| ጥቂት ነጥቦች ስለክብረ ነገሥትና... |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
ጥቂት ነጥቦች ስለክብረ ነገሥትና ስለአማርኛው ትርጉምክብረ ነገሥት ከግእዝ ወደ አማርኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ተተርጉሞ የታተመው በ1994 ዓ.ም ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል አማካይነት ተርጉመው ያቀረቡት አቶ ሥርግው ገላው ናቸው፡፡ በመጽሐፉ በአንዱ ገጽ በግእዝ፣ በትይዩው ገጽ የአማርኛው ትርጉም የቀረበበት ቢሆንም የአማርኛው የፊደል አጠቃቀም በ1973 ዓ.ም የቀድሞው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በረቂቅ ደረጃ በወሰነው የፊደል ገበታ መሰረት የተሰራ፣ ሕጋዊ የአካዳሚ ውሳኔ ባልተሰጠበት ፊደላቱን የቀናነሰ በመሆኑ፣ በተለይም የመጽሐፉ ርእስ በኩሩን ግእዝ ያከበረ ሳይሆን፣ ባልተጻፈበት ፊደል የተጻፈ በመሆኑ ብዙዎችን አላስደሰተም፡፡ ክብረ ነገሥቱን ወደ አማርኛ በመተርጐም ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲገናኝ ያደረጉት ተርጓሚው መምህር ሥርግው ዐቢይ ተግባር የፈጸሙ ቢሆንም፣ ሁለተኛው እትም በሚወጣበት ጊዜ በግእዙ እትም ሆነ በአማርኛው ላይ የታዩትን ግድፈቶች ተስተካክለው እንደሚቀርቡ ተስፋ አለን፡፡ ክብረ ነገሥት ስለተጻፈበት ዘመን በግእዙም ሆነ በአማርኛው ትርጉም የተጻፈውን ተርጓሚው በግርጌ ማስታወሻ ያመላከቱት ዝበት አለው፡፡ “በዐረብኛውም መጽሐፍ ከወንጌላዊውና የሁላችንም መምህር ከሆነው ከማርቆስ መንበር በ409 ዓመተ ምሕረት የቅጽል ስሙ ላሊበላ በሆነው በንጉሥ ገብረ መስቀል ዘመንና በቸሩ ጳጳሳችን በአባ ጊዮርጊስ ዘመን ከቅብጢ ቋንቋ ወደ ዐረብኛ ቋንቋ ተረጎምናት ተባለ፡፡” ስለ ዘመኑ አቶ ሥርግው በግርጌ ማስታወሻው ሲያብራሩ “409 ዓ.ም የሚለው ከላሊበላ ዘመነ መንግሥት ጋር አይቀራረብም፡፡ ይልቁንስ ዓመተ ሒጅራ ይመስላል፡፡ ሒጅራ የሚጀምረው በ622 ዓ.ም ነው፡፡ 622+409 = 1031 ይሆናል፡፡" ተርጓሚው ከዓመተ ሒጅራ ጋር ማዛመዳቸው ስህተት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ “ዓመተ ምሕረት” በሚል መጠርያ የሚታወቅ ከዐቢይ ቀመር (532 ዓመት) ጋር የሚዛመድ አቆጣጠር አለ፡፡ ዘመነ ላሊበላ ወደ ዓመተ ዓለም ለውጦና ለ532 አካፍሎ የሚገኘው ዓመተ ምሕረት” ይባላል፡፡ ክብረ ነገሥት የተጻፈው በአፄ ዐምደ ጽዮን ዘመን ሲሆን፣ በ117 ምዕራፎች የተከፈለ ነው፡፡ ተተርጐመበት የተባለው የዐረብኛው ቅጅ ግን በጣም አጭር ከመሆኑም በላይ እንደ ግእዙ በስፋትና በዝርዝር አይተርክም፡፡ የግእዙ ክብረ ነገሥት የተገኘው በደቡብ ትግራይ ማይ ነብሪ ከሚባለው ከተማ በቅርበት ከሚገኘው ናዝሬት ከተባለው ስፍራ ነው፡፡ ናዝሬት የአፄ ዐምደ ጽዮን ቤተ መንግሥት የነበረበት ሲሆን፣ አጠገቡ የደብረ ዘይት በዓል የሚከበርበት የሰንበት ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን "ዘግሬተር ኢትዮጵያ" ረትልቋ ኢትዮጵያሪ በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ክብረ ነገሥት የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትልቁ ፈጠራ ነው፡፡ በ1650 ዓ.ም ገደማ አባ ጎርጎርዮስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ጆብ ሉዶልፍ ለተባለ ጀርመናዊ ክብረ ነገሥት “ዐቢይ ዕውቀት ያላቸው የአገሬ ሰዎች፣ የጻፉት ነው” ብለው ነግረውታል፡፡ ከኢትዮጵያና ከቅርብ ምሥራቅ ባህሎች የተጻፉ ጽሑፎችና የቃል ታሪኮች ይገኙበታል፡፡ “እኔ ክብረ ነገሥትን የተረጐምኩት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ ብቻ ነው” ብሎ ይስሕቅ የካደበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ መታወቅ የሚገባው እውነት ክብረ ነገሥት በሀገር ፍቅር ስሜት የተሞላና ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የኢትዮጵያን ማነንት በሚያኮራ መልክ የሚያበስር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በቀደምቱ ዘመን ድርስቶቻቸውን ጻፍነው ከሚሉ ይልቅ ለባዕድ ሀገር መስጠትን ሥራዬ ብለው ይዘው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሔኖክ ያሬድ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |