| "ገበሬው ዓሣን ለገበያ ብቻ ሣይሆን... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
"ገበሬው ዓሣን ለገበያ ብቻ ሣይሆን ለቤተሰቡ የምግብ ፍጆታም እንዲጠቀምበት ማድረግ አለብን"አቶ ካሣሁን አሳምነው (የብሔራዊ አሣና የውሃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር) አቶ ካሣሁን አሳምነው የብሔራዊ አሣና የውሃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ማዕከሉ በይበልጥ በአሣ ምርምር ዙሪያ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በማዕከሉ እንቅስቃሴ ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ምን እየሠራ ነው? አቶ ካሣሁን፡- ማዕከሉ ሲቋቋም አሣን በማዕከል አምርቶ አሣ በሌላቸው ትናንሽ የውሃ አካላት ውስጥ በመጨመር የአሣ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ታስቦ ነው፡፡ ይህንን ተግባሩን ለሃያ ዓመታት እያከናወነ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንደ አዲስ በሚቋቋምበት ጊዜ ይህንን ማዕከል ከግብርና ሚኒስቴር ወጥቶ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ጋር ተዋህዶ የአሣ ምርምር በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ በአዋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በእኛ ገበሬ በቀላሉ ሊተገበሩ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅም ሆነ ከሌላ ቦታ አምጥቶ በማዳቀል እየሠራ ነው፡፡ አንደኛው በተፈጥሮ ውሃ አካላት ላይ የምንሠራው ሲሆን በዚህ ሥራ በይበልጥ ማኔጅመንቱ ላይ በማተኮር ፊሽሪና ኒሞኖሎጂ በሚባል ፕሮጀክት በሐይቆችና በወንዞች ላይ የምንሠራው ነው፡፡ ዋና ዋና ሐይቆች ላይ የምርት መጠኑ ምን ያህል ነው? በዓመት ምን ያህል መመረት አለበት? ምን ያህል አሣ አስጋሪዎች መኖር አለባቸው? የሚለውንና የመሳሰሉትን ጥናቶች ሠርተን ለፖሊሲ አውጭዎች የጥናታችንን ውጤት እናቀርባለን፡፡ በተጓዳኝም የአሣውን አረባቡንና የአመጋገብ ሥርዓቱን እናጠናለን፡፡ የውሃውን የጥራት ደረጃ እናጠናለን፡፡ የተፈጠሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ትናንሽ ሐይቆች ሆነው ነገር ግን አሣ የሌለባቸው ቦታዎች ላይ ጥናት አድርገን ምን ዓይነት የአሣ ዝርያ ቢጨመር ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚለውን ካገኘን በኋላ ተስማሚ የአሣ ዝርያ እንጨምራለን፡፡ ውጤቱንም አይተን በአካባቢው ያሉትን ገበሬዎች ስልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ሪፖርተር፡- አሣ ጨምራችኋል? አቶ ካሣሁን፡- በስልጤ ዞን ትንሿ አባያ የምትባል ሐይቅ ላይ ይህንን ሥራ ሠርተን ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ገበሬው ተደራጅቶ ማምረት ጀምሯል፡፡ በቀጣይነት መሥራት ያለብን በገበሬው ላይ ያመጣውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦችን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ገበሬው ምርቱን አዲስ አበባ ድረስ በመላክ እየሸጠ በመሆኑ የሠራነው ሥራ ያመጣውን ለውጥ ልንመለከትበት የምንችልበትን የሶሺዮ ኢኮኖሚ ጥናት እናደርጋለን፡፡ ሪፖርተር፡- በሌሎች አካባቢዎች የሠራችኋቸው ተመሳሳይ ሥራዎች አሉ? አቶ ካሣሁን፡- አሉ፡፡ በፊንጫአ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር ግድብ ላይ እንዲህ ሠርተን ምርት እየተመረተ ነው፡፡ ሌላው ልንጀምር ያሰብነውና ጥናት ላይ ያለው ደግሞ በዝዋይና በአዋሳ ሐይቆች ላይ ከአቅም በላይ የሆነ የአሣ ማስገር (ኦቨር ፊሺንግ) ይካሄድባቸዋል፡፡ ይህን ለማስቀረት መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች ውስጥ አንደኛው ለተወሰነ ጊዜ ሐይቁ እንዲዘጋ ማድረግ ነው፡፡ ካልሆነም በተወሰነ ደረጃ መዝጋት ይቻላል፡፡ አሣ ለማራባት በሚፈልግበት ጊዜ ዳር ላይ ይመጣል፡፡ እንቁላሉ ዳርቻ ላይ ነው የሚጥሉት በሚመጣበት ጊዜ ሰብስበው ይወስዱታል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጫጩቱንና የመሳሰሉትን ከጥቅም ውጭ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም በዚህ ወቅት እንዲዘጋ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሪፖርተር፡- ከአቅም በላይ እንዳይመረት ለማድረግ መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች ለመውሰድ ያልተቻለው ለምንድነው? አቶ ካሣሁን፡- መረጃውን መስጠት እንጂ እርምጃዎችን ለመውሰድ አንችልም፡፡ ግን የውሃ አካላቱ ካሉባቸው አስተዳደሮችና ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በላይ የሚደረገውን የአሣ ማስገርን ለማስቀረት በቅንጅት እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን እርምጃ ለመውሰድና ተግባራዊነቱ ላይ ብዙ ጠንካራ አይደለንም፡፡ ሌላው ለዚህ ኦቨር ፊሺንግ ለምሣሌ በዝዋይ ከሚገባው በላይ እየተጠመደ ያለው ቆሮሶ የሚባለው አሣ ነው፡፡ የቆሮሶ ዝርያን በሰው ሠራሽ ዘዴ እያራባን ሐይቁ ውስጥ በመጨመር መፍትሔ ለመፈለግም እየጣርን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በዝዋይ ሐይቅ አካባቢ ያገኘናቸው አሣ አስጋሪዎች ከዓመት ዓመት የምናመርተው የአሣ ምርት ቀንሷል እያሉ ነው፡፡ ትንንሽ አሣዎች እየተጠመዱ ነውና ይህ ችግር በሌሎች ሐይቆችም ላይ ይታያል? አቶ ካሣሁን፡- አዋሣ፣ አባያና ጫሞ ሐይቆች ተመሳሳይ ችግር አለባቸው፡፡ በቆቃ አካባቢ ደግሞ ገበሬው ጥሩ የአሰጋገር ችሎታ አለው፡፡ ትናንሽ አሣዎችን ሲያገኝ ወዲያው ወደ ውሃው ውስጥ ይመልሳል፡፡ የማጥመጃ መረቡን መጠን በሚገባ ይቆጣጠራል፡፡ በኦቨርፊሺንግ ዙሪያ በሚቀጥለው ወር በተለያዩ ሐይቆች አካባቢ ያሉ አሣ አስጋሪዎች እንዲሰለጥኑ እናደርጋለን፡፡ እኛ የምንነግራቸውን ብቻ ሣይሆን እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡ በማድረግ ሃብቱን እንዲንከባከቡና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ (ኢንደሚክ) የሚባሉ አሣዎቻችንም እንዳይጠፋ እየሠራን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አገሪቱ ያላት የአሣ ሃብት ምን ያህል ይሆናል? አቶ ካሣሁን፡- በአገራችን ከ40 እስከ 50 ሺህ ቶን በዓመት መመረት ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ በዋና መንገድ ላይ ያሉት ሐይቆች ከአቅም በላይ እየተመረተባቸው (ኦቨር ኤክስፕሉት) እየተደረጉ ነው፡፡ ራቅ ያሉትና ለትራንስፖርት ምቹ ባልሆኑት ግን ከሚገባው በታች ነው፡፡ ደግሞ ምርት አይመረትባቸውም፡፡ ማንም እየተጠቀመባቸው አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ማድረግ ያለብን እዚያ ያለው ገበሬ ይህንን ሃብት እንዲጠቀምበት ማድረግ ነው፡፡ ለገበያ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡ የምግብ ፍጆታም እንዲጠቀምበት ማድረግ አለብን፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ የአሣ ምርት የሚገኝባቸው ሐይቆች የትኞቹ ናቸው? አቶ ካሣሁን፡- ጣና፣ ዝዋይ፣ አዋሣ፣ አባያ፣ ጫሞ እነዚህ ብዙ የአሣ ምርት የሚመረትባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ ብዙ ምርት ልናገኝባቸው የሚችሉ ወንዞቻችንን ግን እየተጠቀምንባቸው አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- በወንዞች ላይ ብዙ ምርት ማግኘት ይቻላል? አቶ ካሣሁን፡- ማግኘት ይቻላል፡፡ ትልቅ እምቅ ሃብት አለ፡፡ ጋምቤላ አካባቢ ያለው ገበሬ ከሌሎች አካባቢዎች ካሉት ሲወዳደር አሣን የመጠቀም ባህሉ ጥሩ ነው፡፡ ባሮ ወንዝ አሣ ይመረትበታል፡፡ ሌሎች ብዙዎቹ የአገሪቱ ወንዞች ግን ለአሣ ምርት እየዋሉ አይደሉም፡፡ ሪፖርተር፡- በአሣ ኢንቨስትመንት የተሠማሩና ፈቃድ የወሰዱ ብዙ ኩባንያዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ እያለሙ ነው? አቶ ካሣሁን፡- በአሣ ኢንቨስትመንት ላይ ይሠማራሉ የሚባሉ ኢንቨስተሮች ብዙዎቹ ኢንቨስት ማድረግ ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ ቶሎ ወደ ሽያጭ ለመግባት ሲሉ መጠቀም የሚፈልጉት የተፈጥሮ ውሃዎችን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በቀላሉ ብዙ ወጪ ሳያወጡ ለማምረት ስለሚፈለጉ የተፈጥሮ ውሃ ውስጥ ገብተን ማምረቱ ነው ቶሎ አዋጭ የሚሆነው የሚለውን እምነት ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ኢንቨስትመንት ከሆነ ጨምረው ነው መሸጥ ያለባቸው፡፡ መሥራት ያለባቸው በአሣ ግብርና ላይ መሆን አለበት፡፡ በተፈጥሮ ላይ ብቻ ትኩረት ወጥተው የሚሠሩ ከሆነና በተፈጥሮ ሃብቱ ላይ ሒውማን ኢንተርፈረንስ በሚኖርበት ጊዜ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢኮ ሲስተሙን ልታበላሽ ትችላለህ፡፡ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ቦታ ወስደው በትናንሽ የውሃ አካላት ላይ ቢሠሩ ይመረጣል፡፡ ብዙ አነስተኛ የውሃ አካላት ያሉባቸው ቦታዎች ስላሉ በእነሱ ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉ ይበልጥ ይመረጣል፡፡ ሪፖርተር፡- ማዕከላችሁ የአሣ ሃብትን ለማሳደግና በቅርብ ጊዜ ለማከናወን ያቀደው ምንድነው? አቶ ካሣሁን፡- በአሣ ግብርናና በተፈጥሮ ውሃ አካላት ላይ ጥናት እያደረግን ነው፡፡ በተጠናከረ መልኩ በአሣ ግብርና ላይ ጥናት ለማድረግ አቅደናል፡፡ ይህንን የምናደርገውም ከዚህ በፊት አሣ በማይታወቅባቸው አካባቢዎች ጣልቃ በመግባት በማድረግ የአሣ ምርትን ለማሳደግ ገበሬው ይህንን ምርት እንዲያመርትና ለምግብነት እንዲጠቀምበት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ለመስኖ ተብለው በሚሠሩ ውሃዎች ላይ ገብተን መሥራት ያስችለናል፡፡ በተወሰነ ጊዜ በዝናብ ወቅት በሚሰበሰብ ለምሳሌ ውሃ በማቆር የአሣ ግብርና ቴክኖሎጂን ማስገባት ይቻላል፡፡ በዚህ አካባቢ ትልቅ እምቅ ሃብት አለ፡፡ የተፈጥሮ ትናንሽ የውሃ አካላትም በየቦታው አሉ፡፡ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ምርትን ማሳደግ ይቻላል የሚል እምነት ስላለ በዚህ ዙሪያ ብዙ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ በተፈጥሮ የውሃ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስና የአሣ ዝርያዎቻችን እንዳይጠፉ ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ዝዋይ ላይ እንደተመለከትነው አንድ አሣ በአንድ ብር ይሸጣል፡፡ አዲስ አበባ ሲገባ አንዱ ኪሎ እስከ 2ዐ ብር ይሸጣል፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? አቶ ካሣሁን፡- እንዲህ ያለ ነገር የሚከሰተው በመሀል ላይ ነው፡፡ ይህንን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እያገኘ ያለው አሣ አስጋሪው አይደለም፡፡ የአሣ ነጋዴው ከአስጋሪው ይቀበልና የትራንስፖርት ወጪ ስላወጣ ብቻ በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣል፡፡ አንዳንዴ አሣ የማስገርን ሥራ የሚያደክመው ይሄ ነው፡፡ አሣ አስጋሪው ይለፋል፣ ሌሊቱን ሙሉ ሲሠራና አሣ ሲያሰግር አድሮ የሚያገኘው ገንዘብ በጣም ትንሽ ነው፡፡ አስጋሪው ትክክለኛ ጥቅሙን ካገኘ ደግሞ ሃብቱን ይጠብቃል፡፡ ሕይወቱ ይለወጣል፡፡ ተጠቃሚውም በተመጣጠነ ዋጋ አሣ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- የአሣ ምርትን ከማሳደግ አኳያ አዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቦምሣ በሚባል ፕሮጀክት ዙሪያ እየሰራችሁ ነው የቦምሣ ፕሮጀክት ዋነኛ ዓላማ ምንድነው? አቶ ካሣሁን፡- የዚህ ፕሮጀክት አላማው በኤጅ ወይም ከአሣ መረብ የተሠራ ሣጥን (ኬጅ) በትንሽ የውሃ አካላት ውስጥ ወይም ሲዝናል በሆነ የውሃ አካል ውስጥ አሣን በኬጅ አስቀምጦ የማሳደግ ወይም የማራባት ዘዴ ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ለገበሬው ተጨማሪ ገቢ በማስገኘት እንዲጠቀም ያስችላል፡፡ ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ በጣም ቀላል በመሆኑ በቀላሉ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ቴክኖሎጂው አሁን የሚታየውን በተፈጠሮ የውሃ አካላት ላይ ያለውን የአሣ አስጋሪዎች ፕሬዥርም ይቀንሳል፡፡ ቴክኖሎጂው በትንሽ ሰው ማኔጅ የሚደረግ በመሆኑም ይመረጣል፡፡ በሌላ በኩልም በአሣ ማስገር ሥራ ውስጥ ሴቶች ብዙ ጊዜ ተሳታፊ አይደሉምና በዚህ ቴክኖሎጂ ግን ሴቶችን ወደ አሣ ማስገር ውስጥ እንዲገቡ ያስችላቸዋል፡፡ ሌላው የዚህ ቴክኖሎጂ ጥቅም ገበሬው ሸጦ ከሚያገኘው ጥቅም በተጨማሪ ለቤተሰቡ ፕሮቲን ያለበትን ምግብ እንዲያገኝ ለማድረግ ሲባል ያስገባነው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ይህንን ቴክኖሎጂ ማንኛውም ገበሬ በግቢው ውስጥ መጠቀም ይችላል? አቶ ካሣሁን፡- ይህንን ቴክኖሎጂ በተፈጥሮ ውሃ አንጠቀምም፡፡ በተፈጥሮ ውሃ ውስጥ የማንጠቀመው ለሚራቡት አሣዎች ምግብ ስለምንጨምርና ይህንን ስናደርግ ደግሞ የተፈጥሮ የውሃ አካሉን የተፈጥሮ ሲስተም ስለምናበላሽ ነው፡፡ ነገር ግን ለመስኖ የተገደቡ ግድቦች፡፡ ትናንሽ ወይም በተወሰነ ጊዜ ብቻ ውሃ የሚያቁሩ በበጋ የሚደርቁ የውሃ አካላት ላይ አሣ ጨምረን ማምረት እንችላለን፡፡ ሪፖርተር፡- በሞቦሣ ፕሮጀክት ኬንያ ያገኘችውን ውጤት ለመጠቀም አላቀዳችሁም? አቶ ካሣሁን፡- በዚህ ፕሮጀክት ኬንያውያን ውጤት እያገኙበትና ቴክኖሎጂውን እያስፋፉት ነው፡፡ ገበሬውም በስፋት እንዲጠቀምበት እየተደረገ ነው፡፡ ገንዘብ በማግኘታቸውና ቤተሰባቸውም አሣ በመመገባቸው በጤናቸውና በአኗኗራቸው ላይ ለውጥ እያገኙበት ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን ለማስገባት የፈለግነው የኬንያውያኑን ውጤት አይተን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በእኛ አገር ይህ ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? አቶ ካሣሁን፡- በእኛ አገር ይህንን ቴክኖሎጂ ለማስፋፋት እንዲቻል በሙከራ ደረጃ በሁለት ቦታ ተጀምሯል፡፡ አንደኛው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ አጣዬ አካባቢ ሲሆን ሁለተኛው አላጌ ግብርና ኮሌጅ ውስጥ ነው፡፡ በተለይ አንደኛውን የሙከራ ጣቢያ አላጌ ያደረግንበት ምክንያት በኮሌጁ የግብርና ሰልጣኞች ያሉበት በመሆኑ ቴክኖሎጂውን እንዲያዩና እኛም ስለቴክኖሎጂው ሰልጣኞቹ ስልጠና ለመስጠት እንዲያስችለን ነው፡፡ እነዚህ ሰልጣኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ይህንን ቴክኖሎጂ ይዘው እንዲሄዱ ለማድረግ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አንድ ገበሬ በግቢው ውስጥ አሣ ማርባት ቢፈልግ ምን ያህል አሣ ሊያመርት ይችላል? አቶ ካሣሁን፡- እኛ ልንሠራ ያቀድነው 1.6 በአንድ ሜትር ካሬ በሆነች ኬጅ ነው፡፡ አንድ ኪውቢክ ሜትር እንኳን የማይሞላ ማለት ነው፡፡ በዚህች ሣጥን በዓመት 500 ኪ.ግ አሣ ማርባት ይቻላል፡፡ ሪፖርተር፡- በዚህ ቴክኖሎጂ የሚራቡ አሣዎች የሚመገቡት ምንድነው? አቶ ካሣሁን፡- ቴክኖሎጂውን ለየት የሚያደርገው ይህ ነው፡፡ በሙከራ ጣቢያዎቻችን ለጊዜው እያደረግን ያለነው ፉርሸካ፣ የቢራ ተረፈ ምርት ወዘተ. ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ፕሮጀክት አንዱ ዓላማ ራሱ በቅርብ የሚገኙ ተረፈ ምርቶች መጠቀም መቻል ነው፡፡ ለምሳሌ በአጣዬ የሙከራ ቦታ ላይ ገበሬው የማይጠቀምበትና ይጣሉ የነበሩ አንዳንድ ተረፈ ምርቶችን ፕሮሰስ አድርገን እየተጠቀምን ነው፡፡ ውጤትም ታይቶበታል፡፡ በየቦታው ይህ ቴክኖሎጂ ሲስፋፋ ተረፈ ምርቶችን ለአሣዎቹ ምግብነት እንዲውሉ በላቦራቶሪ መርምረን እንጠቀማለን፡፡ በቤተ የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረግን ነው፡፡ በኬንያ ያለውም ይህ ነው፡፡ ወጪ የማይጠይቅ በአካባቢ የሚገኝ ተረፈ ምርትን በመመገብ ሥራውን መሥራት ይቻላል፡፡ ሪፖርተር፡- ገበሬው ይህንን ቴክኖሎጂ ልጠቀም ቢል የሚያረባቸው አሣዎችን ከየት ያገኛል? አቶ ካሣሁን፡- የምንሰጠው እኛ ነን፡፡ ለጊዜው በሽያጭ ሳይሆን በነፃ ነው፡፡ በአገራችን አሣን የመመገብ ባህል አነስተኛ በመሆኑ አሁን ባለንበት ደረጃ ለማበረታት በነፃ ነው የምንሰጠው፡፡ በኋላ ላይ ግን የተወሰነ ገበሬዎች አሣን እንዲያረቡና ያረቡትን የአሣ ጫጩት ቀልበው ለሚያሳድጉ እንዲሸጡ ነው፡፡ ግማሹ ጫጩቶችን ቢሸጥ ግማሹ አሳድጐ እንዲሸጥና ሁሉም የየራሱ የሆነ ኃላፊነት እንዲኖረው ማስቻል ነው፡፡ አጣዬ ላይ ገበሬዎች ሱቅ ከፍተው እየሸጡ ነው፡፡ በዚያ አካባቢ አሣ አይታወቅም ነበር፡፡ አሁን ግን ለራሳቸውም ለገበያም እያቀረቡ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |