Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ያለፈውን ምርጫ፡-
ያለፈውን ምርጫ፡- Print E-mail
Wednesday, 09 April 2008
ጠንካራ ጎን እናጠናክር፤ ደካማ ጎን እናስወግድ!

በአንድ አገር የምርጫ ታሪክ ልዩ ትኩረትና ክብደት ሊሰጠው የሚገባ በምርጫው ማን አሸነፈ የሚለው ሳይሆን ምርጫው እንዴት ተካሄደ እንዴት ተከናወነ የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም የምርጫ ሂደት የሥርዓት ነፀብራቅ ሲሆን አሸናፊ ፓርቲ ግን በየጊዜው ሊቀያየር ይችላል፡፡ የምርጫ ሥርዓት ዘላቂነት ያለው ሲሆን ተመራጭ ፓርቲ ግን የወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነፀብራቅ ሊሆን ይችላል፡፡

በአገራችን በኢትዮጵያም መመዘኛችኝ ይኸው ነው፡፡ የምርጫ አካሄዳችን እንዴት ነበር የሚለው ነው፡፡ ያለፈው የ1997 ዓ.ም ምርጫችን ከምርጫው በኋላ ተበላሸ እንጂ የሚያኮራና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነበረው፡፡ ከነግድፈቱም ቢሆን የአገራችንን የምርጫ ታሪክና ሂደት አንድ ትልቅ እርምጃ ወደፊት ተራምዷል፡፡

ያለፈው ምርጫችን ልንማርበት የሚገባና ልናጠናክረውና ልናስወግደው የሚገባ ሁለት ምዕራፎች የያዘ ነበር፡፡

እስከ ምርጫው ዕለት የነበረው ምዕራፍ በዋነኛነት በአዎንታ የሚገለፅ አኩሪ ምዕራፍ ነበር፡፡ በርካታ ፓርቲዎች ለውድድር የተሰለፉበት ከፍተኛ ቅስቀሳ በመላው አገራቱ የተካሄደበት ነበር፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሰፊ የክርክር መድረክ ያዘጋጁበትና ያስተላለፉበት ነበር፡፡ በርካታ ሕዝብ ለምርጫ የተመዘገበበትና በከፍተኛ ስነ ሥርዓት እስከሌሊት ድረስ የመረጠበት ነበር፡፡ እጅግ ሰላማዊና ደማቅና አዎንታዊ መንፈስ ያዘለ ምርጫ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የምርጫ ውጤት ሲነገር እንኳ ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ አሸነፉ የሚል ነበር፡፡

ከላይ የጠቃቀስናቸው በቀላሉ ሊታይና ሊገመት የሚገባው አይደለም፡፡ ልናዳብረው የሚገባ የምርጫ ሂደታችንን ጠንካራ ጎን ነው፡፡

ሆኖም ከምርጫው በኋላ አሉታዊ ተሞክሮዎችም በብዛት ታይተውበታል፡፡ ጥቂቶችን እንጠቃቅስ፡፡ ገና ምርጫው ሳይነገርና ሳይቆጠር ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ አካባቢ ገና ሕዝቡ መረጦ ሳይጨርስም ምርጫው ተጭበርብሯል፣ የሚል አስፈላጊ ያልሆነ  መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሳያሳውቅ ውጤቱን ተወዳዳሪዎች ገልፀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ንትርክ ተከስቷል፡፡ አብሮ የተወዳደረ የተቃዋሚ ጎራ ተሰነጣጥቋል፡፡ በኢትዮጵያዊያን ከማመን ይልቅ በውጭ ታዛቢዎች ላይ መተማመን ተጀመረ፡፡ የውጭ በተለይም የአውሮፓ ታዛቢዎች ከስነ ሥርዓትና ከስነ ምግባር ውጭ መግለጫ ሰጡ፡፡ እስከ ምርጫው ዝግጅትና ዕለት በጭራሽ ያልታየ የፀጥታና የደህንነት ሃይል ወደ መድረክ መውጣት ጀመረ፡፡ አላስፈላጊና ዘረኛ ቅስቀሳ ሕዝብን መከፋፈል ጀመረ፡፡ ግድያ እስር ሆነ፡፡

ከምርጫ በኋላ የታየው የጠቃቀስነው ሁኔታ በአሉታ የሚጠቀስ በቀጣይ የፓርቲ ሂደት በጭራሽ ሊደገም የማይገባ ነው፡፡

እንግዲያውስ ስለ ቀጣይ ምርጫ ሰታሰብ ጠንካራ ጎንን የሚያጠናክር ደካማ ጎንን የሚያስወግድ ምርጫ መሆን እንዳለበት ማረጋገጥ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገርም ነፃና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሁኔታ መፍጠርና አሉታዊና እርስ በርስ የሚያጋጭ ዘረኛ ቅስቃሳ ማስወገድ፣ ከዛም ወደ ግድያ፣ እስርና ይቅርታና መፈታት የሚያመራ አላስፈላጊ ነገር ሁሉ ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡

ይህ የሁሉም ወገን ሃላፊነት ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ የተቃዋሚ ፓርቲና የሕዝብ ሃላፊነት ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ በዚህ ምርጫ ያለፈው ስህተት እንዳይደገም ምን ላድረግ? ያለፈውን ጠንካራ ጎን ይበልጥ ለማጎልበት ምን ልስራ? ብሎ ማሰብና ከልብ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንደዚሁ ባለፈው ምርጫ ምን ፈፀምን? ምን ስህተት ነበረብን? ምን ልናስወግደው የሚገባ ነገር አለ? ብለው ራሳቸውን መገምገም ይኖርባቸዋል፡፡ ተስተካክለው ሊቀርቡ ይገባል፡፡

ሕዝብም ቢሆን ሁሉም ነገር ለእነሱ መተው የለበትም፡፡ ሕዝብ ራሱ የሚጠቀመውን ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በትክክል ሊያይና ሊከታተል ይገባል፡፡ አዎንታዊ ቅስቀሳ እንደ አሉታዊ ቅስቀሳ እንዳይቀበል በውል ማሳወቅና ግልፅ መልዕክት ለፓርቲዎች ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡

የማሟያ ምርጫ ለማካሄድ በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ ለአዲስ አበባ ምክር ቤትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ምርጫ እያካሄድን ነው፡፡ ለአዲስ አበባ በሙሉና ለተወካዮች ምክር ቤት በጎደሉት፡፡

ይህ የምርጫ ሂደት ተጨማሪ አዎንታዊ ተሞክሮ የምንሰንቅበት መድረክ አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በዚህ ተሞክሮ ለቀጣይ ዋና ምርጫ የተጠናከረ ዝግጅት የምናደርግበት ይሆናል፡፡

በዚህ የማሟያ ምርጫ ባለፈው ምርጫ ያገኘናቸው አዎንታዊ ተሞክሮዎች አጠናክረን አሉታዊ ተሞክሮዎችን አስወግደን የተሻለ የአዲስ አበባ ምክር ቤትና የተሻለ ፓርላማ ይዘን የምንጓዝበት መሆን ይገባናል፡፡

በዚህ የማሟያ ምርጫ የምንጠብቀው አንድ ዓብይ እርምጃ የተገኘውን ውጤት ማንኛውም ወገን በደስታ አሜን ብሎ እንዲቀበለው ነው፡፡ ምርጫና ሁከት አብሮ ይሄዳሉ የሚል በአፍሪካ እየተያ ያለው ገፅታ መቀየር አለብን፡፡ በአፍሪካም ምርጫን በደስታ መቀበል ተጀምሩዋል፤ የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ይጠበቅብናል፡፡

ይህንና ይህን ስናደርግ ነው ያለፈው ምርጫ አዎንታዊ ገፅታ አጎልብተን ደካማ ገፅታውን ወደ አዎንታዊ ተሞክሮ ልንለውጠው የምንችለው፡፡ ከተሞክሮ ውጭ ልንጠቀም የምንችለው፡፡
 
< Prev   Next >