Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 08th
Home arrow Sections arrow በወንዶ ገነት በተቀሰቀሰ ግጭት...
በወንዶ ገነት በተቀሰቀሰ ግጭት... Print E-mail
Wednesday, 09 April 2008
በወንዶ ገነት በተቀሰቀሰ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ተገደሉ

መኖሪያ ቤቶችና ተቋማት ተቃጠሉ


በደቡብ ክልል በወንዶ ገነት ወረዳ በጉጂ ኦሮሞዎችና በሲዳማ ብሄረሰቦች መካከል ሰሞኑን በተፈጠረ ግጭት 23 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው፣ ንብረት መውደሙና በርካታ ነዋሪዎች ቀዬአቸው ጥለው መሰደዳቸው ተገለፀ፡፡ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ልኮ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጿል፡፡

መጋቢት 26 ቀን ማለዳ ላይ በተፈጠረው በተኩስ የታጀበ ግጭት 23 ሰዎች መገደላቸውን የጉጅ ኦሮሞዎች አባገዳ አፈጉባኤና የብሄረሰቡ ሕገመንግስታዊ የመብት ጥያቄ የሕዝብ ተወካይ አቶ መንገሻ ቲቦ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መንገሻ ገለፃ ለአመታት የጉጅ ኦሮሞዎች በአባገዳቸውና በወኪላቸው አማካኝነት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመማር ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ይህም የሆነው በወረዳው አብላጫው ነዋሪዎች የጉጅ ኦሮሞዎች በመሆናቸው ነው፡፡

ከሶስት ወር በፊት አዋሳ ላይ የጉጅ ኦሮሞዎችና የሲዳማ ብሔረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የሁለቱም ክልል ፕሬዚዳንቶች ሁለቱም ህዝቦች ተስማምተው በአንድነት እንዲኖሩ፣ ወረዳዋ ልዩ ወረዳ እንድትባልና ሁለቱም ብሔረሰቦች በየራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ከስምምነት ተደርሶ እንደነበር አቶ መንገሻ አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስምምነቱ መሰረት ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊት ግጭቱ መፈጠሩን አቶ መንገሻ ያስረዳሉ፡፡ ሲያብራሩም መጋቢት 21 ቀን 2000 ዓ.ም የጉጅ ኦሮሞዎች የአረፋ በዓል ሲከበር በድርብ የኦህዴድ ምስረታ 18ኛ ዓመት ይከበር ነበር፡፡ በበዓሉ ላይ የኦሮሚያና የኦህዴድ ባንዲራ በወንዶ ገነት ከተማ ይሰቀላል፡፡

በበዓሉ ላይ ለተሰበሰው ህዝብ የሁሉም ክልል አመራሮችና መንግሥት የወሰኑትን ውሳኔ እንደሚያከብሩ የጉጅ ኦሮሞዎች በዘፈን፣ በጭፈራና በፉከራ በተደጋጋሚ ያስተጋቡ ነበር፡፡

ከምርጫው ጋር በተያያዘ "ኦሮሞ ስለሆንን ኢህአዴግ /ኦህዴድን እንመርጣለን፤ ምረጡ" የሚል መልዕክትም ይተላለፍ እንደነበር በሥፍራው ከተገኙት ታዛቢዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ አቶ መንገሻ እንደሚሉት በዓሉ በድምቀት ተከብሯል፡፡ ብሔረሰቦች በአንድነት ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ መሪ ድርጅታቸው ኦህዴድ በመሆኑ እንዲመረጥ ቅስቀሳ ተላልፏል፡፡ ይህም ዝግጅት መጋቢት 26 ቀን 2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፏል፡፡

"ፀቡ የተጀመረው ከበዓሉ ፍፃሜ በኋላ ነው" ይላሉ አቶ መንገሻ፡፡ "ከበዓሉ ፍፃሜ በኋላ ወሻ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ከበዓል የሚመለሱ ላይ የድንጋይ ውርወራ ተጀመረ በቀጣይም ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ አለማየሁ ጅቦ የሚባል የብሄረሰቡ ተወላጅ በጥይት ተመታ፡፡"

መጋቢት 25 ቀን 2000 ዓ.ም ዋቅጅራ ሆቴል ውስጥ በመግባት ድብደባ ከተፈፀመ በኋላ ዝርፊያ ሲጀመር ተኩስ ተከፈተ፡፡ ሽማግሌዎች ተኩሱ እንዲቆም አደረጉ፡፡ መጋቢት 26 ቀን 2000 ዓ.ም ሻሻ፣ ወሻ፣ ኬላ በሚባሉት ቀበሌዎች ተኩስ ተጀመረ፡፡ ተኩሱ ተካረረ፡፡ የፖሊስ ኃይል ከአዋሳ ዞን ቢመጣም ግጭቱን ሊቆጣጠር አልቻለም፡፡ እንደ አቶ መንገሻ ገለፃ "የዞኑ ፖሊስ ለሲዳማ ብሔረሰብ አባላት ሽፋን ሰጥቷል፡፡ የጉጅ ኦሮሞዎች በዚህን ጊዜ መሸሽን መርጠዋል፡፡ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወጥተዋል፡፡"

የወንዶ ገነት ፖሊስ ስልክ ቢደወልም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ የወረዳው የፖሊስ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ ለዞኑ ሪፖርት እንዲያቀርቡ መታዘዛቸውን ገልፀውልናል፡፡ የሲዳማ ዞን ፖሊስ አዛዥ አቶ መስፍን በበኩላቸው ችግሩ መፈጠሩን አምነው "የሞባይል ስልኬ በደንብ ስለማይሰማኝ በዋናው መስመር አናግሩኝ" በማለት የቢሮ ስልክ ከሰጡ በኋላ ስልኩን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ሞባይላቸውንም አጥፍተዋል፡፡

የደቡብ ክልል የፀጥታ አስተዳደር የሚሊሺያ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢዮብ አምበሴ በበኩላቸው በወንዶ ገነት ተፈጠረ የተባለውን ችግር እንደሚያውቁት፣ ነገር ግን ለተመሳሳይ ሥራ ወደ ሌላ ቦታ ተጉዘው ስለነበር ሙሉ መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አዶ "ኮሚሽኑ ለማጣራት መርማሪ ፖሊሶችን ልኳል፡፡ መርማሪዎቹ አጣርተው ሪፖርት ሳያቀርቡ ስለደረሰው አደጋ በዝርዝር መናገር ያስቸግራል" በማለት "በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም አለ፡፡" ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፍትህና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አበበ "እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሰላማዊ መንገድ ሁኔታዎችን ለማስተናገድና መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አውቃለሁ" ካሉ በኋላ አሁን ተፈጠረ የተባለው ግጭት የኦህዴድ 18ኛ ዓመት በዓል በወንዶ ገነት ከመከበሩ ጋር ተያያዥነት አለው ለሚለው መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በሥራ ሌላ ቦታ ስለነበሩ ዝርዝር መረጃው እንደሌላቸውም አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ክልል የአጎራባች ክልሎች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጀ ዳኬጉቾ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳላቸው በተገለፀልን መሰረት በፀሐፊያቸው በኩል ልናገኛቸው ሞክረን አልተሳካም፡፡

በወንዶ ገነት ዋቅጅራ ሆቴል፣ መገናኛ ሆቴልና ግሪን ካፍቴሪያ መቃጠላቸውን፣ የቦ፣ ባጃ፣ አሩማ፣ አባዬ፣ ኬላ፣ ወሻ፣ ወተራና ቀጨማ፣ ሸሽና ቀቀሌዎች በርካታ የመኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉ አቶ መንገሻ ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ በተከሰተ ማግስት የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንቶች ተገናኝተው መምከራቸውን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት በሚባሉት ላይ ጥብቅ ርምጃ እንደሚወስድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኦሮሚያና ከደቡብ የተወከሉ በጊዜያዊነት እያስተዳደሩ ነው፡፡

ወንዶ ገነት በተፈጠረው ግጭት የሻሸመኔ፣ አዳማ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ አዲስ አበባ. . . ያሉ የጫት ነጋዴዎችና ቃሚዎች የጫት አቅርቦት፣ እንደተጓደለባቸው መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ የጉጅ ኦሮሞዎችና የሲዳማ ብሄረሰቦች ያለመስማማት በተደጋጋሚ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ እያስከተለ የመጨረሻ ርምጃ የማይወሰድበት ከጫት የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ የመሆኑ ጉዳይ እንደሆነ ባለፈው ዓመት የተፈጠረውን ግጭት አስመልክተን በዘገብንበት ወቅት መጠቆማችን አይዘነጋም፡፡  

በወረዳው ቀደም ሲል በተከሰተ ግጭት የደረሰውን የሞት አደጋና የንብረት ውድመት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥት አጣሪ መድበው ማስጠናታቸውና ጉዳዩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ አስተያየት እንደተሰጠበት መዘገባችን ይታወሳል፡፡  

በአሰግድ ተፈራ
 
< Prev   Next >