው ይችላል፡፡ በመሆኑም የኦሮሚያ መንግሥት ለሚያሰራቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶችና የመስኖ ሥራዎች ሲባል በቦታው ላይ የድንጋይ ምርት እየፈጨ ለፕሮጀክቶቹ እያቀረበ ነው" በማለት ምላሽ የሰጡት የአቃቂ ወረዳ አስተዳደር አቶ ደበሌ ቀበታ ናቸው፡፡ ቦታውን በዋናነት የፈለገው የኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ መሆኑን የገለፁት አቶ ደበሌ፣ ለአርሶ አደሮቹ ካሳ እንዲከፍል ትዕዛዝ መተላለፉን ገልፀዋል፡፡ ለአርሶ አደሮቹ ሁለት አማራጭ እንደተቀመጠላቸው ማለትም በአካባቢው በተወሰነ ቦታ ላይ ማኅበሩ ሥራውን እንዲቀጥል፣ በተወሰነ መልኩ ደግሞ መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ወይም ሌላ ሰፋ ያለ የድንጋይ ምርት የሚያካሂዱበት ተመጣጣኝ መሬት እንዲሰጣቸው የሚል መሆኑን አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡ "እነዚህን ለምን እንደ አማራጭ ማየት እንዳልፈለጉ አላውቅም፡፡ መንግሥት ካርታ ከሰጠም በኋላ ቢሆን ለልማት ከፈለገው ሊወስድ ይችላል" ያሉት አቶ ደበሌ አርሶ አደሮቹ የታሰሩት ሥራ አንዳይሰራ ድንጋይ በመወርወር በማወካቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |