| የዚምባብዌ ምርጫ ለኢትዮጵያ ምን ያስተምራታል? |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
ዓለም እ.ኤ.አ ከ198ዐ እስከ 2ዐዐ8 ያለው ሀያ ስምንት ዓመት ባሉት ጊዜያት በበጎውም ሆነ በክፉው በብዙ ተቀይራለች፡፡ አፍሪካ ሰቆቃዋ ጨምሮ እንደሆነ እንጂ መሠረታዊ ለውጥ ለዜጎቿ አልታየም፡፡ በቅርብ ዓመታት የሚደረጉና የተደረጉ ብሔራዊ ምርጫዎች ግን የአፍሪካን ተስፋ ያለመለሙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ቀጥሎም በኬንያ ከዚያም አሁን በዚምባብዌ ከመንግሥት፣ ከተቃዋሚ ኃይሎችና ከምርጫ አስፈፃሚ አካላትም በላይ ህዝቡ የተሻለ አርቆ አሳቢ መሆኑን አሳይቷል፡፡
ከላይ በመግቢያችን ላይ የተገለፀው ዓመት የዚምባብዌው ኘሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የሥልጣን ዘመን ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት በርካታ ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ መጭበርበራቸው ቢገለፅም ሙጋቤ ሁሉንም አሸንፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1987 የዚምባብዌ ህገ መንግሥትን ለማሻሻል የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስማቸውን ወደ ፣ኘሬዚዳንትነት፣ ቀየሩ፡፡ የኢትዮጵያ አቻቸው በተቃራኒው እ.ኤ.አ እስከ 1995 ድረስ ኘሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት፡፡ ይህም የሆነው በተመሳሳይ የሽግግር ወቅት ቻርተሩን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በመተካት ነው፡፡ ሦስት ብሔራዊ ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን ሦስቱም ላይ ተቃዋሚዎች በምርጫው ውጤት ላይ ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡ ስለ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስንጠቅስ በእንግሊዝና በአሜሪካ ያሉት ፓርቲዎች፣ የሚሰሩት ሥራ ስላላቸው ተቃዋሚዎች አይባሉም፡፡ በመደበኛው ጊዜ ያው ፓርቲ ናቸው፡፡ በምርጫ ጊዜ ደግሞ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ይባላሉ፡፡ ለመለየት ሲባል ፣ገዥው፣ የሚል ቅጥያ መንግሥት ለሆነው ፓርቲ ይጨመራል፡፡ በዚምባብዌና በኢትዮጵያ ግን ፓርቲዎቹ ዋነኛና ብቸኛ ሥራቸው አድርገው የሚይዙት መንግሥትን መቃወም እንጂ ህዝብን መምራት መስሎ ስለማይታይ ስሙ አብሯቸው ይሄዳል፡፡ በዚያ ላይ በአቅምና በብቃት ስለማይጎለብቱ ባላቸው አቅም ሁሉ መንግሥትን በመቃወም ልዩ ክህሎት አዳብረዋል፡፡ ይህ የመቃወም አባዜ መጠኑን ሲያልፍ እርስ በርስ እንዲናናቁና እንዳይቻቻሉ በር ከፍቷል፡፡ የተገኘችውን ትንሽ ቀዳዳ ደግሞ በመጠቀም መንግሥታቱ በእጃቸው ያለውን ኃይልና ህጋዊ አሠራር ተጠቅመው ማስፋቱን በስህተት አልፈውት አያውቁም፡፡ ዚምባብዌ ከ1ዐ ቀን በፊት ባደረገችው ምርጫ የተነሳ የፖለቲካ ኃይሎቿ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በ1997 ዓ.ም. ካደረገችው ሞቅ ያለ ብሔራዊ ምርጫ በኋላ በመጪው እሁድ የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ታካሂዳለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ሆኑ ኘሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በደጋፊዎቻቸው እንደ ጀግና የሚቆጠሩ ቢሆኑም ተቃዋሚዎቻቸው ግን ሁለቱን መሪዎች "በደካማ ፖሊሲና በሰብአዊ መብት አከባበር ችግራቸው" ይተቿቸዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራትም ሆነ ሁለቱ መሪዎች ብሎም ፓርቲያቸው ኢሕአዴግና ዛኑ ፒ.ኤፍ ከአንድነታቸው ልዩነታቸው ያመዝናል፡፡ ከታሪካዊ መነሻቸው፣ የትግል ስልትና ሒደት እስከ አሁን ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ይለያዩ እንጂ አንዳቸው ለአንዳቸው የሚያውሱት በጎ ነገር አይጠፋም፡፡ በችግር የተሞላው የኬንያ ምርጫ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ሚዲያ፣ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማኀበረሰብ እና መንግሥት ብዙ ትምህርት ሰጥቶ እንዳለፈው ሁሉ በዚምባብዌ ምርጫ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድና ተቃዋሚ ፖርቲዎች በተለይም መራጩ ሕዝብ ብዙ የሚማረው ቁም ነገር ይኖራል፡፡ የዚምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን ከመንግሥት ጣልቃ እስኪገባበትም ቢሆን በአግባቡ ሥራውን መሥራቱና ይህም መንግሥትን ማበሳጨቱ ለኢትዮጵያው ምርጫ ቦርድ ትምህርት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችንም የዜጎችን ሲቪልና ዴሞክራሲያዊ መብት በማዳበር ላይ እንዲተጉ የዚምባብዌ ምሳሌ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተከፋፍለው ከሚጠፉ ተጠናክረው ቢመጡ ሕዝቡ ድጋፍ እንደሚሰጥ ከዚምባብዌ ቢረዱ ጥሩ ነው፡፡ በዚምባብዌ ምርጫ አንዱ ኘሬዚዳንታዊ እጩ የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትርና የፖሊት ቢሮ አባል ሲምባ ማኮኒ ከባድ ተፎካካሪ መሆናቸውን ቀድመው አረጋግጠዋል፡፡ ማኮኒ በሀገሪቷ ሀብታሞች የሚደገፉ ሲሆን አንዳንዶቹ ነገ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም በማሰብ የሚደግፉ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ግን በሀገሪቷ እውነተኛ ለውጥ እንድኖር አጥብቀው የሚፈልጉ ሀገር ወዳዶች መሆናቸው ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ከማኮኒም በላይ የሀገሪቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ንቅናቄ ለዴሞክራሰያዊ ለውጥ (MDC) የሙጋቤን የሥልጣን ቆይታ ለማክተም ተቃርቧል፡፡ የዚምባብዌ ምርጫ ኮሚሽን በሞርጋን ቻንጋራይ የሚመራው ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫዎችን በአብላጫ ማሸነፉን አረጋግጧል፡፡ ቻንጋራይ የኘሬዚዳንትነት ምርጫን እንዳሸነፉ እየተናገሩ ሲሆን ሙጋቤ ደግሞ ሀሰት ይበሉ እንጂ የምርጫ ኮሚሽኑን ውጤት እንዳይገልፅ ማዘዛቸው እና አንዳንድ ሰራተኞችንም ማሰራቸው የቻንጋራይን የይገባኛል ጥያቄ እውነተኛነት ያረጋገጠ ተግባር ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ኤም.ዲ.ሲ (MDC) በዲሲኘሊን የታነፀውን ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ማሸነፉ ነፃ ወገኖችንም አስገርሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ1999 ሙጋቤ በ2ዐዐዐ ሊያካሂዱ ያሰቡትን ሕገ መንግሥታዊ ሪፈረንደም ለመቃወም በሲቪክ ማህበረሰብ፣ በታዋቂ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች በሞርጋን ቻንጋራይ አስተባባሪነት ነው MDC የተቋቋመው፡፡ ሮበርት ሙጋቤ ኤምዲሲ የምዕራባዊያን መሳሪያ ነው በማለት ይተቹት እንጂ መሪዎቹ ለዚምባብዌ ዜጎች ሠላም፣ ድሞክራሲና ብልፅግና የሚታገሉ አባሎቻቸው በሙጋቤ ፓርቲ አባላት እንደ ተገደሉ፣ እንደተሰቃዩና እንደተገረፉ ይናገራሉ፡፡ ሙጋቤ እ.ኤ.አ በ2ዐዐ5 በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ የፓርላማውን ሁለት ሦስተኛ በማሸነፋቸው እ.ኤ.አ በ2ዐዐዐ ሊያካሂዱት የነበረውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በማካሄድ የላይኛውን ምክር ቤት (ሴኔት) እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ ከዚያ በፊት በ2ዐዐ2 እ.ኤ.አ በተካሄደው ኘሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ሮበርት ሙጋቤ እንደተለመደው ከተቃዋሚዎች ተጭበርብሯል የሚል ክስ አስተናገደው ነበር፡፡ ሆኖም የውጭ ታዛቢዎች ምርጫው መጭበርበሩን በማረጋገጣቸው ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ህብረት (common wealth of nations) አባልነት ታግዳለች፡፡ ምርጫ ከማጭበርበር ችግር በተጨማሪ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በመሬት ማሸጋሸግ ድልድል ቅሬታ የገባቸው ምዕራባዊያን የሙጋቤን መንግሥት ይወቅሳል፡፡ ኤምዲሲ በአሁኑ ሰዓት ለሁለት ተከፍሏል፡፡ የመከፋፈሉ መነሻ ሙጋቤ ሴኔት ካቋቋሙ በኋላ ለሴኔት ምክር ቤት እንወዳደር ወይስ አንወዳደር በማለት አተካሮ ከገቡ በኋላ ነወ፡፡ በዌልሽማን ንኩቤ የሚመራ ቡድን በምርጫው ለመሳተፍ ፈቃደኝነቱን ሲያሳይ ሞርጋን ቻንጋራይ የሚመሩት ቡድን ግን በተጭበረበረ ምርጫ መሳተፍ ያለፉት ምርጫዎች ነፃና ገለልተኛ ነበሩ የማለት ያህል በመሆኑ አንሳተፍም ብለው ራሳቸውን ከውድድሩ አገለሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2ዐዐ5 በይፋ ከተለያዩት ከሁለቱ የኤምዲሲ ቡድኖች መካከል የቻንጋራይ ቡድን ይበልጥ ጠንካራና የተሻለ የሕዝብ ድጋፍ ያለው ሲሆን ሌላኛው ቡድን ዌልሽማን ንኩቤን በቀድሞው የናሳ ሮቦቲክስ ስፔሻሊስት ኘሮፌሰር ሙታምባራ ተክቷል፡፡ ቢሆንም የበላይነቱን ከቻንጋራይ አሁንም አልወሰደም፡፡ የኤምዲሲ መሪ ሞርጋን ቻንጋራይ ለረጅም ዓመታት በዘለቀው የፖለቲካ ትግል ህይወታቸው ከሙጋቤ በመቀጠል የተፋጠጡት ከሀገሪቷ ፍርድ ቤቶች ጋር ነው፡፡ ኘሬዚዳንቱን ለመግደል ከመሞከር ወንጀል እስከ ሀገር ክህደት ወንጀል ድረስ ታስረዋል፣ ተደብድበዋል ተሰቃይተዋል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ በ2ዐዐ3 ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በመምራታቸው ተይዘው በፖሊስ የደረሰባቸው ስቃይ ለሕይወታቸው ሁሉ አስጊ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቻንጋራይ የተሰነጣጠቁትን የተለያዩ የዚምባብዌ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማዋሀድና የተባበረ ትግል ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ደካማ በመሆኑ ይተቻሉ፡፡ ከዓመታት በፊት የእንግሊዝ ነጭ ገበሬዎች የእርሻ መሬትን የዚምባብዌ የሙጋቤ ደጋፊዎች በኃይል ከቦታቸው ያለበቂ ካሳና አስፈላጊ ዝግጅት ሲያባሯቸው በጭፍን ድርጊቱን ከመቃወም በዘለለ ከአንድ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በሚጠበቅ አኳኋን ማብራሪያ አልሰጡም፡፡ አንድ ከመቶ የዚምባብዌ ህዝብን የማይወክሉት እነዚህ ነጭ የእንግሊዝ ገበሬዎች የሃገሪቷን 7ዐ በመቶ የሚሸፍን መሬት መያዛቸው የትኛውንም የዚምባብዌ ዜጋ የማያስደስት ቢሆንም ለዚህ ችግር የተሰጠወን መፍትሔ ከተቃወሙ አማራጭ የመፍትሔ ሃሳብ መስጠት ነበረባቸው ተብለዋል፡፡ የዚምባብዌ ኢኮኖሚ እንዲደክም የነጭ እንግሊዛዊያን ገበሬዎች ከእርሻ መሬታቸው መፈናቀል የምርት መቀነስን በማምጣት አስተዋፅኦ አድርጓል ተብሎ ይተቻል፡፡ እርስ በርስ የሚተቻቹትና የሚጣሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ለሀገሪቱ ውድቀት የራሳቸው ድርሻ ያላቸው ሲሆን ሀገሪቷ ቀውስ ውስጥ በገባችበት ወቅት በምርጫ ስትራቴጂው ባለመስማማት ከባድ የአመራር ብቃት እጥረት እንዳለባቸው አሳይተዋል፡፡ የዚምባብዌ ሚዲያ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ አራማጆች እና የሰብአዊ መብት ተከላካዮች በመንግስት ላይ የሰላ ሂስ ያቅርቡ እንጂ ለተቃዋሚዎች ያቀረቡት አማራጭ የትግል ሃሳብም በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ውድቅ እንደተደረገ ይናገራሉ፡፡ በአፍሪካ አህጉር ኃያል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልዕል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ከዚምባብዌ ጋር ያላትን ግንኙነት ከማንም ሌላ ሀገር ጋር የላትም፡፡ ለዚህም ነው እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ 2ዐዐ2 ሀገሪቷ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ጋር በጦርነት ላይ በነበረችበት ጊዜ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ሲጠፋ ተፅእኖው ለደቡብ አፍሪካም ተርፏል፡፡ የዚምባብዌ አለመረጋጋት ደቡብ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አጎራባች ሀገራትን ሁሉ ይጎዳል፡፡ አሁን ከአንዳንድ ምንጮች የሚሰማው ወሬ ሃገራቱ የተከፋፈለውን ኤም.ዲ.ሲ ወይስ ለዓመታት የዳበረ የዲሲኘሊን ባህል ያለውን ዛኑ ፒ ኤፍ እንደግፍ በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡ በየትኛውም የአፍሪካ ሃገር በምርጫ ወቅት በከባድ ሁኔታ ችግር ውስጥ የሚገቡት የምርጫ አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡ የዚምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን የሞርጋን ቻንጋራይ ፓርቲ የሙጋቤን ፓርቲ በፓርላማ ማሸነፉን ቢገልፅም ተቃዋሚዎቹ ግን ሁኔታውን በጥርጣሬ እንደሚያዩት እየገለፁ ነው፡፡ በተለይም ምርጫ ውጤት አለመገለፁ ከጀርባ ችግር ቢኖር ነው፤ እንዲሉ እንዳነሳሳቸው የ" ፓርቲ ቃል አቀባይ ኔልሰን ቻሚሳ ለኤ ኤፍ ፒ ገልፀዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲው ጠበቆች ለዚምባብዌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ይግባኝ የምርጫ ኮሚሽኑ የኘሬዚዳንታዊ ምርጫውን ውጤት እንድገልፅ ፍርድ ቤቱ እንዲያዘው በጠየቀው መሠረት ፍርድ ቤቱ ፣ውጤቱ እንዲገለፅ፣ በማለት ወሰኗል፡፡ ሙጋቤ ግን ምርጫ ኮሚሽኑ የምርጫ ወጤት መግለፁን በማቆም እራሱን ለድጋሜ ቆጠራ እንዲያዘጋጅ አዘዙ፡፡ እንደ ሙጋቤ እምነት ቆጠራው ላይ የአገላለፅ ችግርና የቆጠራ ስህተት አለበት፡፡ በተጨማሪም አጭበርብረውኛል ያላቸውን የምርጫ ኃላፊዎች ያሰረ ሲሆን በጉቦና በምርጫ ማጭበርበር ከሷቸዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ አጠቃላይ ውጤቱ ሳይገለፅ ድጋሜ ቆጠራ እንዲካሄድ መጠየቁ ስሜት እንደማይሰጥ እየገለፁ ነው፡፡ የኘሬዚዳንታዊ ምርጫውና 16 የሚጠጉ የፓርላማ ቦታዎች ላይ የተደረገው ምርጫ ድጋሜ ቆጠራ በገዥው ፓርቲ መጠየቁ አሜሪካን ጨምሮ የምርጫ ኮሚሽኑን ገለልተኝነት የሚጠራጠሩ አካላትን አበሳጭቷል፡፡ የዚምባብዌ ምርጫ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2ዐዐ6 ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በቀረበ ቅሬታ በወቅቱ የነበረውን የምርጫ ጉዳዮች ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ተክቶ የተቋቋመ ነው፡፡ ሙጋቤ ምርጫዎችን እንዲያጭበረብሩ ተባብሯል የተባለውን ድርጅት የተካው ድርጅት ግን አሁንም ምርጫ ለማጭበርበር እየተባበረ ነው እየተባለ ነው፡፡ የህገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ጠበቃና የመንግሥት ተቃዋሚ የሆነው ሎቭሞር ማድሁኩ በሁለቱ ኮሚሽኖች መካከል "የስም እንጂ የተግባር ለውጥ የለም" ይላል፡፡ የዚምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን የሚቋቋመው የፓርላማው ኮሚቴ ከሚቀርቡት 7 እጩዎች ኘሬዚዳንቱ በሚመርጧቸው አራት ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ ከላይ የተገለፁት የዚምባብዌ ምርጫ እውነታዎች መካከል በተፅእኖ ሥር ያሉት የምርጫ ኮሚሽኑ ሠራተኞች፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የገዥው ፓርቲ አባላት ለእውነት፣ ለፍትህና ለህሊናቸው ማደራቸውን ወደ እኛዎቹ ማምጣት ተገቢ ነው፡፡ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ተከፋፍሎም የህዝብ ድጎፍ ማግኘቱ የዚምባብዌ ሕዝብ እንደመሪዎቹ በቀል የማይዝና የማያኮርፍ ይህ አድራጎቱም ጥቂት ግለሰቦችን ሳይሆን ብዙሀኑን እንደሚጎዳ ቀድሞ ያየበት ነው፡፡ ይህ የሕዝብ ትዕግስትና የማያጠራጥር ምርጫ ከዚህ ቀደም ሌላ መስመር የነበራቸውን ሰዎች በአንድነት ተረባርበው ትግል እንዲያካሂዱ ማድረጉም ለእኛዎቹ መራጭና ተመራጮች የላቀ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ምሳሌ የምትፈልግ ከሆነ ኬንያና ዚምባብዌ ከተፈጠሩ ትልቅ ጠባሳ ነጥቦች ላይ እርግቦች ያረፉበትን አረንጓዴ ለምለም መስክ በበረሃውም መሐል ልትፈልግና ንስሀ ልትገባበት ወቅቱ አሁን ነው፡፡ በሰለሞን ጐሹ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |