| ለአዲስ አበባ ችግሮች የተወዳዳሪ... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
ለአዲስ አበባ ችግሮች የተወዳዳሪ ፓርቲዎች የመፍትሄ አማራጭ
በአዲስ አበባ የሚታዩ ውስብስብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት በከተማው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀዱት የመፍትሄ አማራጭ ላይ ተከራከሩ፡፡ ባለፈው እሑድ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ "የአዲስ አበባ ችግሮችና የተወዳዳሪ ፓርቲዎች የመፍትሄ ዕቅድ" በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የክርክር መድረክ፣ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ፣ ቅንጅት፣ ኢዴህ፣ ኢዴኃህ፣ ኦፌዴንና መኢብን ቢመረጡ ለከተማዋ የያዙትን ዕቅድ አስታውቀዋል፡፡ በመድረኩ ቀድሞ የአማራጭ ሃሳቡን ለተሳታፊዎች ያቀረበው ኢሕአዴግ ሲሆን በከተማው ላሉት ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ መጠለያ፣ አገልግሎት፣ ውሃ፣ ትራንስፖርት፣ ስልክና መብራት የመሳሰሉት ችግሮችን ለማስወገድ የያዛቸውን ዕቅዶች ዘርዝሯል፡፡ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ፓኬጆች ተዘጋጅተው ለወጣቶች የሙያ ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ የፓርቱው ተወካዮች ተናግረዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለልም የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እየቀየሰና እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ፣ ፓርቲው ከተመረጠ እነዚህ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገል"ል፡፡ የመጠለያ ችግርን ለመቅረፍ የኮንዶሚንየም ቤቶች ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በአሁኑ ወቅት 33 ሺህ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት የድርጅቱ ተወካዮች፣ ኢሕአዴግ የአዲስ አበባ ሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ ከተመረጠ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ በየዓመቱ ከ50 ሺህ በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለመገንባት ማቀዱን አስረድተዋል፡፡ ትምህርትን በተመለከተ ኢሕአዴግ እስከ አሁን በርካታ ሥራዎች መሥራቱና የፈረቃ ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ማድረጉ እንዲሁም ጥራት ያለው ትምህርት እየተሰጠ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዴህ/ኢዲዩ) ተወካዮች በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተቋቋሙት ሲቪል ማኅበራት (ፎረሞች) የኢሕአዴግ የፖለቲካ መሣሪያ መሆናቸውን በመጠቆም ሕዝቡ ከመረጠው ከማንም የፖለቲካ አመለካከት የፀዱ ማኅበራት በነፃ እንዲቋቋሙ ይታገላል ብለዋል፡፡ ከላይ እስከታች ያሉት የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም በኢሕአዴግ አባሎች የተተበተቡ ናቸው በማለት፣ ኢሕአዴግን በፈላጭ ቆራጭነት ፈርጀዋል፡፡ ልማት ኖረም አልኖረም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያጣው ትልቁ ነገር "ፍትህ" እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከፖለቲካ ቁጥጥር ነፃ የሆነ አሰራር ለማንገሥና የዜጎችን የህሊና ነፃነት ለማረጋገጥ ድርጅታቸው ተግቶ እንደሚሰራ ተወካዮቹ ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተጠቃሚዎች የኢሕአዴግ አባላት ብቻ ናቸው በማለት ገዢውን ፓርቲ ኮንነዋል፡፡ ኢዴህ በመዲናው ያለው ቆሻሻ ለተለያዩ በሽታዎችና ችግሮች መንስኤ መሆኑን ገልፆ፣ ድርጅቱ ቢመረጥ ቆሻሻውን አስወግዶ መልሶ ጥቅም ላይ እንደሚያውለው ቃል ገብቷል፡፡ ለአረጋውያንም ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጡ ተወካዮቹ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት ተወካዮችም በከተማው ያለው የመሬት አሰጣጥ ስርዓት ወጥ አለመሆኑ፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በሕገወጥ መንገድ መሬት እየሸጡ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከተመረጡ ነዋሪዎች በማኅበራት ተደራጅተው ቦታ የሚያገኙበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ተናግረዋል፡፡ ከተመረጡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በአነስተኛ ወለድ ብድር አግኝተው ኑሯቸውን የሚያሸንፉበት መንገድ እንደሚፈጥሩም ጠቁመዋል፡፡ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ወክለው የተገኙት የከተማው ዕጩ ተወዳዳሪዎች በበኩላቸው፣ ከተማዋ ዘመናዊና ለኑሮ ተስማሚ እንድትሆን እናደርጋለን ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፍትህ አካላት ነፃና ገለልተኛ አለመሆናቸውን በመውቀስ፣ ድርጅታቸው ከተመረጠ ፍ/ቤቶች በነፃነት እንዲሰሩ እንደሚያደርጉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ተወካዮቹ በከተማው በትምህርት፣ ጤናና ሌሎች አገልግሎቶች ከፍተኛ ችግር እንዳለ ጠቁመው፣ በተለይ ሆስፒታሎች የቆዩና ያረጁ በመሆናቸው፣ ብቁ ባለሙያም ስለሌላቸው መሥራት በሚያቆሙበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ የድርጅቱ ተወካዮች በማከልም ዝቅተኛ ገቢ ያለው ድሀው የህብረተሰብ ክፍል ተገቢ የህክምና አገልግሎት እያገኘ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ቤተሰብ ልጆች እየተሰጠ ያለው ትምህርት ጥራት የጎደለው መሆኑን ውጤታቸው ይመሰክራል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ "ጨንፈሩ ብዙ ነው" በማለት የሴቶች፣ የነዋሪዎችና የወጣቶች ፎረም ስማቸው ተለወጠ እንጂ የኢህአዴግ አደረጃጀት አካል ናቸው ብለዋል፡፡ ኦፌዴን ሕዝቡ ከመረጠው የፍትህ፣ የአደረጃጀት፣ የትምህርትና የህክምና ጥራት እንደሚያሻሽል ተወካዮቹ ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ ይሁንታ ካገኘ፣ ዴሞክራሲ፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ እውነተኛ ፌዴራሊዝምንና የፍትህ ነፃነት ማረጋገጥ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ተወካዮችም አሁን የሚታየው ጥራት የሌለው ቢሮክራሲና ብልሹ አሰራርን አስወግደው የገዢው ፓርቲ ፖሊሲና የአፈፃፀም ችግሮችን ለማሻሻል ተግተው እንደሚሠረ አስታውቀዋል፡፡ "ሕዝብ እውነት ልንነግረው ይገባል" ያሉት ተወካዩ "በአሁኑ ምርጫ የመንግሥትን የፖሊሲ ለውጥ የምናደርግበት ሳይሆን መንግሥት የዘረጋው ፖሊሲ በተሻለ ሁኔታ የምናስፈፅምበት ነው" ብለዋል፡፡ መኢብን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለው ሲቪል ሰርቪስና የፖለቲካ ሹመኛ መለየት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል፡፡ የማይሰራውን ነገር እንሰራለን እያሉ መዋሸት ሊስተካከል እንደሚገባና በ97 ምርጫ "የማይሰራውን ነገር እንሰራለን" ተብሎ ያስከተለውን ከፍተኛ ችግር ጠቅሰዋል፡፡ የመኢብን ተወካዮች ድርጅታቸው ከተመረጠ በአዲስ አበባ የመሬት ችግር እንደማይኖር ጠቅሰው፣ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ እርከን የሚገኙ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው መሬት የሚያገኙበት ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ፓርቲውን ወክለው በአዲስ አበባ የሚወዳደሩት የድርጅቱ አመራሮች እንዳሉት ከሆነ የመኢብን ዋነኛው ዓላማ በከተማው ሰላምን ማስፈን ነው፡፡ በዚህም "ዝም ያለው"ን የከተማው ሕዝብ ቀርበው በማነጋገር ፍላጎቱን ተገንዝበው ችግሩን መፍታትና ሰላምና መረጋጋት መፍጠር የፓርቲው ትልቁ ዓላማ እንደሆነ ተወካዮቹ ገልፀዋል፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ተወካዮች ከሙስና የፀዳ አሰራር ዘርግተው ሕዝቡን ለማገልገልና ፍትህን ለማስፈን እንደሚታገሉ የፓርቲው ተወካዮች ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ለከተማው ችግሮች መፍትሄ ይሆናል ያሉዋቸውን ፕሮግራሞች ለክርክሩ ተሳታፊዎች ካሳወቁ በኋላ በመድረኩ የተገኙት ተሳታፊዎች ለእያንዳንዱ ፓርቲ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በመከላከያና በፖሊስ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው አብዛኛዎቹ ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ እንደሚያደርጉ ያላቸውን አቋም አስታውቀዋል፡፡ በተለይ መኢብን እነዚህ ተቋማት ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ባለመሆናቸው፣ ፓርቲ በተለዋወጠ ቁጥር ሳይፈርሱ ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ፓርቲው በማከልም ፎሮሞቹና ማህበራቱ የኢህአዴግ እጅ አለባቸው ብሎ እንደማያምን ገልፀዋል፡፡ ፎሮሞቹ ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው መሥራታቸውና መድረክ እያመቻቹ ችግራቸውን ለሚመለከተው አካል ማቅረባቸው አወንታዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን በማድረጋቸው ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነት አላቸው ወዘተ. የሚል አሉባልታ ልናስወግድ ይገባል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ከፎረሞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት አስመለክቶ "የእኔ አባላት ከሆኑ ዕድለኛ ነኝ" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ለምን በቀበሌዎች አልተወዳደረም በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ተወካዮቹ "የራሳችንን ፖሊሲ ለማስፈፀም ስላልሆነ አስፈላጊነቱ አልታየንም" ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ የፓርቲዎቹን ፕሮግራም ተመልክቶ፤ ፕሮግራምና ዕቅድ የማስፈፀም አቅም የሌላቸውና አንዳንዶቹም በቤተሰብነት ብቻ የተሰባሰቡ በማለት ተቃዋሚዎችን ተችቷል፡፡ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች ተሰንዝሮበታል፡፡ የመጀመሪያው የቅንጅት አመራሮች የበፊቶቹ ናቸው ወይ? የሚል ሲሆን ተወካዮቹ የፓርቲው ህገ ደንብና ፕሮግራም ራሱ እንደሆነ ጠቅሰው አሁን ያሉት አመራሮችም በ97 ምርጫ በፓርቲው ስም ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተወዳደሩ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ፓርቲው ከፅንፍና ከብጥብጥ ተላቋል ወይ? ለሚለው ሁለተኛው ጥያቄ የፓርቲው የትግል ስትራቴጂ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ ተወካዩ አረጋግጠዋል፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |