| ፀረ ሙስና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰራር... |
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
ፀረ ሙስና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰራር ለሙስና ክፍት ነው አለ - አመራሮቹ ራሳቸው ጠይቀው፣ ለራሳቸው ፈቅደው፣ ክፍያ ይወስዳሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሙስና የተጋለጠ አሰራር እንደሰፈነበት የፌደራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በትናንትናው ዕለት ያሰራጨው የአሰራር ስርዓት ጥናት ሪፖርት አመለከተ፡፡ ኮሚሽኑ በሙስና የሚያስጠይቅ ወንጀል መኖሩ ከተረጋገጠ የፌዴሬሽኑን አመራሮች ተጠያቂ እንደሚያደርግ በተለይ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ በፌዴሬሽኑ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የግዥ ሂደት፣ ንብረት አስተዳደርና ስርዓት፣ የሰራተኞች ቅጥር፣ ሪከርድና ማህደር አያያዝ የአሰራር ስርዓት ላይ ለሶስት ወር ያህል ጥናት ሲያካሂድ እንደነበር ገልጿል፡፡ ..የሙስናና ብልሹ አሰራር ስጋቶችን ለመከላከል የተካሄደ የአሰራር ስርዓት ጥናት.. ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው ፌዴሬሽኑ ለሂሳብ አያያዝ የሚረዳ የሂሳብ ኮድ /ቻርት ኦፍ አካውንት/ የለውም፡፡ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ የሂሳብ አያያዝ ሰሌዳ ቢኖረውም መረጃ አልባ የሆነው ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በዚህም የተነሳ ሂሳቦች ተለይተው በአይነታቸው ስላልተመዘገቡ ወጪንና ገቢን በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር እንዳይቻል አድርጓል፡፡ የአሰራር ስርዓቱ ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው፡፡ ፌዴረዴሽኑ በዳሽን ባንክ አራት አካውንት ያለው ሲሆን ሁለቱ የዶላር አካውንት ናቸው፡፡ ሌላው የከረንት አካውንት ሲሆን ቀሪው ደግሞ የስፖንሰር ሺፕ አካውንት መሆኑ የዘረዘረው ሪፖርቱ በንግድ ባንክም ሂሳብ በማንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡ ሆኖም ግን ይላል ሪፖርቱ ..ሆኖም ግን ለዶላር አካውንት የባንክ ሂሳቡን ለመከታተልና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያመች የባንክ ሂሳብ መዝገብ የለም፡፡ በተጨማሪ በሁሉም የባንክ ሂሳቦች ላይ እስከ 1979 ዓ.ም ድረስ የባንክ መዝገብና የባንክ ስቴትመንት መካከል የማስታረቅ ስራ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም 1998 ዓ.ም ጀምሮ የባንክ ሂሳብን የማስታረቅ ሥራ አለመሰራቱን ለመረዳት ተችሏል.. በዚህም የተነሳ ፌዴሬሽኑ በባንክ ያለው ቀሪ ሂሳብ ትክክል ስለመሆኑ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስርዓት እንዳይኖር ስለሚደረግ አሰራሩ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር በር እንደሚከፍት በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ የተለያዩ የሂሳቦች አይነቶች አጠቃላይና ተቀጽላ የሂሳብ ቋት /ጀነራል ኤንድ ሰብሲደሪ ሌጀር/ እስከ 1997 ዓ.ም ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ለሁሉም የሂሳብ ዓይነቶች አንድ አንድ ቅጠል የሂሳብ መመዝገቢያ መዝገብ ብቻ እየተጠቀሙ መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት ይፋ ያደርጋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለጥቃቅን ወጪ /ፒቲ ካሽ/ የተመደበውን ገንዘብ በአግባቡ ለማስተዳደርና በገንዘብ ከፋይም እጅ የሚገኘውን ገንዘብ ለመቆጣጠር እንዳይቻል ያደርጋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰንዶች ቢጠፉ ተጠያቂነትን የማያሰፍን አሰራር እንደሆነ፣ አሰራሩም ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጥ መሆኑን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ በየዓመቱን ሆነ በተወሰኑ ጊዜያት የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ ስለማያደርግ ... . . የፌዴሬሽኑ አሰራር የጥሬ ገንዘብ አበአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋሉ ለማረጋገጥና ለመቆጣጠር እንዳይቻል ያደርጋል.. ያለው ሪፖርቱ ወቅታዊ የሂሳብ ሪፖርት ለበላይ ኃላፊዎች እንደማይቀርብ ገልጿል፡፡ ..እ.ኤ.አ 2005-2007 የተዘጋጀ ሪፖርት ተብሎ የቀረበልን ሰነድ በሂሳብ ክፍል ወይም በሌላ አካል ያልተረጋገጠ ከሆኑም በላይ ስለ ጉዳዩ በኮንትራት ቅጥር የሂሳብ ሪፖርቱን አዘጋጅተዋል የተባሉትን ግለሰብ አነጋግረን ለኃላፊዎች ያቀረብኩት መረጃ እንጂ የሂሳብ ሪፖርት እንዳልሆነ ገልፀውልናል.. በዚህና በሌሎች ምክንያቶች አሰራሩ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ በፌደሬሽኑ በሂሳብ ክፍል አንድ የሰው ኃይል ብቻ ነው ያለው..፣ ገንዘብ ያዥ (በተደራራቢነት ነው የሚሰራው..፣ በንብረት ክፍል (አንድ የሰው ኃይል ብቻ ነው ያለው..፣ በሰው ኃይል አስተዳደር (በጥናቱ ወቅት የሰው ኃይል የለም..፣ መዝገብ ቤት (አንድ የሰው ኃይል ብቻ ነው ያለው..፣ በውስጥ ኦዲት (በጥናቱ ወቅት የሰው ኃይል የለም) የተሟላ የሰው ኃይል አለመኖሩ የሂሳብ፣ የንብረት፣ የግዥ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የሪከርድና ማህደር አያያዝ ስርዓቱ ላይ ለተፈጠረው ችግር የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በጥናቱ ወቅት በሂሳብ ክፍል አንድ ባለሙያ ብቻ መኖሩንና የመዝገብ ቤት ሠራተኛዋም የገንዘብ ያዥነት ሥራን በተደራራቢነት እንደሚሰሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የስቴዲየም መግቢያ ቲኬት የሚሰራጨው በንብረት ክፍል ሠራተኛ መሆን ሲገባው በፀሐፊነት ተግባር ላይ በተሰማሩት ሰራተኛ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በሥራ ክፍሎች ውስጥ መሟላት የሚገባው የሰው ኃይል አለመሟላቱ፣ መያዊ ብቃትና ችሎታ በሌላቸው ሠራተኞች መሰራቱ፣ የውስጥ ኦዲት ክፍል በየመስሪያ ቤቶች ከሚዘረጉት የቁጥጥር ስርዓቶች አንዱ እንደመሆኑ መጠን በፌዴሬሽኑ የውስጥ ኦዲተር ባለመኖሩ ለሙስና በር ከፋች የሆነ ብልሹ አሰራር እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ክፍያዎች ሲፈፀሙ ያለቃለ ጉባኤ ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ራሳቸው ክፍያ እንዲፈፀም ይጠይቃሉ፡፡ ይፈቅዳሉ፡፡ ክፍያውን ይወስዳሉ፡፡ ለራሳቸው ማበረታቻ ይጠይቃሉ፡፡ ራሳቸው ይፈቅዳሉ፡፡ ለራሳቸው ይወስዳሉ፡፡ ይህ የሚደረገው ብሔራዊ ቡድን ባሸነፈበት ወቅትና 29ኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አላሙዲ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ ወቅት ነው፡፡ ይህ አሰራር የክፍያ አጽዳቂዎች እና አመራሮች ለሙስናና ለብልሹ አሰራር እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሊቢያን ባሸነፈበት ሽልማቱ እንዲሰጥ ማን እንደፈቀደ፣ በምን መስፈርት እንደተፈቀደ፣ የሚገልጽ ሰነድ ፌዴሬሽኑ ማቅረብ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ..በጀት ላልተያዘባቸው ጉዳዮች አስቸኳይነቱ ሲታመንበት እስከ ብር 750..000 ወጪ ለማድረግ በቀጣዩ ጠቅላላ ጉባኤ ያሳውቃል.. ተብሎ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 33 ቁጥር 9 ላይ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የስራ አመራሩ ውሳኔ ማሳለፉንና የዚህ ዓይነት አሰረር በውጪው ዓለም የተለመደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ..ክፍያው በቃለ ጉባኤ የፀደቀ ቢሆንም እንኳን የስራ አመራሮች እርስ በእርሳቸው ላበረከቷቸው አስተዋጽኦ ማበረታቻ ገንዘብ ይገባናል በሚል እና የገንዘቡንም መጠን በቃለ ጉባኤ ለራሳቸው ወስነው የገንዘብ ክፍያው እንዲፈፀምላቸው ማድረጋቸው የአሰራር ስርዓቱ ምን ያህል ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ ለዚህም አሰራር ክፍተት የፈጠረው የመተዳደሪያ ደንቡ መሆኑን ለመረዳት ችለናል.. ሲል ሪፖርቱ ለፕሬዚዳንቱ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የትራንስፖርት ክፍያን በተመለከተ በርካታ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ለእያንዳንዳቸው 5ሺ፣ ለፀሐፊው 3ሺ፣ ለፌዴሬሽኑ ገንዘብ ያዥ ብር 3ሺ (በፌዴሬሽኑ ሥራ ገንዘብ ለማውጣታቸው ሰነድ ሳያቀርቡ) ክፍያ መፈፀሙን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ሪፖርቱ እስኪጠናቀቅ የቀረበ ደጋፊ ማስረጃም ሆነ ሌላ ቃለ ጉባኤ የለም፡፡ በርካታ የገንዘብ ወጪ ማዘዣዎች (የቼክ ፔይመንት ቮቸር) በሚመለከተው ባለስልጣን ወይም ኃላፊዎች ሳይፀድቁ፣ የሂሳብ ኃላፊ፣ የገንዘብ ወጪ ማዘዣውን ያዘጋጀው ሰራተኛ፣ የውስጥ ኦዲተር ሳይፈርሙ ክፍያዎቹ በቼክ ተፈጽመው ተገኝቷል፡፡ (ለምሳሌ፣- የገንዘብ ወጪ ማዘዣ ቁጥር 4018፣ 4019፣ 4020፣ 4021፣ 4022 እና 4023፣ 4036) ከላይ ከተገለፁት ክፍያዎች ውስጥ ገንዘብ ያዥዋ ብር 30000.00 እና ብር 3000.00 የተከፈላቸው ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቼኩ የሚቀመጠው ገንዘብ ያዥዋ እጅ ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ አይነት አሰራር በገንዘብ ያዥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰራተኛ በቼክ ላይ የኃላፊዎችን ፊርማ አስመስለው በመፈረም ገንዘብ ማውጣት እንዲችሉ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ስለሆነም የገንዘብ ወጪ ማዘዣው በገንዘብ ያዥና በገንዘብ ተቀባይ ፊርማ ብቻ እየተከናወነ መሰራቱ የክፍያ አፈፃፀሙ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ በፌዴሬሽኑ የግዢ ሥራ ሲከናወን ወጥነት ያለው መመሪያ የለም፡፡ ግዢዎች የሚካሄዱት በልምድ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ያዘጋጀው የግዥ መመሪያ ለሙስና በር የሚከፍት በመሆኑ ሳይፀድቅ ሊመረመር እንደሚገባው ያመለከተው የኮሚሽኑ ጥናት እስካሁን በፌዴሬሽኑ የተፈፀሙ ግዢዎች ለሙሰናና ለብልሹ አሰራር ከፍተኛ ክፍተት የሚፈጥር ነው.. በማለት ሪፖርቱ ምሳሌ ያስቀምጣል፡፡ በጥናቱ ወቅት ሦስት የቼክ ክፍያዎች ማለትም፡- ብሔራዊ ቡድኑ አሸንፎ ስለመጣ ሽልማት የተሰጠ በሚል ቼክ ቁጥር 1128700 ብር 3000.00 የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፀሐፊ፣ ቼክ ቁጥር 1128737 ብር 3000.00 ለፌዴሬሽኑ ፀሐፊዋ፣ ቼክ ቁጥር 1128735 ብር 3000.00 ከፌዴሬሽኑ ገንዘብ ያዥ ያለ ክፍያ ማስመስከሪያ (ያለ ገንዘብ ወጪ ማዘዣ) ገንዘብ ተቀባዮቹ ሳይፈርሙ ክፍያ ተፈጽሞ ተመልክተናል፡፡ ይህ አሰራር የፋይናንስ አያያዝ ስርዓትን ያልተከተለ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሙስና የሚያጋልጥ ነው፡፡ ባዶ ቼክ ማስቀመጥ፣ ቼክ እና የክፍያ ማስመስከሪያ ማዘጋጀት ገንዘብ ያዧ ራሳቸው የሚያከናውኑበት ሁኔታ በፌዴሬሽኑ ስላለ አሰራሩ ያለ ኃላፊ ፈቃድ ክፍያ እንዲፈፀም ከማድረጉም በተጨማሪ ሙስና እንዲፈፀም የሚገፋፋ ነው፡፡ ንብረት አያያዝን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ መመሪያ የለውም፡፡ ንብረት በአግባቡ አይመዘገብም፡፡ የንብረት ቆጠራም አይደረግም፡፡ በሌላም በኩል ፌዴሬሽኑ የራሱ የሆነ የፀደቀ ድርጅታዊ መዋቅር የለውም፡፡ የሰው ኃይል ፍላጎቱ ዝርዝርና የቅጥር መመሪያው አይታወቅም፡፡ ባለሙያ ከገበያ አወዳድሮ አይቀጥርም፡፡ የተቀጠሩ ሰራተኞች የቅጥር ሁኔታ ለማጣራት ለናሙና ማህደሮቻቸው እንዲቀርብ ተጠይቆ ሊቀርብ አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ ፌዴሬሽኑ የሰራተኞች ቅጥርን ያለውድድር፣ በመተዋወቅ፣ በዝምድና እንዲፈፀም ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ይህ አሰራር ኃላፊዎቹን ለሙስናና ለብልሹ አሰራር እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡ በፌዴሬሽኑ የክፍያ ሰነዶች በየሂሳብ ዓይነታቸው የሚቀመጡበት ስርዓት ባለመኖሩ የተነሳ የተለያዩ የሂሳብ ሰነዶች በአንድ ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ለአንድ ተግባር በድጎማ የሚሰጡ፣ የፊፋ ሂሳቦች፣ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ከራሱ ገቢ የሚጠቀምባቸው የሂሳብ ሰነዶች ለየብቻ የሚያዙበት (ተለይተው የሚቀመጡበት) ስርዓት የለም፡፡ የባንክ ክፍያ ሰነዶች በየባንክ ሂሳብ አካውንታቸው ተለይተው ለየብቻ የሚያዙበት የሂሳብ ሰነድ አያያዝ ስርዓት የለም፡፡ ይህ አሰራር ተቆጣጣሪ አካል ቁጥጥር ማድረግ እንዳይችል እንዲሁም ገቢና ወጪውን በየሂሳብ አይነታቸው ለይቶ ኦዲት ማድረግ እንዳይቻል ስለሚያደርግ አሰራሩ የቁጥጥር ስራን በማዳከም ሙስና እንዲፈፀም በር ከፋች ነው፡፡ ለጥቃቅን ክፍያዎች መክፈያ ሰነድ በፌዴሬሽኑ መኖሩ ጥሩ ጅምር ቢሆንም የ ፒቲ ካሽ ሲስተም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሆኗል ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ለፒቲ ካሽ የተመደበ የገንዘብ መጠን የለም፡ ፒቲ ካሽ የሚተካው ምን ያህል ገንዘብ በገንዘብ ያዧ እጅ ሲቀር እንደሆነ የተቀመጠ አሰራር የለም፣ በካዝና ምን ያህል የገንዘብ መጠን መቀመጥ እንዳለበት የተደነገገ ነገር የለም፣ የ ፒቲ ካሽ ሰነዶችን ገንዘብ ያዥና ሂሳብ ክፍል የሚረካከቡበት ስርዓት የለም፣ የ ፒቲ ካሽ ሂሳብ የሚመዘገብበት መዝገብ የለም፡፡ ፌዴሬሽኑ ይህንን ችግር ለመፍታት በረቂቅ የፋይናንስ መመሪያው ላይ ለማካተት መሞከሩን ጥሩ ጅምር መሆኑን የገለፀው ሪፖርቱ ..ሆኖም ረቂቅ መመሪያው ላይ ስለ ፒቲ ካሽ መዝገብ አያያዝ እንዲሁም ቁጥጥር ስርዓቱን በተመለከተ የተገለፀ ነገር የለም፡፡.. በማለት ጉድለቱን ያመለክታል፡፡ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ የፌዴሬሽኑ ጉዳይ አልባት እያገኘ ባለበት ወቅት ጥናቱ ይፋ መደረጉን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ..የአሰራር ስርዓቱ ተጠናም አልተጠናም በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቅ ጉዳይ ከተገኘ የትኛውም አካል ይጠየቃል.. በማለት መልሰዋል፡፡ ..ዋናው ዓላማችን የሙስናን ወንጀል መመርመር ሳይሆን የአሰራር ስርዓቱን ማስተካከሉ ላይ ነው.. ያሉት አቶ ብርሃኑ የቀድሞ አመራር ቢቀየርም የአሰራር ስርዓቱ መቀየር እንዳለበት ኮሚሽኑ ያምናል፡፡ ከዚህ በፊት በፌዴሬሽኑ አሰራር ላይ ጥናት መደረጉን በጥናቱ መሰረት ለውጥ ቢኖርም የተፈለገውን ያህል ሆኖ ባለመገኘቱና አሁን በተግባር እንደሚታየው ፌዴሬሽኑ ችግር ላይ በመሆኑ የአሰራር ጥናቱን ይፋ ማድረጉ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡ ሪፖርቱ በትናንትናው ዕለት ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተላከ እንደሆነ የገለፁት አቶ ብርሃኑ ..ፌዴሬሽኑ በአስር ቀን ውስጥ የጽሁፍ መልስ እንዲሰጥ ተጠይቆ፣ ከተጠቀሰው ቀን በላይ ቢጠብቅም መልስ አልሰጠም.. ብለዋል፡፡ ..የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ወርዶፋ በቀለና ከምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አርአያ ተስፋዬ ጋር ውይይት የተደረገበት በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ሪፖርቱን መቀበል አለበት.. በማለት አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
|
| Last Updated ( Saturday, 12 January 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |