Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow “ምረጡኝ”
“ምረጡኝ” Print E-mail
Wednesday, 09 April 2008
ነጋድራስ እገሌ ለመመረጥ ብለው በየጊዜው ጠጅ አስጥለው ጮማ እያስቆረጡ ነው፡፡ ይህም ወጭያቸው በአራት ዓመት የእንደራሴነት ዘመናቸው የሚመልሱት አይሆንም እየተባለ የሚታሙ ተወዳዳሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ሊካሄድ ስላለው ምርጫ አስመልክቶ በ1960 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ የወጣ ፅሑፍ ነበር፡፡

የመመረጥ ኃላፊነት በግል ፍላጐታቸው ብቻ የሚመሩ መሪዎች የሕዝብን መብት ገፈው ከአስተዳደር ተካፋይነት አግደው ግላዊ ፈላጭ ቆራጭ በመሆን ስለመግዛታቸው የሚሰጠው ምክንያት አለው፡፡ በመጨረሻ ራሱንና ሕዝቡን ከከባድ ጥፋት ላይ የጣለ አንድ አምባገነን እንደጠቀሰው፣ "ሕዝቦች የሚፈልጉትን አያውቁም የሚመስላቸውን መምረጥ አይችሉም፡፡ አጉል ስሜት ቀቢፀ ተስፋና ጅልነት ሞልቷል፡፡ ይህንን ሁሉ ማስቀረት አለብኝ" የሚል ነው፡፡ የግለኛ የጭቆና አገዛዝ ብቻ ለመሥራትና ብዙ ለማሠራት ይቻል ይሆናል፡፡ በፈርኦዎ የጭቆና በትር ባይሆን ኖሮ ፒራሚድ መሠራቱ ያጠራጥራል፡፡ ነገር ግን ከሕዝብ መብቶች፣ ከሕዝብ ክብር የሚበልጥ ምንም ዓይነት ሥራ የለም፡፡ ስለዚህም በዘመናዊ የዴሞክራሲ እምነት የሕዝብ መብት በሕግ ተከብሮ አስተዳደሩም ተካፋይ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የአንድ አገር ሕዝብ በአስተዳደሩ ተካፋይ የሚሆነው ለእያንዳንዱ ግለሰብ በነጠላ ወይም በድምር በመንግሥት አቋም ቀጥተኛ ሥልጣንና ሥራ ተሰጥቶት አይደለም፡፡ በእንደራሴዎቹ አማካኝነት ነው፡፡ እንደራሴዎቹን መርጦ ይልካል፡፡

(ነጋሪት ጋዜጣ መጋቢት 5 ቀን 1960)

ለአምስት ሳንቲም ብልጫ አምሳ ብር ተቀጣ

ከዛሬ 33 ዓመት (1967) በፊት ከዋጋ በላይ የሚሸጡ ነጋዴዎች እየታደኑ ፍርድ ቤት መቅረብ ጀምረው ነበር፡፡ አንድ የአዲስ አበባ የሱቅ ነጋዴ አንድ ምርት ላይ አምስት ሳንቲም ጨምሮ በመገኘቱ ፍርድ ቤት ቀርቦ 5ዐ ብር የተቀጣበት ዜና መጋቢት 17 ቀን 1967 ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዘግቧል፡፡

“ለአምስት ሳንቲም ብልጫ 50 ብር ተቀጣ የሀሰት ስም በመስጠትና መሐመድ አህመድ ነኝ በማለት ሲያስቸግሩ የቆዩት አቶ ዓለም የተባሉ ግለሰብ በተሰማ አባቀማው መንገድ ላይ የሚገኙ ነጋዴ ስልሳ ሳንቲም መሸጥ የሚገባቸውን ሲጃራ አምስት ሳንቲም አስበልጠው ስልሳ አምስት ሳንቲም ስለሸጡ የ6ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት 50 ብር ቀጥቷቸዋል” ሲል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና የማስታወቂያ ክፍል ገለጠ፡፡

አቶ ዓለም ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የቻሉት ቀደም ብሎ በተሰጠው ተገደው እንዲቀርቡ በሚለው በዳኛው ትዕዛዝ መሠረት 24 ሰዓት ፖሊስ ጣቢያ ገብተው ከታሰሩ በኋላ ነው፡፡ ይህም የሆነው ሦስት ጊዜ የፍርድ ቤት ጥሪ ደርሶዋቸው ባለመቀበላቸውና ሕግ በመጣሳቸው ሲሆን፣ እስር ቤት እያሉ የንግድ ሱቃቸው ዝግ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍርድ ቤት ቀርበው ዋጋ በማስበለጥ ተከሰው ከተቀጡት ነጋዴዎች መካከል አቶ ዓለም አስረኛው ናቸው፡፡

(አዲስ ዘመን መጋቢት 17 ቀን 1967)

ዋኛን

ተወለድሁኝ መጥፎ ቀን
በከንቱ ልባክን
ሳልጠጣ ልሰክር
በዋዛ ልሰፈር፣
ዘንግቼያት ስራዬን
ዋ! አንቺን ዋ! ኔን
ሳልወለውል ቀረሁ
የጧት ኮከቤን፣
እኔው አዘጋጀሁ ነጫጭባ ድሌን፣
እንዴት ስል ረስቼ ወዴትን፡፡
ይግረማት ብዬ ደግሞ ዛሬ
አበባዬን ረሳህዋት አበባዬን
ህዋላ ትቼ መጣሁ እንቁጣጣሼን፤
ዋ! አንችን ዋንቺን
ያላቻ ለበን
አንነሳ ይመስል አንዴ ከወደቅን
ዋ ኔን፤ አንቺን ዋ ኔን . . .  

(ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ልጅነት፣1963)

ምኒሊክ የምድር ባቡር ያቆሙት “ድሬ”ን አስበው አይደለም

ምኒሊክ የምድር ባቡር ያቆሙት ድሬዳዋን ለመቆርቆር አስበው ወይም አልመው ሳይሆን በልጅነታቸው በገጠማቸው በሁለት አጋጣሚ ነው፡፡ ምኒሊክ በልጅነት እድሜያቸው በአፄ ቴዎድሮስ ተማርከው በእስር በቆዩበት ዘመን በጊዜው የንጉሡ እስረኛ እንግሊዛዊ ዋልድማየር አስተማሪያቸው ሆኖ ነበር፡፡ ከዋልድማየር ጋር በነበራቸው ቆይታ ከቀሰሙት እውቀት ሁሉ በዘመኑ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ስለሚችለው የምድር ባቡር ጠቀሜታ የሰሙት ቁም ነገር የመጀመሪያው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ የታሰሩ እስረኞችን በኃይል ለማስለቀቅ በጄኔራል ናፒየር እየተመራ ወደ መቅደላ ያመራው የእንግሊዝ ጦር ከባድ የጦር መሳሪያዎቹን ከወደቡ ለማንቀሳቀስ ሐዲድ በመዘርጋት መጠቀሙን በማስተዋላቸው ምኒሊክም በኢትዮጵያ የምድር ባቡር አገልግሎት ነፍስ ዘርቶ የሚያዩበት አጋጣሚ ናፋቂ በመሆናቸው ምክንያት ነበር፡፡

(ድሬ መፅሔት፣ 2000)

ይፈረድብኝ

በዘመኑ፣ በአጉራህ ጠናኝ የተፈጸመ ክርክር ዛሬ በሽምግልና ዳኝነት እንዳለቀ ስምምነት ይግባኝ የሌለው የነገር መደምደሚያ ነበር፡፡ ለተካሄደው ክርክር በቅሎ ወይም ማር እሰጥ እገባ ተባብለው ከሦስት ያላነሱ ምስክሮች ይቆጠሩና ወዲያው ቃላቸውን እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ እቦታው ላይ ከሌሉ ግን የዳኛው መልእክተኛ ወይም ተከራካሪዎቹ የመረጡት ሰው ጭብጡን ተቀብሎ ምስክሮቹ ወዳሉበት ሄዶ ሁለቱም ወገኖች ባሉበት ያመሳክራል፡፡ በዚህም ጊዜ በሁለቱ ተከራካሪዎች የተመረጡ አራት እማኞች መኖር አለባቸው፡፡ መልእክተኛው ትእዛዙን ከፈጸመ በኋላ የምስክሮቹን ድምጽ በቃሉ ይዞ እያንዳንዳቸው የተናገሩትን በየስማቸው ዘርዝሮ ለዳኛው ያስረዳል፡፡ የተዘነጋ ነገር ካለ ያቃናል፡፡ በቃሉ የጸና እንደሆነ ግን ተቃዋሚው የምስክሮቹን ቃል በሚጣረሱ ሰድቤዋለሁና ምስክሩን የሰሙት እማኞች ይንቀሱልኝ ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ እማኞቹ እንዴት እንደተመሰከረ ይጠይቃሉ፡፡ እርሱ እዳለው ነው ብለው የመሰከሩ እንደሆነ ነቃፊው አመሳካሪውን ዳኛ ይከሳል፡፡ አጓድሎ የተገኘ እንደሆነ ግን የምስክሮቹ ድምጽ እማኞቹ እንደተናገሩት ሆኖ ይጸናል፣ ዳኛውም ይወቀሳል፡፡ ተከራካሪዎቹ የምስክሮቹን ቃል ለኔ ነገሩ ለኔ ነገሩ በማለት የተሻሙ እንደሆነ ለማን እንደመሰከሩ በእማኞች ይታደላል፡፡ እማኞቹ የምስክሮቹ ድምጽ ለተከሳሹ ነው ብለው ቢአድሉም ዳኛው የምስክሮቹ ድምጽ ለከሳሽ ነው እንጂ ለተከሳሽ አይደለም ካለ በእሱው ይጸናል፤ በፍርድም ጊዜ እማኞቹም ሆኑ ዳኛው የሚያደርጉት ቃለ መሐላ፣
ይፍረድብኝ ይፈረድብኝ፣
ባደላም ያድላብኝ
በጌታዬ ጠላት ሰይፍ ሞት ይፈረድበት፣
የራቀውን በመድፍ የቀረበውን በሰይፍ
አርዶ ፈርዶ ይጣለው፡፡

(ማኅተመ ሥላሴ ወ፡መ፣ ባለን እንወቅበት፣ 1961)

በሩን እሱ ይዞታል

በዱሮ ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ ባለሥልጣን የፈቀደውን ለማድረግ ባለ ሙሉ ሥልጣን ነበር፡፡ እሱ እንደዚህ አደረገን የሚል አንድም ጯሒና ለፋፊ ባለመኖሩ ከዘመናቱ ብዛት ከዕለታት አንድ ቀን ለንጉሡ እንዲህ ሲል ተናገረ፡፡ ንጉሥ ሆይ? እስቲ አግዠዋለሁ፣ ብለው ሁለት ቀን ልታሠርና ወዳጄና ጠላቴን ልወቀው አለው፡፡

ንጉሡም መልካም ብሎ ወደ እሥር ቤት ሰደደው፡፡ የንጉሡ ባለሟል መታሰር ዕለቱን ሲሰማ ከ2 ሺህ የሚበልጥ ጯሂ፣ ሁሉም የየራሱን በደል ለንጉሡ ገለጸ፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ “ለምንድነው እስካሁን ሳትነግሩኝ የቀራችሁት” ቢላቸው፣ “ጃንሆይ በሩን እሱ ይዞታል፤ በየት አልፈን ልንነግርዎ እንችላለን?” አሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተቆጣና ያንን ባለሟል ዕድሜ ይፍታህ አለው፡፡

(አበበ አይቼህ፣ ጉራማይሌ፣ 1948)

ገራገር

ሟች ላይ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተጣለ


ቤልጂየማዊ ዳኛ በሞተ ግለሰብ ላይ የስምንት ወር እስራትና የአራት መቶ ሠላሳ ፓውንድ የክፍያ ቅጣት ውሳኔ አስተላለፉ፡፡

ጀይ ሻን ብሮክ የተባለ የሀያ አንድ ዓመት ቤልጂየማዊ ከሴት ጓደኛው ጋር በገባው እሰጥ እገባ ክስ ተመስርቶበት ነበር፡፡ የክሱ የውሳኔ ቀጠሮ ከመድረሱ በፊት በደረሰበት የመኪና አደጋ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ጉዳዩን ያልሰሙት የአንትወርፕ ፍርድ ቤት ዳኞች ጀይ በሌለበት የስምንት ወር እስራትና የአራት መቶ ሠላሳ ፓውንድ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡

የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ “ጀይ በቀጠሮው ባይገኝም የፍርድ ሂደቱ በቀጠሮ መሠረት ተካሂዷል፡፡ ስለጀይ መሞት አልሰማንም ነበር” በማለት ገልፀዋል፡፡

ፍየልና ተኩላ ጓደኝነት መሠረቱ

በቻይና በሚገኝ ታወር የእንስሳት ፓርክ ውስጥ ፍየልና ተኩላ ጓደኝነት መስርተው እንደሚኖሩ ተገለፀ፡፡

የፓርኩ ሠራተኛ የሆነው ፃው “በፓርኩ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ፍየሊቷና ተኩላው ጓደኛሞች ሆነዋል” በማለት ገል"ል፡፡ የፓርኩ ሠራተኞች ሳያውቁት ወደ ፍየል ጋጣ የገባው ተኩላ ፍየሊቷን ሳይተናኮል አብሯት ተኝቶ ተገኝቷል፡፡ በዚህ የተጀመረው ድንገተኛ ግንኙነት ቀጥሎ መለያየት ከብዷቸዋል፡፡ ፃው “ተኩላው ፍየሊቱ ከአጠገቡ ከጠፋች ይጮሃል፣ ይረብሻል” ብሏል፡፡ ፍየሊቷና ተኩላው አብረው አንድ ጋጣ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን የሚለያዩት በምግብ ብቻ እንደሆነ የፓርኩ ሠራተኛ አመልክቷል፡፡

ያልታወቁ በራሪ አካላት ጥቃት አደረሱ

ቦስኒያዊው ሪዲቮጂ ላጂክ ከአምስት ጊዜ በላይ የቤቱ ጣሪያ ባልታወቁ በራሪ አካላት መደብደቡን ገል"ል፡፡ የቤል ግሬድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በላጂክ ቤት አካባቢ የተገኙት አለቶች ከጠፈር የተገኙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ተመራማሪዎች በሚስተር ላጂክ መኖሪያ አካባቢ የማግኔት ስበት ስለመኖሩ ጥናት እያካሄዱ ነው፡፡ ላጂክ “እነዚህ አካላት ለምን እንደሚያጠቁኝ አላውቅም፤ ምን እንዳጠፋሁም አልገባኝም” ሲል አማርሯል፡፡

ላጂክ ከአንድ ዓመት በፊት ባዕድ የሆነ በራሪ አካል በቤቱ አካባቢ ማንዣበቡንና ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ በራሪ አካላት እየመጡ በአለት ጥቃት እንዳደረሱበት ተናግሯል፡፡ በተለይ በዝናብ ወቅት እንደሚመላለሱም ጠቁሟል፡፡

በጐች የሳር ማጨጃ ማሽንን ተኩ

በኢጣሊያ የቱሪን አስተዳዳሪ በከተማው ውስጥ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ ለሳር አጨዳ ከሰባት መቶ በላይ በጐችን መቅጠራቸው ተሰማ፡፡

የፓርኩ አስተዳዳሪ በዓመት ከሃያ ሺህ ፓውንድ በላይ ለሳር ማጨጃ ማሽን ወጪ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው “በጐቹን መጠቀም ወጪን ይቀንሳል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም “በጐችን ለሳር አጨዳ ማሰማራት የተፈጥሮን ሚዛን ይጠብቃል፡፡ ከበጐቹ ሽያጭም ተጨማሪ ገቢ ይገኛል” ሲሉ አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡

የፓርኩ ተገልጋዮች በበኩላቸው፣ በበጐቹ በጠጥ ፓርኩ መበላሸቱንና በሳሩ ላይ ተቀምጠው መዝናናት አለመቻላቸውን በመግለፅ የአስተዳደሩን የአጨዳ ስልት ተቃውመዋል፡፡
 
< Prev   Next >