| ብረት ሲግል ቀጥቅጥ |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
ከሳሪስ አዲስ ሠፈር ተነስተን ወደ ቀለበት መንገድ የሚያወጣውን አስፋልት ይዘን በመጓዝ ላይ እንዳለን መንገድ ዳር ገርበብ ብሎ የተከፈተ የቆርቆሮ በር ተመለከትን፡፡ የሚቀጠቀጥ ብረት ድምፅም ሰማን፡፡ እዚያ ቤት ውስጥ ምን እንደሚሠራ ለማወቅ ስለጓጓን ቆም አልን፡፡ ጭስ በበሩ እየወጣ ነው፡፡ በድጋሚ ቢላ እርስ በርሱ ሲፋጭ ሰማን፡፡ ወደ ውስጥ ስንበገባ ሁለት ወጣቶች አንደኛው እንጨት ፈቅፍቆ ሲያለሰልስ ሌላኛው ደገሞ ብረት በእሳት ለማቅለጥ ሲታገል አጋጠመን፡፡
ቤቱ ጠባብ ነው፡፡ ጣሪያና ግድግዳው በማዳበሪያና በሳጠራ ተሰርቷል፡፡ በአንድ በኩል ክፍት ነው፡፡ ወለል፣ ግድግዳው ጣሪያ እያልን ለመጥራት እንኳ ይከብዳል፡፡ ፀሐይም ሆነ ዝናብ በቀላሉ ሊገባ ይችላል፡፡ ሥራቸውን በትኩረት በመሥራት ላይ ያሉት ወጣቶች ይህ ብዙም ያስጨነቃቸው አይመስሉም፡፡ ተመቻችተው ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ስለስራቸው ልናነጋግራቸው እንደምንፈልግ እየጠየቅናቸው እያለ አንድ ሌላ ወጣት ወደ ጠባቧ ቤት እየተጣደፈ ገባ፡፡ እነሱን የሚያሠራቸው ይህ ወጣት እንደ ሆነ ገለፁልን፡፡ ደሳለኝ ጋዲሳ ይባላል፡፡ ከክልል ወደ አዲስ አበባ ከመጣ ቆይቷል፡፡ ቀራኒዮ አካባቢ ከታላቅ ወንድሙ ቤት እየኖረ የቀን ሥራ እየሠራ፣ ማታ ማታ ይማር ነበር፡፡ እስከ ስድስተኛ ክፍል እንደተማረ የሚናገረው ደሳለኝ የተሻለ ሥራ በመሥራት ራሱን ችሎ ለመኖ ከወንድሙ ቤት ወጥቷል፡፡ እንደ ቢላ፣ መጥረቢያና ሌሎች ከብረት የሚሠሩ እቃዎችን ከሚሠሩ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ለሰባት ዓመት ያህል ሠርቷል፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለራሱ አሟልቶና ራሱን ችሎ መኖር ስለከበደው ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም፡፡ ሥራውን በከፍተኛ ትጋት በመሥራት ከሚያገኘው አነስተኛ ገቢ ላይ ገንዘብ መቆጠብ ጀመረ፡፡ ከስምንት ወር በፊት ያችን ጠባብ ቤት በመከራየትና ሁለቱን ወጣቶች በመቅጠር የተለያዩ የብረት ውጤቶች መሥራቱን እንደ ጀመረ ነገረን፡፡ “ከጓደኞቼ ጋር በዚህ ሥራ ረዥም ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ ሥራው አድካሚ ቢሆንም ውጤታማ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ጓደኞቼ ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ወደ ሥራው እንድገባ ያደረገኝ እነሱ ለሥራቸው ያላቸው ትጋትና ጥረት ነው፡፡ በመጨረሻም ሥራውን በደንብ ስለለመድኩት ባጠራቀምኩት ገንዘብ በትንሹ ብጀምርስ ብዬ ወሰንኩ” ብሏል፡፡ የጀመረው ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ብር ይዞ ሲሆን ብረት ማቅለጫ፣ መቀጥቀጫና ሌሎች አስፈላጊ መሳሪያዎችን በመግዛት ወደ ሥራው ለመግባት ችሏል፡፡ ደሳለኝና ሁለቱ ጓደኞቹ (ተሻለና ናታ) ከብረት የሚሠሩ የተለያዩ እቃዎችን ቢሠሩም በብዛት የሚሠሩት ቢላዋ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡ የቢላዋ እጀታዎችንም ይሠራሉ፡፡ ለቅልጥፍናና ፍጥነት ሲባል ሥራ ክፍፍል ቢኖርም በዚያች ጠባብ የማምረቻ ክፍል ውስጥ የሚከናወነውን ማንኛውም ሥራ ሦስቱም መሥራት ይችላሉ፡፡ ሌሎች ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በቀን እስከ ሰባ ሁለት ቢላዋ እንደሚሠሩና አብዛኛውን ጊዜም ቢላዎችን የሚያስረክቡት ለነጋዴዎች እንደሆነ የሚናገረው ደሣለኝ የሚያመርቷቸው ቢላዎች በአይነትም በዋጋም እንደሚለያዩ ያስረዳል፡፡ ማረጃ፣ መክተፊያ፣ መቁረጫና መከትከቻ በማለት የተለያዩ የቢላዋ አይነቶችን የሚሰሩ ሲሆን እነዚህ የቢላዋ አይነቶች በመጠንም ሆነ በስለት ልዩነት አላቸው፡፡ ከብረት የሚሠሩ አዳዲስ እቃዎችን ከመሥራት ጐን ለጐን ቢላዎችን ይስላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠሯቸውን ለነጋዴዎች ቢያስረክቡም ለግለሰብም ይሸጣሉ፡፡ ከሁለት ብር እስከ አራት ብር የሚሸጡ ቢላዎች ሲኖሩ በውድ የሚሸጠው የማረጃ ቢላዋ ነው፡፡ “ቢላዋዎቻችንን የሚረከቡን ነጋዴዎች ለሆቴሎች ስለሚያቀርቡ ደውለው ይህን ያህል ቢላዋ ያስፈልገናል ሲሉን ያዘዟቸውን አይነት ቢላዋዎች በመሥራት በሚፈልጉት ጊዜ እናደርሳለን፡፡ እንደዚህ ዓይነት ትዕዛዞች ተደራርበው ከመጡ አምሽተን እንሠራለን” ብሏል፡፡ ለሁለቱ ረዳቶች የሚከፈላቸው በቀን ሲሆን እንደተሠሩት እቃዎች አይነትና ብዛት የዕለት ገቢያቸው ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ብረት ቆርጦ ከማቅለጥ ጀምሮ ሥራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ባለው ሂደት የቀለጠውን ብረት ቅርፅ ማስያዝ በተወሰነ መልኩ ፈታኝ እንደሚሆን ደሳለኝ አልደበቀም፡፡ ብረት በእሳት ማቅለጡም ቢሆን አስቸጋሪ መሆኑን ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ በጥሬ እቃነት የሚጠቀሟቸውን ብረቶች የሚገዟቸው በውድ እንደሆነ በመግለፅ ብረቶች ወደ ተደረደሩበት አመለከተን፡፡ “ሥራው አድካሚ ነው፡፡ ዘወትር እስከ ምሽት አሥራ ሁለት ሰዓት እንሠራለን፡፡ እሑድ እናርፋለን፡፡ የበዓል ዋዜማ ሲሆን ደግሞ ሥራ ይበዛል” ብሏል፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |