| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
(ክቡር ሚኒስትሩ ከነበሩበት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ተዛውረው በሌላ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፡፡ አንዳንዶቹ እንደ እድገት ቆጥረውታል፡፡ ለአንዳንዶቹ አማካሪዎች የሚባሉት ግን ሚኒስቴርም ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስትርም ሚኒስትር ነው፡፡ በለመዱት መንገድ ለማማከር እየተንቀሳቀሱ ናቸው)
- እንግዲህ ያው አዲስ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እንደተለመደው ተጠናክረን ሥራችንን መቀጠል ነው፡፡ - ትክክል ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ በተቻለን መጠን ይፈፀሙ የነበሩት ድክመቶች እንዳይደገሙ እየተጠንቀቅን መቀጠል ነው፡፡ - ምን ስህተቶች ይፈፀሙ ነበር? - ክቡር ሚኒስትር፣ በርካታ ስህተቶች ይፈፀሙ ነበር፡፡ እኛ አማካሪዎችም ኤክስፐርቶችም ነን፡፡ ጥፋቱ ሳይባባስ አሁን መንግሥት እሳቸውን አንስቶ እርስዎን መሾሙ እጅግ ደስ ብሎናል፡፡ እሳቸው ባይነሱ ኖሮ ግን ብዙ ችግር ውስጥ እንገባ ነበር፡፡ - የነበሩት ሚኒስትር የተነሱት ደካማ ስለሆኑ፣ ወይ ጥፋተኛ ስለሆኑ እኮ አይደለም፡፡ ስለታመሙና መንግሥት ጊዜ አግኝተው እንዲታከሙ ብሎ ነው እኔን እዚህ የሾመኝ፣ እንጂ እሳቸው ደካማ እኔ ጠንካራ ስለሆንኩ አይደለም፡፡ እንዳትሳሳት፡፡ - ገባኝ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በተቻለ መጠን አጠናክሮ ማስኬድ ይቻል ነበር፤ ማለታችን ነው፡፡ - የትኞቹን ፕሮጀክቶች? - ክቡር ሚኒስትር፣ ሦስቱ ፕሮጀክቶች፤ ሁሉም የሚያውቃቸው ስለሆኑ መዘርዘር አያስፈልግም፤ ብለን ነው፡፡ - እና ሦስቱ ምን መደረግ አለባቸው? - ክቡር ሚኒስትር፣ የጨረታው አሸናፊ መሆን የነበረበት ሌላ ኩባንያ ነው፡፡ የታወቀ ኩባንያ እያለ ለእነሱ ኩባንያ ለምን እንደተሰጠ አልገባንም፡፡ - የእናንተ አስተያየት ምን ነበር? - አሁን ላሸነፈው እንዳይሰጥ፣ ለዚያኛው እንዲሰጥ የሚል ነበር፡፡ ሰሚ አጣን፡፡ ከተፈለገ ግን አሁንም ያለውን ሰርዞ ለዚያኛው መስጠት ይቻላል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ይህን ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡ - የጨረታ ኮሚቴ አልነበረም? - ነበር፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ነገር ግን የጨረታ ኮሚቴው የተስተካከለው ይህ የቢ.ፒ.አር ፕሮግራም ከጀመርን በኋላ ነው፡፡ - በፕሮግራሙ መሠረት ምን አደረጋችሁ? - ክቡር ሚኒስትር ሁሉንም የጨረታ ኮሚቴ አባላት አባረርን፡፡ - ክቡር ሚኒስትር፣ ከኮሚቴው አይደለም ከመሥሪያ ቤቱ ነው የተባረሩት፡፡ የነበሩት ሚኒስትርም አፀደቁልን፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ ለዚያኛው አለመሰጠቱ ግን አሁንም ጨረታውን ማስተካከል አልቻልንም፡፡ - መቸ ነው፤ የጨረታ ኮሚቴው የተባረረው? ሚኒስትሩ ያውቁ ነበር? - ክቡር ሚኒስትር፣ እሳቸው ታመው ደቡብ አፍሪካ ነበሩ፡፡ አስተካክለን እንቆይ ብለን እሳቸውን ሳንጠብቅ አባረርናቸው፡፡ - አሁን የቢ.ፒ.አር. ፕሮግራም ጨርሳችኋል? - ክቡር ሚኒስትር፣ ሰሞኑን ብዙ ሥራ ሰርተናል፡፡ ሌላ ሚኒስትር እንደሚመጣ ስለሰማን አስተካክለን እንቆይ ብለን ብዙ ሥራ ሰርተናል፡፡ - ምን ዓይነት ሥራ? - ያለውን መንግሥት አመላከከት ሊቀበሉ ፈቃደኛ ያልሆኑ፣ አምስት ኤክስፐርት ተብየዎችን አባረናል፡፡ የእነሱን አይተው ሌሎች አምስት ኤክስፐርቶች ደግሞ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራ እንለቃለን፤ ብለው አመልክተው ሄደዋል፡፡ ውስጥ ለውስጥ ሲያጉረመርም የነበረው አኩራፊ ሁሉ ጠራርገን አስወጥተናል፡፡ - በጠቅላላ ስንት ተባረሩ? - ክቡር ሚኒስትር፣ ሰላሳ ይሆናሉ፡፡ - ይህ ሁሉ ሚኒስትሩ ታመው ደቡብ አፍሪካ ባሉበት ወቅትና እኔም እዚህ ሳልመጣ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው? - አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡ - በሉ ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ ረጋ ብለን እናወራለን፡፡ (አማካሪዎቹ ወጡ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ፀሐፊያቸውን ጠሩ) - ደህና ነሽ? - ደህና ነኝ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እየለመዱ ነዎት? - እንጃ". የምታስለምዱ ግን አትመስሉም፡፡ - እንዴት ክቡር ሚኒስትር? - የቢ.ፒ.አር. ፕሮግራም አካሄድ እንዴት እንደሆነ ታውቂያለሽ? ያለፈው የሦስት ፕሮጀክቶች ጨረታ አካሄድ እንዴት እንደነበር የሰማሽው ነገር አለ? - ይኸውልዎት ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ የዚህ ሙያ የለኝም፡፡ ነገር ግን ብዙ የማስታውሰው ጉዳይ አለ፡፡ ሠራተኛውም ዝም ይላል እንጂ ብዙ ያስተውላል፡፡ እና". - እና ምን? - ክቡር ሚኒስትር፣ አሁን ከእርስዎ ጋር የነበሩት አማካሪና ኤክስፐርት ነን የሚሉት ሰው በላዎች ናቸው፡፡ ቢ.ፒ.አር. ብለው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ባዶ አስቀርተውታል፡፡ ምሁርና ባለሙያ የሚባለውን ሁሉ አባረዋል፡፡ ሰራተኛው እያለቀሰ ነው፡፡ - ለምን አቤት አላለም? - ብሏል፡፡ አቤት ብሎ ለእንባ ጠባቂ፣ ለፀረ ሙስና፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ፅፏል፡፡ ተፈራርሞ ልኳል፡፡ መልስ አላገኘም፡፡ ሆን ብለው ደህና ደህና ሠራተኛ እንዳይሰራ እያደረጉ ናቸው፡፡ - በአንድ በኩል ሲታይ መጥፎ የነበሩ የጨረታ ኮሚቴውን ያስወገዱ ይመስላሉ፤ - እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡ የጨረታ ኮሚቴው የወሰነው ትክክል ነበር፡፡ እነዚህ ጉቦ የበሉበት ድርጅት ስላላሸነፈ ነው የተናደዱት፡፡ - ፕሮጀክቱ ግን ጥሩ እየሄደ ይመስልሻል? - ክቡር ሚኒትስር፣ እነዚህ እያሉ እንዴት ጥሩ ይሄዳል? ጥሩ የሚሰራውን አባረሩት፡፡ ማሻሻያ ፕሮግራም እያሉ ነቀሉት፡፡ የሚሠራውን እያነሱ ፕሮጀክቱ ሰው አጥቶ ሲቆም ጨረታው ለሌላ ቢሰጥ ኖሮ ይሠራ ነበር እያሉ ያወራሉ፡፡ የሰሩት ተንኮል አለ፡፡ ክቡር ሚኒስትር፣ እነሱ ከእርስዎ ጋር እያወሩ እያሉ ያ ያላሸነፈው ተጫራች እርስዎ አቤት እንዲል ጠርተውት መጥቷል፡፡ ይግባ ወይስ አይግባ? - ምን እንደሚል መስማት ስለምፈልግ አስገቢው፡፡ (ፀሐፊዋ ወጣችና ሰውየው ገባ) - ክቡር ሚኒስትር እንኳን ደስ አለዎት! - ምን አገኘሁ? - እዚህ በመምጣትዎ ነዋ፡፡ - እዚያም ሚኒስትር ነበርኩ፡፡ - ይህ ትልቅ ቦታ ነዋ፡፡ - ያው ነው፤ ያኛውም ትልቅ ነበር፡፡ - ይህችን ይቀበሉኝ (እየሰጠ) - ምንድነው? - ሰዓት ነች፡፡ - ጉቦ መሆኑ ነው? - ጉቦ አይደለም፡፡ - በል በል ሰዓትህን ይዘህ ውጣ፡፡ ጥፋልኝ፤ ከዚህ ቢሮ፡፡ ሂድ ውጣ፡፡ (ክቡር ሚኒስትሩ ሰውየው የመጣበትን ሳይናገር አባረሩት፡፡ በፀሐፊዋ በኩል የስልክ ጥሪ መጣላቸው) - ሃሎ፡፡ - ሃሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡ የኢ.ሲ.ኤ.ውን ስብሳባ እንዳይረሱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ነው፡፡ - እንዴ? አሁንማ እኔ መሥሪያ ቤት ቀይሬያለሁ እኮ፡፡ - ግድ የለም፡፡ በዚያ ምክንያት እንዳይቀሩ ተብሎ ነው እንድደውል የተነገረኝ፡፡የአገር ጉዳይ ሊነሳ ስለሚችል ይምጡ፡፡ - እሺ ካላችሁ፡፡ (ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ስብሰባው ቦታ ሄዱ፡፡ የስብሰባው መግቢያ ሰዓት እስኪደርስ ከአንድ የውጭ አገር አምባሳደር ጋር እያወሩ ናቸው) - ክቡር ሚኒስትር ምርጫው እንዴት ነው? - በቅርብ አላውቀውም፡፡ ዛሬ በየመንገዱ ገዥው ፓርቲም ተቃዋሚዎችም ሲንቀሳቀሱ ነበሩ፡፡ በየቦታውም ክርክር እየተካሄደ ነው፡፡ ሰላማዊ ነው፣ ጥሩ ነው፡፡ - የዚምባቡዌ ግን ጥሩ አይደለም፡፡ - እንጃ፣ ብዙ አልተከታተልኩትም፡፡ - ሲ.ኤን.ኤን፣ ቢቢሲ ይከታተላሉ የለም? - እሱን እከታተላለሁ፡፡ ግን በጥንቃቄ ነው የምከታተለው፡፡ - እንዴት በጥንቃቄ? - ሙጋቤን አልወደውም፡፡ ነገር ግን የዓለም ሚዲያ ስለሙጋቤ የሚያወራውን እከታተለዋለሁ ማለቴ አይደለም፡፡ - ለምን? - ሙጋቤን ሰይጣን፣ ተቃዋሚን መልዓክ አድርጎ የሚፈርጅ ሚዲያ አልፈልግም፡፡ የተቃዋሚዎችን ድክመትም የሚነግረኝ እፈልጋለሁ፡፡ - እሱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የውጭ ሚዲያ በኬንያ ጥሩ ሥራ ሰርቷል፡፡ አይደል? ሁለቱም ወገን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ አይመስልዎትም ክቡር ሚኒስትር? - አስተዋፅኦ አላደረገም፣ አልልም፡፡ ነገር ግን ያው የተለመደው ደብል ስታንዳርድ አሳይቷል፡፡ - እንዴት? - ሥልጣን እንዲያጋሩ እንጂ ሥልጣን እንዲጋሩ አላደረገም፡፡ አንተ ፕሬዚዳንት፣ አንተ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁኑ የስልጣን ድልድል አድርጉ ነውኮ ያለው፡፡ - ይህ መጥፎ ነው ክቡር ሚኒስትር? - ኢትዮጵያኖች ስንሆን ተጠያቂ ማን እንደሆነ፣ አጣሪ ኮሚቴ ካላቋቋማችሁ ሞተን እንገኛለን አላችሁ፡፡ እናንተ ስላላችሁ ሳይሆን ራሳችንም አጣሪ ኮሚሽን አቋቋምን፡፡ ኬንያ ግን ስልጣን ተጋሩ አላችሁ፤ እንጂ ተጠያቂነት ተጋሩ አላላችሁም፡፡ ከናንተ ፍላጎት ጋር ነው ችግርን የምታዩት እንጂ ከኬንያ ወይ ከኢትዮጵያ ችግር አንፃር አይደለም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር፣ ኢትዮጵያና እዚያ ያለው ይለያያል፡፡ - እውነት እንነጋገር፡፡ የኢትዮጵያን ምርጫ ሂደት ከዚያኛው በእጅጉ የተሻለ አይደለም? - ችግሩ ከምርጫ በኋላ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ከምርጫ በኋላ በተከሰተም ችግር የውጭ እጅ አለበት፡፡ - የውስጥ ችግራችሁ ነው? - የውስጥ ተቃውሞ ነበር ግን ለመፍታት ይቻል ነበር፡፡ ታዛቢዎቹ ረበሹት፡፡ ለነገሩ ሁሉም የውጭ ታዛቢ አይወቀስም፡፡ ካርተር ሴንተር ጥሩ ነበር፡፡ አና ጎሚዝም የረብሻው ተጠያቂ፡፡ - ዋናው ቁም ነገሩ ለቀጣይ ልምድ መገኘቱ ነው፡፡ የሶማሊያና የኤርትራ ጉዳይስ እንዴት ነው፤ ክቡር ሚኒስትር? - የእኛ አቋም ግልፅ ነው፡፡ በሶማሊያ መቆየት አንፈልግም፡፡ የሚተካ የአፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት ሃይል አምጡና ኢትዮጵያ ትውጣ፡፡ ባዶውን ትታችሁ ውጡ ግን ያስቸግራል፡፡ ደህንነታችን እንዲጠበቅ እንፈልጋለን፡፡ - ቦንብ እዚህም እዚያም እየወረወሩ አስቸገሩ አይደል? - ችግሩ የቦንብ አይደለም፡፡ ቦንብ እኛም መወርወር እንደምንችል ከማንም በላይ እነሱም ሻዕቢያም ያውቁታል፡፡ ወታደራዊ ችግር የለብንም፡፡ ነገር ግን የፖለቲካው መረጋጋት ለማምጣት አለም አቀፉ ሕብረተሰብ ግዳጁን መወጣት አለበት፡፡ - አሁንም የኤርትራ እጅ አለበት አይደል? - ከሶማሊያው ችግር በስተጀርባ የሻዕቢያ ችግር አለ፡፡ ከኤርትራው ችግር በስተጀርባ ደግሞ የሌሎች መንግሥታት ችግር አለ፡፡ ይህ ሁኔታ ስላለ ነው ደህንነታችን ጥያቄ ውስጥ ይሆናል የምንለው፡፡ - ኢትዮጵያ ትክክል ናት፣ ክቡር ሚኒስትር? - አዎን ለራሷም ለሶማሊያም ኢትዮጵያ ያደረገችው ትክክል ነው፡፡ - ቀጣዩስ ምንድነው? - አልገባኝም፡፡ - የሻዕቢያ እጅ በሶማሊያ ካለ መጀመሪያ ኤርትራን መምታት የሚል እቅድ ይኖራችኋል ማለት ነው? - አለን የለንም ለማለት አልችልም፡፡ - ኤርትራን የመምታት እቅድ አለን ብለው እንዲነግሩኝ አልጠብቅም፡፡ - አለመጠበቁ ትክክል ነው፡፡ - አለን ባይሉም የለንም ማለት ግን አይደለም፡፡ ተሳሳትኩ ክቡር ሚኒስትር? - ስብሰባው ሊጀመር ስለሆነ ክቡር አምባሳደር እንሂድ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |