| ከበልግ ዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
ከበልግ ዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የመጠጥ ውሃ ችግር አይከሰትም
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን የሚያመርተውና የሚያቀርበው የውሃ ምርት አለመቀነሱን የባለሥልጣኑ የማስታወቂያና የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ሀላፊ አቶ ጌትነት ገሠሠ ለሪፖርተር ጋዜጣ አስታወቁ፡፡ በአቶ ጌትነት ገለፃ መሰረት በበጋው መራዘም ወይንም በበልግ ዝናብ እጥረት ምክንያት የባለሥልጣኑ በሚያመርተው የውሃ ምርት ላይ ችግር አልተከሰተም፡፡ "እንደውም ባለሥልጣኑ በቀን ከሚያመርተው የ235 ሜትር ኩብ የውሃ ምርት ወደ 256ሺ ሜትር ኩብ አሳድጓል" ሲሉ አቶ ጌትነት ገልፀዋል፡፡ በማያያዝም በበልግ ዝናብ እጥረት ምክንያት በግድቦች ውስጥ የውሃ እጥረት አለመከሰቱን ገልፀዋል፡፡ "ግድቦች እስከመጪው ክረምት ድረስ የሚቆይ በቂ ውሃ ይዘዋል" ሲሉ አቶ ጌትነት አስታውቀዋል፡፡ ሀላፊው "ይህ ማለት ግን በአዲስ አበባ የውሃ እጥረት የለም ማለት አይደለም በማለት በከተማው ውስጥ የውሃ እጥረት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ የከተማው የውሃ እጥረት ለረዥም ጊዜ የቆየ ከመሆኑ ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማው የሚታየው የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኮንስትራክሽንና የኢንቨስትመንት መጨመር፤ የውሃ እጥረቱን እንዳባባሰው አቶ ጌትነት አብራርተዋል፡፡ በዚህም በውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ክፍተት መፈጠሩንና በአንዳንድ የከተማው ክፍሎች ውሃ በፈረቃ እየተሰራጨ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የከተማውን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ እቅድ በዘንድሮ በጀት አመት ሀምሳ ሦስት የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ መጀመሩንና ቁፋሮው ሲጠናቀቅ 46 ሺ 380 ሜትር ኩብ ውሃ ማግኘት እንደሚቻልና የአንድ ሚሊዮን ህዝብ የውሃ ፍላጎት እንደሚሸፈን አስታውቀዋል፡፡ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ ትግበራም መጀመሩን አቶ ጌትነት ገልፀዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |