Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ...
ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ... Print E-mail
Wednesday, 09 April 2008
ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የተከሰሱ የዋስትና መብት ተከለከሉ

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከ158 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ወርቅ አጭበርብረዋል በማለት የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 29 ቀን 2000 ዓ.ም ክስ የመሠረተባቸው 21 ተከሳሾች የዋስትና መብት ተከለከሉ፡፡

በሁለት መዝገብ የቀረቡት እነዚሁ ተከሳሾች በእያንዳንዱ ስድስት፣ ስድስት ክሶች የቀረበባቸው ሲሆን በአንደኛው የክስ መዝገብ 14 የሰውና 27 የሰነድ ማስረጃዎች፣ እንዲሁም በሌላኛው የክስ መዝገብ 34 የሰው፣ 42 የሰነድ፣ 3 የፎቶ ግራፍና 6 ኤግዚቢት ማስረጃዎች ቀርቦባቸዋል፡፡

በአንደኛው የክስ መዝገብ የተከሰሱት ሰባት የብሔራዊ ባንክ ሠራተኞችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አራት የጂኦሎጂካል ሰርቨይ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተጣለባቸውን ሥልጣን (የሥራ ኃላፊነት) በመጠቀም በጋራም ሆነ በተናጠል በአደራ ሊጠብቁትና ሊከላከሉት የሚገባውን የመንግሥት ጥቅም የሚጐዳ ህገወጥ ተግባር በመፈፀም በግብረ አበርነት በፈፀሙት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ አስማረ አያሌው ደስታ (ያልተያዘ) ለተባለ ተካሳሽ ከህዳር 3ዐ ቀን 1998 እስከ ሚያዚያ 27 ቀን 99 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ቀናትና ወራት መንግሥት ያለ ችግር በሕግና ሥርዓት የሚመራ የወርቅ ግብይትና ወጪ ንግድ ስርዓትን በመዘርጋት ሀገሪቱ ከወርቅ ሐብት ዘርፍ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሪ ይበልጥ ለማሳደግ ያለውን እቅድና ፍላጐት እውን ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ማደናቀፋቸውን ያትታል፡፡

የወርቅ መመሪያ ቁጥር ጂቲ 001/2005 አንቀፅ 3"1"፣6፣7 ነሐሴ 19 ቀን 97 ዓ.ም የተሰጠ ኮሚቴ ውሳኔ መጋቢት 2ዐ ቀን 96 ዓ.ም እና መስከረም 10 ቀን 97 ዓ.ም የድርድር ስምምነትና በፍትሐብሔር ሕግ መሠረት ስለሕጋዊና የታደሰ የወርቅ ንግድ ፈቃድ ለባንኩ ስለሚቀር ከ1 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ መጠን፣ ወርቁ ስለተመረተበት ቦታ መግለጫ፣ ለሚቀርበው ወርቅ መጠንና የጥራት ልዩነት 20 በመቶ ዋስትና መያዢያ፣ 100 ኪ.ግ ወርቅ ሲሞላ ወደ ውጭ ስለሚላክበት፣ የተመረመረ ወርቅ በአጃቢ ወደ ባንክ ስለሚቀርብበት፣ ተመርምሮና ታሽጐ የሚላከው ወርቅ እሽጉ ተከፍቶ ስለሚታይበትና ርክክብ ስለሚፈፀምበት፣ አቅራቢው ማመልከቻ ስለሚያቀርብበት ሁኔታ የተቀመጡትን የአሠራር መመሪያዎችና ድንጋጌዎችን ወደ ጐን በመተው፣ በመሻርና በመቃረን፣ ለባንኩ ወርቅ እንዲያቀርብ ፈቃድ በመስጠት ተዋውለዋል ይላል፡፡

አያይዞም ያልታጀበ፣ ያልተመዘነ እሽጉ ተከፍቶ ወርቅ ለመሆኑ ያልታየና ከተመረመረ ውሎ አድሮ ወርቅ ተብሎ የቀረበን ባዕድ ብረታ ብረት ወርቅ አስመስሎ በመረከብ ሙሉ ክፍያ እንዲፈፀም በማድረግ፣ የተመረተበትን ቦታ የሚገልፅ ማስረጃ ሳይቀርብ የሻኪሶ አካባቢ የደለል ወርቅ እንደሆነ የሀሰት መግለጫ በማቅረብና ሀሰተኛውን መግለጫ ተቀብሎና ወርቅ መሆኑ ሳይረጋገጥ የክፍያ ሂሣብ እንዲዘጋጅ በማድረጋቸው ተከሰዋል፡፡

አቶ አስማረ አያሌው ደስታ የተባለው ተከሳሽ ሕጋዊና የታደሰ የወርቅ ንግድ ፈቃድ ሳይኖረው ሕጋዊ የወርቅ ነጋዴ በመምሰል ከባንክ በወሰዳቸው 29 ሳጥኖች ውስጥ በድምሩ 597084.8 ግራም ባዕድ ብረታ ብረት ሞልቶ በሀሰት ማሸጊያ በማሸግና ሀሰተኛ የወርቅ ጥራት ማረጋገጫ ጭምር ለባንኩ በማቅረብ ብር 95 ሚሊዮን 537 ሺህ 413 ብር ከ89 ሣንቲም የሆነ የመንግሥት ገንዘብ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ ተከሷል፡፡

ይኸው ተከሳሽ (አስማረ አያሌው) የማይገባ ብልፅግና ለማግኘት ዘመዱን የአቶ መስፍን ወልዴ ዜናን ፎቶ ግራፍ በመጠቀም ነጋዴ ሳይሆን ነጋዴ፣ ስሙም ከፍ ያለው ዑመታ ጆቴ እንደሆነና መታወቂያ እንዲያወጣ በማድረግ የላኪነት ንግድ ፈቃድ በማውጣት በከባድ አታላይነት ወንጀል ሁለቱም መከሰሳቸውን ይጠቁማል፡፡

ተከሳሹ (አስማረ አያሌው) በተለያዩ ጊዜያት ራሱን ከፍ ያለው ዑመታ ጆቴ፣ ኩራባቸው ዑመታ ጆቴና ከበደ ዑመታ ጆቴ በማለት ሦስት የሀሰት ስሞችን እያለዋወጠ የራሱንና የሌላ ሰው ፎቶ ግራፍ እየለዋወጠ በመጠቀምና በሀሰተኛ ስሙ ሀሰተኛ የሆነ የንግድ ፈቃድና የቀበሌ መታወቂያ በማቅረብ፣ ከፍያለው ዑመታ ጆቴ የሚለውን ስሙን ኩራባቸው ዑመታ ጆቴ ለሚለው የሀሰት ስሙ ውክልና ስልጣን የሰጠ በማስመሰል እውነተኛ አስመስሎ በማቅረብ አታሎ በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱና ለራሱ ህገ ወጥ ጥቅም ለማካበት ከባድ የአታላይነት ወንጀል ፈፅሟል፡፡

በሌላው የክስ መዝገብ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች "የደለል ወርቅ ተረክበናል" በሚል ያቀረቡትን ሪፖርትና የክፍያ ጥያቄ የወጪ ምንዛሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ በማፅደቅ መሐመድ አወል ለተባለው ወርቅ አቅራቢ በስድስት ዙሮች ላቀረባቸው ብረታ ብረቶች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፈል በማስደረጉ መከሰሱን ያስረዳል፡፡

በባንኩ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ይሠሩ የነበሩ ተከሳሾች ወርቅ አቅራቢ ነኝ ባዩ መሀመድ አወል ሕጋዊ የሆነ ፈቃድ ይኑረው ወይም አይኑረው ሳያረጋግጡ አስር ሣጥን ሰጥተውት 13 ሣጥን ሲያመጣ 3ቱ ከየት መጣ ሳይሉ "የደለል ወርቅ ተረክበናል" በማለት ሂሳቡ እንዲከፈል በማድረጋቸውና በፈፀሙት የመንግሥት ስር በሚያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ከፍተኛ ኃላፊነት ወርቅ አቅራቢው (መሀመድ አወል) ፈቃድ ያለው መሆኑን ያቀረበውን ወርቅ መርምረው ያለአጃቢ በአስመርማሪው እጅ በመላክና የአሠራር ክፍተት በመፍጠራቸውና የመንግሥትን ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል መከሰሱን ያስረዳል፡፡

አቶ አብዱል ሽኩር መሀመድ ሶፋም ህገ ወጥ ጥቅም ለሌላ ሰው ለማስገኘት አስቦ ታናሽ ወንድሙን ሙደሲር መሀመድ ተጠርጥሮ እስር ላይ በነበረበት ወቅት ይኖርበት ከነበረባት ዛምቢያ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መሀመድ አወል/ሙከሚል ሸሪፍን/ ወደ ሌላ አገር ካልሄደ ለሙደሲር ጥሩ አይደለም በሚል ሱልጣን መሀመድ ከተባለ ወንድሙ ጋር ተመካክረው ስሙን ሐሰን አብደላ በማለት ከኬንያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ሁኔታዎችን አመቻችቶ አዲስ አበባ ሲመጣ መያዙን በመጥቀስ የመንግሥት ሰነድ አመሳስሎ ማዘጋጀት በሚል የሙስና ወንጀል መከሰሱን ይገልፃል፡፡

የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ዘርዘር ያለ ክስ የቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን የክስ መግለጫና አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎች ዝርዝር ለሚያዚያ 10 ቀን 2000 እንዲያቀርቡ አዝዞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታምሩ ጽጌ
 
< Prev   Next >