| ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ የደረቅ... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ የደረቅ ወደብ ባለቤት ትሆናለች
ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞጆ ከተማ የመጀመሪያው የደረቅ ወደብ በኢትዮጵያና በቻይና ኩባንያዎች ጥምረት በተቋቋመውና ኖራላ ተብሎ በሚታወቀው የኮንስትራክሽን ኩባንያ እየተገነባ ነው፡፡ 60 ሔክታር ስፋት ያለው የደረቅ ወደብ ግንባታ ከ7 ወራት በኋላ አልቆ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም ሁለተኛው የደረቅ ወደብ በአፋር ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ሰመራ አካባቢ የሚገነባ ሲሆን ለዚህም ግንባታ የሚሆን 100 ሄክታር ቦታ መሰጠቱም ታውቋል፡፡ እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ይህንን የሰመራ የደረቅ ወደብ ግንባታ ለማከናወን መንግስታዊው የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን እንደሚሰራው ገልፀው የግንባታ ስምምነቱም በቅርቡ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለሁለቱም የደረቅ ወደቦች የሚሆኑ የመሣሪያ መረጣዎች ተከናውነዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ የሚሆንም በጀት ተጠንቶ መንግሥት በጀት እንዲተከል ጥያቄ መቅረቡም ታውቋል፡፡ የደረቅ ወደብ አገልግሎት (Dry port) ወደብ አልባ አገሮች የሚጠቀሙበት ዘመናዊ የወጪና የገቢ ምርቶች ማካከል በመሆን አንድ ወደብ ሊሰጥ የሚገባውን ሙሉ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን አገልግሎት ለመጀመር ከታቀደ አስር ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የደረቅ ወደብ አስፈላጊነት እየታመነበትና በመንግሥት ደረጃም ትኩረት ተሰጥቶት በአዲስ መልክ ሥራው እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በተለይ ይህ እንቅስቃሴ ከአዲሱ ዓመት መግቢያ ጀምሮ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ውጤት እየተገኙ መሆናቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ይገልፃሉ፡፡ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ደግሞ የደረቅ ወደብ ግንባታና አገልግሎትን እውን ለማድርግ በብሔራዊ ደረጃ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተቋቋመው አዲስ ኮሚቴ ከትራንስፖርትና ከወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንዲካተቱበት መደረጉንም ሥራውን በመሥራት ላይ ያሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር የተደረገው ኮሚቴ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት የሚሰሩ ባለሙያዎችን ያጠቃለለ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ከኮሜት ትራንስፖርት፣ ከትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ከአምበሳ አውቶቡስ እና ከክልል ከዚሁ ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች ተካተዋል፡፡ ኮሚቴው የግንባታ ሥራዎችን በኃላፊነት ከማስገንባት ጎን ለጎን ከግንባታ በኋላ በይፋ የሚቋቋመውንና ደረቅ ወደቡን የሚያስተዳድር አዲስ መስሪያ ቤት ለማቋቋም የሚያስችለውን ሥራ እየሰራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ደረቅ ወደቡን የሚያስተዳድረው መስሪያ ቤት ሊኖረው የሚገባው የሥራ መዋቅር የባለሙያዎች ብዛትና ጠቅላላ አደረጃጀት ጥናት እየተሰራ ሲሆን አሁን በጊዜያዊ ኮሚቴውን የሚመሩት ባለሙያዎች ወደቡን ለማስተዳደር በሚቋቋመው መስሪያ ቤት ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ እንደሚሰሩም የተገለፀላቸው እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ እነዚህ ሁለት የደረቅ ወደቦች ሥራ ከጀመሩ በኋላ በየአንድ አመቱ ተጨማሪ ደረቅ ወደብ ሊያሰራ የሚችል ገቢ ስለሚገኝ እንደ አስፈላጊነቱ ተመሳሳይ የሆኑ ግንባታዎች ማድረግ ይችላል፡፡ አገሪቱ የደረቅ ወደቦች ባለቤት መሆን በመቻልዋ በዋነኝነት ለወጪና ገቢ ምርቶች የሚወጣ የወደብ አገልግሎት ክፍያ ይቀንሳል፣ ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎትም ለማግኘት ይችላል የሚሉት እኚሁ ባለሙያዎች በተለይ የጉምሩክ አገልግሎቶች በሙሉ በዚህ ደረቅ ወደብ ማዕከል ውስጥ የሚሰጥ በመሆኑ የአገልግሎት ቅልጥፍናን ያመጣል ባይ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር አሁን እየተጠና ባለው ጥናት መሠረት እያንዳንዱ የደረቅ ወደብ ማዕከል በትንሹ 500 ለሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል ሊፈጥር ስለሚችልም ትልቅ ጠቀሜታ አለው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ደረቅ ወደብ አገልግሎት በተወሰኑ መስሪያ ቤቶች ባለሙያዎች ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ከዚሁ ሥራ ጋር የተያያዙ መስሪያ ቤቶች ጋርም በጋራ ለመስራት እንዲቻል የጋራ ምክክሮች እየተደረጉ ነው፡፡ የአገሪቱ የወጪም ሆነ የገቢ ምርቶች ለመውጣትም ሆነ ለማስገባት ጉዳያቸውን አገር ውስጥ ባለው የደረቅ ወደብ ማዕከል የሚፈጸም በመሆኑ የመርከብ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ውል ሲዋዋሉ ገቢ እቃ ከሆነ በመርከብ የማጓጓዙ ሥራና ደረቅ ወደብ እስኪደርስ ድረስ ያለውን ሙሉ የትራንስፖርት አገልግሎት አንድ ኩባንያ የሚሰራው ይሆናል፡፡ አሁን ሊተገበር ለታሰበው የደረቅ ወደብ አገልግሎትና የትራንስፖርት ድርጅቶች በጥምረት የሚሰሩበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡ ለዚህም የሚሆን አዋጅ ባለፈው አመት የወጣ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊትም የደረቅ ወደብ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል የዚህ ኮሚቴና የኢትዮጵያ መንግሥት ትልቅ ፈተና ይሆናል ተብሎ የተገመተው የደረቅ ወደቡ ከመጀመሩ በፊት ከጅቡቲ መንግሥት ጋር የሚደረገው አዲስ ውል ነው፡፡ የወደቡ ሥራ መጀመር የጅቡቲን ገቢ በተወሰነ ደረጃ ስለሚቀንስ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ ስምምነት ከባድ ይሆናል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |