| የገንዘብ ቁጥጥር ፖሊሲው የዋጋ ንረቱን... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
![]() አቶ አንዱዓለም ብርሃኑ አሁን ባለው የኢኮኖሚ መዋቅር የዋጋ ንረቱን ለማስተካከል የገንዘብ ቁጥጥር ፖሊሲ አቅም አናሳ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የዕቅድና ንግድ ሥራ ማስፋፊያ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም ብርሃኑ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት የገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ንረትን የማረጋጋት አቅሙ አናሳ ነው፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ የሚነካው የኢኮኖሚ ክፍል አነስተኛ በመሆኑ የሚወሰዱት እርምጃዎች ለውጥ የማምጣት አቅማቸው አነስተኛ እንደሆነ የገለፁት አቶ አንዱአለም የወለድ ምጣኔ ከ3 በመቶ ወደ 4 በመቶ ቢያድግም በተቀማጭ ሂሳብ ላይ ለውጥ አለመፍጠሩን፣ የማስቀመጫ ወለዱንም መጨመር የሚኖረው ለውጥ አነስተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የወለድ ምጣኔ ጭማሪው ለውጡ አስቀማጮች የሚያስቀምጡትን ገንዘብ ለማሳደግ አላማ ቢያደርግም የተለየ ያመጣው ለውጥ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡ የተቀማጭ ሂሳብ በፊት ያድግበት ከነበረበው የተለየ ለውጥ አለመፍጠሩን ገልፀው ከዚህ ይልቅ ለባንኮች ተጨማሪ ወጪ ፈጥሯል ብለዋል፡፡ የማስቀመጫ ወለድ መጨመር ወለድ ምጣኔ ላይ ጫና ስለሚኖረው የተበዳሪዎችን ወጭ በመጨመር ቁጥራቸውን ይቀንሳል የሚል አመለካከት ቢኖርም የተለየ ውጤት አለመምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው የተቀማጭ ገንዘብ፣ የወለድ ምጣኔና ኢንቨስትመንት ያላቸው ተያያዥነት በኘሪንስኘል ደረጃ ወለድ ሲጨምር ተቀማጭ በመጨመር ኢንቨስትመንት ቢቀንስም በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ እንደማይሆን ገልፀዋል፡፡ የኢኮኖሚው መዋቅርና ሁኔታ ከባህላዊ ግብርና ጋር የተያያዘ መሆኑ የወለድ መረጃዎች በዘርፉ ላይ ለውጥ የመፍጠር አቅማቸው አናሳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የአስቀማጮች ሁኔታ ሲታይ የአብዛኛው አስቀማጮች ሂሳብ በአማካይ ከ1ዐ ሺህ ብር ያነሰ እንደሆነና የአስቀማጮች በአላማ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ለደህንነት ሲሉ መሆኑን ጠቁመው የሚያስቀምጡት ለወለድ ተብሎ ቢሆንም እንኳ ከዋጋ ንረቱ ጋር ተነፃፅሮ የሚገኘው ትክክለኛ ወለድ አሉታዊ ሆኖ ተቀማጭ እያደገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ የተበዳሪዎች የመበደሪያ ወለድ ቢጨምርም፤ በገንዘቡ ኢንቨስት በማድረግ የሚገኘው ውጤት ከፍተኛ በመሆኑ የተበዳሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የወለድ መጠን ከግል ዘርፍ ባለሃብቶች ጋር ትስስር ቢኖረውም እስከ አሁን ችግር አለመኖሩን ገልፀዋል፡፡ የንግድ ባንኮች የተቀማጭ ሂሳብ ወደ 15 በመቶ የተንቀሳቃሽ ሂሳብ ወደ 25 በመቶ ማደጉ የተቀማጭ ገንዘብ ከፍላጎት ጋር ያለው ትስስር አናሳ በመሆኑ ብዙ ለውጥ እንደማይፈጥር ተናግረዋል፡፡ የንግድ ባንኮች ከሚሰበስቡት ገንዘብ ውስጥ በግዴታ የሚያስቀምጡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን መጨመሩ ባንኮች ለተበዳሪዎች የሚያበድሩትን ገንዘብ በመቀነስ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ፍላጐት ለመቀነስ ያለመ ቢሆንም ያለው አቅም ውሱን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በእኛ አገር ዋጋ የሚለካው በችርቻሮ ዋጋ ሲሆን (CPI) 60.3 በመቶ የሚሆነው የምግብ እህልና ከግብርና ሥራ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የተቀማጭ ገንዘብ መጨመር ለውጥ እንደማይፈጥር፤ የምግብ ፍላጎት ተፈጥሯዊ በመሆኑ ከገንዘብ ፍላጎት ጋር ያልተያያዘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በ2ዐዐ2 ዋጋ በተከታታይ ይቀንስ በነበረበት ወቅት የገንዘብ አቅርቦቱ እያደገ የመጣበትን ሂደት አስታውሰው የኢኮኖሚ መዋቅሩ ብዙ ባልተለወጠበት ሁኔታ የገንዘብ አቅርቦትን በመቀነስ ዋጋ መቀነስ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲና የምግብ እህሎች ዋጋ ያላቸው ትስስር አናሳ መሆኑን የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የገንዘብ ፖሊሲን መጠቀም አዋጪ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ ዋጋን ለማረጋጋት በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ለውጥ ባይፈጥርም ባንኮች ከብድር በሚያገኙት ገቢ ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ገልፀዋል፡፡ ባንኮች ሳይገደዱ የሚያስቀምጡት ትርፍ ገንዘብ አለ ብለን ለጠየቅናቸው ሲመልሱ በግል ባንኮች የተንቀሳቃሽ ገንዘብ እጥረት እንጂ ሳይገደዱ የሚያስቀምጡት ገንዘብ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ ባንኮች የሰበሰቡትን ገንዘብ በአጠቃላይ የሚያበድሩበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀው አሁን በወጣው መመሪያ እስከ 75 በመቶ ለማበደር እንደሚፈቅድ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ 3ዐ በመቶ የሚሆን ተንቀሳቃሽ ገንዘብ አስተማማኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የገንዘብ አቅርቦት እያደገ መሆኑን የገለፁት አቶ አንዱአለም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ጋር በተመጣጠነ መልኩ መጓዝ ቢኖርበትም የአቅርቦቱ እድገት ፈጣን መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአጠቃላይ ገንዘብ አቅርቦት መጨመሩ በአጭር ጊዜ ዋጋ የመጨመር አቅም ቢኖረውም የገንዘብ ፖሊሲ ተፅእኖ ያለበት ዘርፍ አናሳ በመሆኑ የምግብ እህሎችን ዋጋ የመጨመር አቅሙ አናሳ ነው፡፡ የኢኮኖሚ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑና በገንዘብ ፖሊሲ የሚጎዱ ዘርፎች ከምግብ ምርቶች ላይ ያላቸው ትስስር አናሳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የዋጋ ንረትን ለማስተካከል ባደጉት አገራት ለደህንነት የተቀመጡ ቦንዶችን በመግዛትና በመሸጥ፣ የተቀማጭ ገንዘብና ወለድ በመለዋወጥ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ኢኮኖሚ ስላላቸው ውጤታማ የሚሆኑበትን ሁኔታ ገልፀዋል፡፡ ዋጋ በአብዛኛው መሠረት ያደረገው ከምግብ አቅርቦት ላይ ስለሆነ ምርትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ ከዋጋ ንረት በበለጠ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ለውጥ እንደሚፈጥር ጠቁመው የወለድ መጠን የተቀማጭ ሂሳብ መጨመሩ ኢንቨስት በማድረግ ከሚገኘው ገቢ ከበለጠ በኢንቨስትመንት ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የሚወሰዱ እርምጃዎች በኢኮኖሚ እድገት ላይም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ በአጭር ጊዜ ምርት ሊሰጡ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር የተለየ የትኩረት እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የብድር አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠር በአጭር ጊዜ ምርትን በሚሰጡ ዘርፎች ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ብሔራዊ ባንክ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት በቂ በሆነ ማበረታቻና ታክስ ዙሪያ ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡ በማዳበሪያና ማስቀመጫ ወለድ መካከል ያለው ሠፊ ልዩነት የመጣው የገንዘብ ተቋማቱ ተወዳዳሪ ባለመሆናቸው ነው የሚለውን ሲመልሱ ካለው አደጋ አንፃር የማበደሪያ ወለዱ ትልቅ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዓለም ባንክ የተሠራ አንድ ጥናትን ጠቅሰው የማበደሪያ ወለድ ገንዘቡ በብድር በመሰጠቱ የሚቀረው ጥቅምና አደጋን መሠረት ያደረገ ሲሆን አንድ ብድር በታሰበው ሥራ ላይ ላይውል፣ የተፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ብሎም ብድሩ ባይመለስ ያሉትን አደጋዎች ለመሸፈን የወለድ መጠኑ ከፍ ማለቱ አስፈላጊ መሆኑን በታዳጊ አገሮች ያለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የባንኮች ትርፋማነት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ ከወለድ በሚገኘው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን በውጭ ምንዛሬ ዋጋ፣ ኮሚሽን፣ የገንዘብ ዝውውር የሚገኝ ገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በባንኮች መካከል ያለው ውድድር አንፃራዊ መሆኑን ገልፀው ባንክ በሚጠቀመው የሕብረተሰብ ክፍል እንደሚወሰንና የውጭ ንግድ ተሳታፊዎችና የሚላኩ ምርቶች አነስተኛ በመሆናቸው በወጪ ንግድ ያለው ውድድር ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመው በሌላ የባንክ አገልግሎት ባንክ ብዙ ባለመስፋፋቱና የአንድ የባንክ ቅርንጫፍ እስከ 155"000 ሰዎች አገልግሎት ስለሚሰጥ ውድድሩ ከፍተኛ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ በቤዛዊት ሥዩም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |