Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow ኤሌክትሪክ በሳምንት ሁለት...
ኤሌክትሪክ በሳምንት ሁለት... Print E-mail
Wednesday, 09 April 2008
ኤሌክትሪክ በሳምንት ሁለት ሙሉ ቀን ይቋረጣል

ፕሮግራሙ ዛሬ ይፋ ይሆናል


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከገጠመው የኃይል እጥረት ጋር በተያያዘ በእያንዳንዱ አካባቢ በሳምንት ሁለት ቀናት ለ12 ሰዓታት ያህል የመብራት ኃይል እንደሚያቋርጥ፣ ዝርዝሩን በዛሬው ዕለት ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
 
የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰንደቁ አርአያ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ ከመጋቢት 29 ቀን ጀምሮ በጀመረው አዲስ ፕሮግራም መሰረት እያንዳንዱ አካባቢ በሣምንት ሁለት ቀናት ኃይል የሚቋረጥበት ሆኖ፣ በእያንዳንዱ ቀን ከጧቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ድረስ ፕሮግራሙ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

ቀደም ሲል እየተሰራበት የነበረው ፕሮግራም ከጧቱ ለግማሽ ቀን ማለትም 12፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 6፡00 ሰዓት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰንደቁ በዚህ አይነቱ ፕሮግራም እስከ ክረምት መግቢያ (ሰኔ 30 ቀን) እንደማይደረስ በመገመቱ የፕሮግራም ለውጥ ማድረግ ማስፈለጉን አስታውቀዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በአዲስ ዘመን እና በኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጦች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቋረጥባቸው አካባቢዎች የአንድ ወር ፕሮግራም ማለትም ከሚያዚያ 1-30 ቀን 2000 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግ፣ ሚያዝያ 30 ቀን ከመድረሱ አስቀድሞ የግንቦት ወር ፕሮግራም ለውጥ ስለመደረጉም ሆነ አለመደረጉ ለሕዝብ እንደሚገለፅ አቶ ሰንደቁ ገልፀዋል፡፡

አዲሱ ፕሮግራም ከጧቱ 2፡00 ሰዓት እንዲጀምር የተደረገው ሕብረተሰቡ ወደ ሥራ በመግቢያው ሰዓት ላይ ኃይል አጥቶ እንዳይጨነቅ በማሰብ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ፕሮግራም ውጪ ደንበኞች የኃይል መቋረጥ ሲያጋጥማቸው የቴክኒክ ችግር መሆኑን ተረድተው በተለመዱ ስልክ ቁጥሮች ጥገና እንዲከናወንላቸው ለኮርፖሬሽኑ እንዲያስታውቁ አሳስበዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የመጠጥ ውሃ ሥርጭትን ያስተጓጉል እንደሆነ አቶ ሰንደቁ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  "ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ኮርፖሬሽኑ ኃይል የማይቋረጥባቸው መስመሮች ማዘጋጀቱን፣ ከዚህም በተጨማሪ በአራት ቦታዎች ማለትም (ጃልሜዳ፣ ተፈሪ መኮንን፣ ጌጃ፣ ራስ ሀይሉ) አምስት ዲዝል ጄኔሬተሮች መተከላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ዲዝል ጀኔሬተሮች በወር 100 ሚሊዮን ብር እያወጣ መሆኑንም አቶ ሰንደቁ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እስከ 1998 ዓ.ም በተገነቡ የማመንጫ ጣቢያዎች 814 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያገኘ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከበልግ ዝናብ መጥፋት፣  ከኢንቨስትመንትና ከቤት ውስጥ ፍጆታ ማደግ ጋር በተያያዘ ወደ 80 ሜጋዋት የኃይል ጉድለት እንዳጋጠመው፣ ችግሩን ለመፍታት በመጪው ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ተስፋ የተጣለው 300 ሜጋዋት በሚያመነጨው የተከዜ ፕሮጄክት ላይ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ማኔጅመንት ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫም ችግሩን ለመቋቋም ኢንዱስትሪዎች እና ልዩ ልዩ ተቋማት የራሳቸው ዲዝል ጀኔሬተር እንዲገጥሙ፣ ለዚህም ኮርፖሬሽኑ የቴክኒክ የምክር ድጋፍ የሚሰጥ ቢሮ ማቋቋሙን፣ ኅብረተሰቡም ሀይልን በቁጠባ የመጠቀም ባህል እንዲያዳብር መምከሩ ይታወሳል፡፡

በፍሬው አበበ
 
< Prev   Next >