Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow የእህል ዋጋ ጭማሪው አፍሪካን አደጋ ውስጥ ከቷል
የእህል ዋጋ ጭማሪው አፍሪካን አደጋ ውስጥ ከቷል Print E-mail
Wednesday, 09 April 2008
በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ እህል ዋጋ በመወደዱ በአፍሪካ አገሮች ላይ አደጋ እያንዥበበ ነው፡፡ የአህጉሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትሮችም ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከምግብ እጥረትና የምግብ እህል ውድነትን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ችግር ከኢኮኖሚያዊ ጉዳይ አልፎ ለአህጉሪቱ ሰላምና ፀጥታ አስጊ ሊሆን እንደሚችል ባለፈው ሣምንት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው የአፍሪካ ፋይናንስ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ዋነኛ አጀንዳ ተደርጐ መነሳቱንና የአፍሪካ አገራቱም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በአህጉሪቱ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት ከዙምባብዌ ተነስቶ ሞሮኮ ደርሷል፡፡ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉት ድጐማ ውጤት ባለማምጣቱም በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ ሲያካሂዱ የቆዩት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ድምዳሜ ላይ መድረስ ባይችሉም የአህጉሪቱ ቅድሚያ አጀንዳ ሆኖ ተከታታይ ውይይቶች እንዲዳረጉና መፍትሔ የሚሆን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ስብሰባ ላይ እንደተጠቆመውም የዋጋ ግሽበቱና የሰብል እህል መወደድ የአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይም የራሱን ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ በመሰጋቱ በቀጣይ ዓመታት ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ያዘቀዝቃል ተብሎ ተሰግቷል፡፡

የወቅቱን የአፍሪካውያን ችግር በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢንተርናሽናል ፈንድ አግሪካልቸር ዴቨሎፕመንት ምክትል ዳይሬክተር እንደገለፁት ደግሞ በካሜሮን፣ በሴኔጋል፣ በቡርኪናፋሶና በሞሪታንያ እየታየ ያለው የሕዝብ አመፅ መሠረቱኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሆነና ይህም ችግር ወደ ሌሎች አገራት ይዛመታል የሚል ስጋት እንዳላቸው ነው፡፡

እንደ ኤክስፐርቶች ገለፃ ደግሞ አፍሪካውያን ራስን በመቻልና አማራጭ የሃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ እንዲሁም በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል ከውጭ የሚያስገቡትን እህል በማስቀረት ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትም በዚሁ የሚኒስትሮች ስብሰባ ተገልጿል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ በ2008 ዓ.ም በ62 ከመቶ ዕድገት ማሳየቱ ቢጠቆምም አሁንም አፍሪካ በመሠረተ ልማት ወደ ኋላ የቀረች በዋጋ ግሽበትና በፖለቲካ አለመረጋጋት እየታመሰች ያለች አህጉር ናት፡፡

በአፍሪካ ለዋጋ ግሽበት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የነዳጅ ዋጋ መጨመር በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ እህል ምርት ዋጋ እየተወደደ እንዲሄድ አድርጓል፡፡

ሞውስታፋ ካሴ የተባሉ የሴኔጋል ኢኮኖሚስት እንደገለፁት፣ በዓለም ገበያ ነዳጅ ዋጋ መጨመርና በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣው ከተሜነት ለምግብና ለነዳጅ እጥረት መፈጠር ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት መሠረታዊ መፍትሄ ማግኘት እንደሚኖርበት የሚገልፁ በርካታ ናቸው፡፡ ሁኔታዎች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ በአፍሪካ ከአሁኑ እየታዩ ያሉት የሕዝብ ተቃውሞዎች ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ ይነገራል፡፡

ግብፅ ውስጥ ተቃውሞ ለማድረግ ለሕዝብ ጥሪ ቢያቀርቡም የግብፅ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሰልፉን ማድረግ የማይሞከር መሆኑን አስታውቋል፡፡ በጊኒ ውስጥም ተመሳሳይ ነገር እየታየ ነው፡፡ የጊኒ መንግሥት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ በማቆሙ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በ61 በመቶ እንዲጨምር አስገድዷል፡፡ የታክሲና የትራንስፖርት አገልግሎት ቆሟል፡፡

በጊኒ ቢሣዋ በእጥረቱ ምክንያት የነዳጅ ዘይት ዋጋ በስምንት እጥፍ ጨምሯል፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ባጋጠማቸው የዋጋ ግሽበት የተነሳ በየአገሮቻቸው ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ባለፈው ፌብሩዋሪ ካሜሩን ውስጥ በተነሣ ተቃውሞ 40 ሰዎች ሊሞቱ ችለዋል፡፡

በካሜሮን ብቻ ሣይሆን በአይቮሪኮስት፣ በሞሪታኒያ፣ በሴኔጋልና በቡርኪናፋሶ በተመሳሳይ ሰዎች የሞቱበትና የተጎዱበት ተቃውሞ መካሄዱንም ይኸው ዘገባ ያስረዳል፡፡

ይህንን ተከትሎ የአፍሪካ አገሮች የተለያዩ እርምጃዎች ለማድረግ ተገደዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የካሜሮን፣ የሴኔጋልና የአይቮሪኮስት መንግሥታት በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) አንስተዋል፡፡

ካሜሮን የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ስትጨምር፣ ሱዳን ደግሞ በአንዳንድ ምግቦች ላይ የዋጋ ድጎማ ማድረግ ጀምራለች፡፡

ግብፅ በበኩልዋ ለተከታታይ ስድስት ወራት የሩዝ ምርት ኤክስፖርት ማድረግ አቁማለች፡፡

የሴራሊዮን መንግሥት ደግሞ የሩዝ ምርት በገፍ ለማምረት ፕላን አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር
 
< Prev   Next >