| ባህልና ቱሪዝም፣ ሞኖ 2000 እና... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
ባህልና ቱሪዝም፣ ሞኖ 2000 እና ማስታወቂያ ሚኒስቴር በፎቶ ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዲጅታል ፎቶግራፍ ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ያነሷቸው ፎቶግራፎች ከመስሪያ ቤታቸው እውቅና ውጭ በሞኖ 2000 እና በማስታወቂያ ሚኒስቴር እንደተወሰደባቸው ገለፁ፡፡ በአሰራር ላይ አንዳንድ ችግሮች መከሰታቸውን ያመኑት የሞኖ 2000 ማስታወቂያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ እስክንድር አሰፋ ሁለቱ ተቋሞች ተነጋግረው ከተስማሙ ስህተቱን ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዲጅታል ፎቶግራፍ ባለሙያ የሆኑት አቶ መታፈሪያ አየለ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት እርሳቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው ያነሷቸው የብሄር ብሄረሰብ ፎቶዎች ከመስሪያ ቤታቸው እውቅና ውጭ በህገ ወጥ መንገድ ታትሞ በቴዎድሮስ አደባባይ እንዲሰቀል ተደርጓል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦቹ ፎቶ ለንግድ ትርዒት ኤግዚቢሽን እንዲቀርብ ታስቦ ሞኖ 2000 የማስታወቂያ ድርጅት እንዲያሳትም ተሰጥቶት እንደነበር የጠቆሙት አቶ መታፈሪያ ኤግዚቢሽኑ ከታየ በኋላ ግን ሞኖ 2000 ለባህልና ቱሪዝም ሳያሳውቅ የብሄር ብሄረሰቦቹን ፎቶ በመጠቀም ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ቢል ቦርድ እንደሰራለት አስታውቀዋል፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴርም ፎቶዎቹን ራሱ የሰራ አስመስሎ እንዳቀረበና ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር እውቅና እንዳልሰጠ የፎቶ ግራፍ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ "ማስታወቂያ ሚኒስቴር በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተነሱትን ፎቶዎች ከሞኖ 2000 ወስዶ ቢል ቦርድ ሲያሰራ ለግለሰቦቹም ሆነ ለመስሪያ ቤቱ ህጋዊ በሆነ መንገድ አላሳወቀም" ያሉት አቶ መታፈሪያ ጉዳዩ ለምን እንደተፈፀመ ለመጠየቅ ወደሚመለከተው ክፍል ሲሄዱም ዛቻ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ ሌላው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዲጅታል ፕሮሞሽናል ፊልም አዘጋጅ አቶ ውብአለ የሺጥላ በበኩላቸው ማስታወቂያ ሚኒስትርና ሞኖ 2000 በመተባበር በቴዎድሮስ አደባባይ በሰቀሉት ቢል ቦርድ ላይ 21 ፎቶዎች የአቶ መታፈሪያ፣ 12 ደግሞ የእርሳቸው ሥራ መሆናቸውን ጠቁመው ለሰሩት ሥራ ተገቢው እውቅና ሳይሰጥ በአደባባይ መዋሉ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡ የቢል ቦርድ ሥራ ሲከናወን መስሪያ ቤታቸውም ሆነ ባለሙያዎቹ አለመጠየቃቸውን የገለፁት አቶ ውብሸት ሞኖ 2000 የማስታወቂያ ድርጅት እጁ ላይ ያገኘው ፎቶ ለማስታወቂያ ሚኒስትር አሳልፎ ሲሰጥ ማስታወቂያ ሚኒስትርም ፎቶግራፎቹን ራሱ ሰርቶ ያወጣ አስመስሎ እንዳቀረባቸው አስረድተዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ባለሙያዎች ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች አንስተን ያነጋገርናቸው የሞኖ 2000 ማስታወቂያ ድርጅት ሜኔጂንግድ ዳይሬክተር አቶ እስክንድር አሰፋ በበኩላቸው በአሰራር ላይ አንዳንድ ችግሮች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ጠቁመው ማስታወቂያ ሚኒስቴርና ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ከተስማሙ በስምምነቱ መሰረት ተፈጠረ የተባለውን ችግር ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸው ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ክፍያ የተቀበለው ለቢል ቦርዱ ሥራ እንጂ ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ ላገኘው ስዕል አለመሆኑን የገለፁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ቢልቦርዱ ከመሰራቱ በፊት ፎቶግራፎቹ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር መሆናቸውን መስሪያ ቤቱን ማነጋገር እንደሚያስፈልግ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለፃቸውን፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴርም ሁለታችንም የመንግሥት ተቋም ነን እንነጋገርበታለን የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው አብራርተዋል፡፡ ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኙትን ፎቶ ለማስታወቂያ ሚኒስትር የሰጡትም ሁለቱም ተቋሞች የአገር ገጽታ የሚገነቡ ናቸው የሚል እምነት ስላደረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሞኖ 2000ን ወክለው የቢል ቦርዱን ሥራ ሲከታተሉ የነበሩት ወ/ሪት ዛህራ እስማኤል በበኩላቸው ሞኖ 2000 ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚያሰራውን ቢል ቦርድ በጨረታ ሲያሸንፍ ስዕሎቹን የማቅረብ ኃላፊነት የወደቀው በደምበኛው ላይ መሆኑ ቢገለፅም ሥራው ከተጀመረ በኋላ ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዲዛይኑንና ፎቶግራፎቹን ማምጣት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሁለቱ ተቋሞች ለአንድ ዓላማ የሚሰሩ መሆናቸውን እሳቤ በማስገባት የባህልና ቱሪዝም ሚኒሰትርን ፎቶግራፎች መጠቀማቸውን ተናግራለች፡፡ ድርጅቱ ክፍያ የተቀበለው ለቢልቦርዱ ሥራ ብቻ መሆኑን ወ/ሪት ዛህራ ገልጸዋል፡፡ "ድርጅታችሁ የሌላ ተቋምን ፎቶ ግራፎች አውጥቶ ለሌላ ወገን ለመስጠት እንዴት ድፍረቱን አገኘ?" ለሚለው ሲመልሱም "ረማስታወቂያ ሚኒስትርሪ ከባህልና ቱሪዝም ጋር ተነጋግረናል፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበናል ስላሉን ነው" ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉትን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ አቶ ጌታቸው ዘሩን በስልክ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |