| የመልካም አስተዳደግ ወይስ የመልካም አስተዳደር |
|
|
| Wednesday, 09 April 2008 | |
|
በየዕለቱ ከቦታ ወደ ቦታ፣ ከቤት ወደ ሥራ፣ ከሥራ ወደ ቤት ስንመላለስ ታክሲ ውስጥ የምንቆይበት ጊዜ ለብዙዎቻችን የታክሲ ተጠቃሚዎች ለ”ኢሰብዓዊ ጨካኝና ነውረኛ ቅጣት” የምንዳረግበት ወቅት ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ከመነሻ መድረሻችን ድረስ ታክሲው ወይም የምንጠቀምበት ሌላው የትራንስፖርት አይነት የሚወስድበት ጊዜ በዚህም የተነሳ የሚደርስብን መጉላላት አይደለም፡፡
ይህን የመሰለ ታክሲ ለማግኘት አግኝተንም ሰው አልሞላም፣ ተጨማሪ ሌላ አንድ ሁለት (ትርፍ) ሰው ያስፈልጋል ተብለን አልተጉላላንም፡፡ የዚህ ዓይነት ውርደት አልደረሰብንም፡፡ እንዲህ ያለ፣ በዚህ ስም የሚጠራ ውርደት የሚባል ነገር የለም በመባሉ ላይ ባልስማማም ይህም ቢሆን የሚናቅ ነገር አይመስለኝም፡፡ ከዚህ የበለጠ ሁልጊዜም ስለ ታክሲ ሳስብ በእጅጉ የሚያሳስበኝ ታክሲ ውስጥ ስንሆን በጥፍራችን እስክንቆም ድረስ የሚያሸማቅቀን የሚያሳፍረንና የሚያሳዝነን ከዚህ በፊት አንዳንድ ጊዜ ወይም አልፎ አልፎ ብቻ ያጋጥም የነበረው የታክሲ ውስጥ ወሬ ነው፡፡ ሞባይል ከመጣ በኋላ ግን ይህ ዱሮ አልፎ አልፎ ብቻ ያጋጥም የነበረው የአንዳንድ አማረልን ባዮች ወይም በዘመኑ ቋንቋ “ፍንዳታዎች” ጉዳይ ከሞላ ጎደል የሁሉም ወግና ፋሽን ሆኗል፡፡ ውሸትም ይሁን እውነት ገበና ውጭ ወጥቶ ሲደፋ ጉራ የሰው ሁሉ መለያና በልጦ መታየት እስኪመስል ሲደነፋ፣ የባንክ የገንዘብ ማዘዣ (የአስሮች የመቶ ሺዎች) በስልክ ሲሰጥ ፍቅረኞች የትናንት ምሽት ቆይታቸውንና አዳራቸውን በስልክ ሲገመግሙ እመቤቲቷ ታክሲ ውስጥ ሆና የወጥ ቤት ሠራተኛዋን በስልክ እያንዳንዱን ተራ ነገር ጭምር እያዘዘችና መመሪያ እየሰጠች ..ወጥ ስትሰራ.. ሌላም ሌላም ፀያፍና አስፈላጊ ያልሆነ ነገር ሲሰራ መስማት ሁሌም ያስተዳደግ ጉዳይ ነው ወይስ ከወያላው፣ ከሾፌሩ፣ ከሥነስርዓት አስከባሪ ተብዬዎች እንደምንሰማው ዓይነት የአስተዳደርም ጭምር ያሰኛል፡፡ አንዳንዴ ታክሲ ውስጥ በፍላጎታችን ሳይሆን በሾፌሩ ምርጫ ተገድደን የምንሰማቸው የአንዳንዶቹ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ዝግጅቶች አሸማቃቂና አሳፋሪ ናቸው፡፡ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በአንድ በኩል፣ በታክሲ ውስጥ ወሬና የሞባይል ንግግር በሌላ በኩል መካከል ግን መደበኛ የአሰራር ልዩነት አለ፡፡ ቤታችን የምንሰማውን ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን ስንፈልግ እንሰማዋለን ሳንፈልግ እንዘጋዋለን፡፡ አያያዙን አይተንም መልሰን ላናየው መወሰን እንችላለን፡፡ ታክሲ ውስጥ ግን ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን ታጋች ..እስረኞች.. ነን፡፡ አቁም ብለን መውረድ አንችልም፡፡ እንኳንስ የሰው ወሬና የሞባይሉን ዲስኩር የታክሲ ውስጥ ሬዲዮንን የምናዝበት አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ድምጽ እንኳ ቀንስልን የማለት መብት የለንም፡፡ አለን ብንል የሌለን መሆኑን “አሳምሮ” የሚነግሩን ወያላውና ሾፌሩ ብቻ አይደሉም፡፡ አንዳንዴም ተሳፋሪውም ጭምር ነው፡፡ ከመደበኛው ሁኔታ በተለየ በዚህ ወር ያጋጠመን ግን የሚገርምና የሚዘገንን ከዚያም በላይ ቁጭትና ፀፀት የሚያሳድር ነው፡፡ 12 ሰው በሚይዝ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ የመጨረሻውን አራት ሰው እንዲቀመጥበት “የተፈቀደውን” የጀርባ መቀመጫ ሦስት ወጣት ሴቶች ይዘውታል፡፡ ከእነርሱ ፊት ለፊት ባለው ወንበር ላይ ሌሎች ሁለት ሴቶች ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ አምስት ሴቶች ኋላ ላይ እየተረዳን ስንመጣ እንዳወቅነው አንድ ላይ ናቸው፡፡ የሥራ ባልደረቦች ናቸው፡፡ ከሾፌሩና ከወያላው በስተቀር የተቀሩት ተሳፋሪዎች እዚያ ታክሲ ውስጥ የተገናኙ እንጂ እንደ አምስቱ ሴቶች የሚተዋወቁ አይደሉም፡፡ ታክሲው ሞላ ተብሎ “ይወሰን” ዘንድ የሚቀረው አንድ ተሳፋሪ ወዲያው (ብዙም ሳይቆይ) ገብቶ የተቀመጠው ከአምስቱ ሴቶች መካከል ሦስቱ ወደያዙት የኋላ መቀመጫ ነበር፡፡ ነገሩ የጀመረው ይህን ጊዜ ነበር፡፡ የመጨረሻው ተሳፋሪ አራተኛ ሆኖ መጨረሻው የኋላ ወንበር ላይ እንደተሳፈረ ኋላ ከተቀመጡት ሴቶች መካከል አንደኛዋና ኋላም ታክሲው መጨረሻ ድረስ አብዛኞቻችንና ሁላችንም እስከምንወርድ ድረስ ዋነኛና ቀንደኛ ተራኪ ሆና የዘለቀችው ነገሩን የጀመረችው የእሷንና ከእሷ ጋር የተቀመጡትን እንዲሁም ከፊት ለፊት ያሉትን ጓደኞቿን (ባልደረቦቿን) “መቀመጫ” ስፋት በማወዳደር ነው፡፡ የአምስቱንም እያንዳንዱን ከሌላው ጋር እያወዳደረች በቃልና በአፍ “እየለካች” “እየመተረች” የደረጃ መለኪያ ትሰጠዋለች፡፡ በዚህ ርዕስ ላይ ያነጣጠረው መነሻም ሆነ ለዛ የለሽ ወሬዋ ተደራሲ ያደረገው ጓደኞቿን ሳይሆን ሌላውን ተሳፋሪ ነበር፡፡ ያም ሆኖ እንዳላማረባት ወዲያው ሳታውቅ የቀረች አትመስልም፡፡ ወዲያውኑ ስለ ሥራዋ ማውራት ጀመረች፡፡ ነርስ መሆኗን ሌሎቹ አራቱ ሴቶችም ባልደረቦቿ እንደሆኑ መረዳት የጀመርነው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰለ ሥራ ቦታዋ የውስጥ ጉዳይ ብዙ የተናገረችለትን ለጓደኞቿ በምታቀርበው ..መሪ.. ጥያቄ መሰረት ነው፡፡ አይደለም ወይም ከዚያ ብዙ ያልራቀ መልስ እያገኘች ሰው እንዲሰማት “እየጠየቀች” ትኩረቱን እየሳበች ብዙ ያወራችለትን የውስጥ ጉዳይ ብዙም አልተከታተልኩትም፡፡ ድንገት መሸማቀቅ የጀመርኩት ከሌሎች ከማንተዋወቅ ሰዎች ጋር እርስ በርስ መተያየት የጀመርነው በሥራዋ አጋጣሚ ያገኘቻቸው (ወይም እሷ አገኘሁት የምትለውን) የሰው ምስጢር፣ የታካሚዎች ገበና እንደ “የአዋጅ ቅዳጅ” ውጭ አውጥታ ስትደፋው ነው፡፡ አንዱ መርፌ ሊወጉ የመጡ ሰው ሱሪያቸውን ሲያወልቁ ተሰማኝ ያለችውን ሽታ እያነሳች ስለ “ትንፋጉ” ክርፋቱ ስትናገር ከጓደኞቿ መካከል ምላሽ የሚሰጥ ጣልቃ ገብቶ የሚናገር ቢኖር “ይገርማል እኔኮ ጫማ ሸተተኝ” የምትል መስሎኝ ነበር የሚል ብቻ ነው፡፡ ቀጠለች፡፡ “አቤት! ነርስ ያደረገኝን ጌታ!”እያለች እያማረረች ስለሌላ ወጣት መርፌ ተወጊ ተሞክሮ በዝርዝር ታወራለች፡፡ የመጀመሪያ እርግዝና “ብርቅ” ስለሆነባትና ስለባሏ ጭምር የምታውቀውንም የምትገምተውንም የመሰላትንም ሁሉ ከሌላ የ”ወሲብ” ጉዳይ ጋር እያጣቀሰች ትለፈልፋለች፡፡ ዝርዝሩ ከዚህ በላይ ብዙና ሰፊ ነው፡፡ እያንዳንዱ ጉዳይ ራሱ “ኧረ ምኑ ቅጡ!” የሚባል ነው፡፡ እንዲህ እየተሸማቀቅን ነገር ግን ለእነዚህ ሰዎች ዘግናኝ ወሬና “ኃይል” እንዲሁም “አምባገነንነት” ሰግደን ምንም ሳንልና ዝም ብለን መውረጃችን ደርሶ ወረድን፡፡ በየፊናችን ተበታተንን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ካለፈ በኋላ የቆጨኝና የፀፀተኝ፣ ምንም ባለማድረጋችን፣ ምንም ባለማለታችን ነው፡፡ ምን ማድረግ እንችል ነበር? እዚያ ውስጥ የነበረን ጊዜያዊ አንድ እና አንድ ነገር የነበርን ተሳፋሪዎች በላይ “ምን እናድርግ ማለት”ስ እንችል ነበር ወይ? ይህንንስ መባባል አለብን ወይ? ለምን እኔ ራሴ ነውር ነው አላልኩም? የሚሉ ጥያቄዎች እኔ ራሴ ያነሳሁት በኋላ ነው፡፡ ጉዳዩ አሁንም ያለቀለት ባይሆንም ማንነታቸውን ማወቅ ፋይዳ ተገኘበትም አልተገኘበትም ለሚመለከተው አሰሪ ማሳወቅ ይቻል ነበር፡፡ ምን አገባህ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ የዚህ ምክንያት ብዙውን ጉዳይ፣ የሰማሁትን ሁሉ በነቂስ ዘርዝሬ ስላላወጣሁት ነው፡፡ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን፣ በሙያ ወይም በሥራ ምክንያት የታወቀ ምስጢርን መግለጽ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀል ነው፡፡ ያስቀጣልም፡፡ አስተዳደራዊ እርምጃም ያስወስዳል፡፡ በአገራችን ሕግ የማናቸውም እምነት (ሃይማኖት) አገልጋይ የሕግ አማካሪ ጠበቃ፣ ነገረ ፈጅ፣ የሽምግልና ዳኛ፣ አስታራቂ ሽማግሌ፣ ልዩ አዋቂ (ኤክስፐርት) ነባሪ፣ አስተርጓሚ፣ ውል አዋዋይ፣ የግል ድርጅት ዳይሬክተር የሥራ መሪ፣ ተቆጣጣሪ ወይም በፍትሀብሄር ወይም በንግድ ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ምስጢር መጠበቅ የሚገባው ማናቸው ሠራተኛ፣ የጥርስ ሐኪም፣ የመድሃኒት ቀማሚ፣ ባለሙያ (ፋርማሲስት)፣ አዋላጅ ነርስ ወይም ሌላ ረዳት የሕክምና ሠራተኛ ወይም ሌላ በሙያው ወይም በሥራው ምክንያት የተገለጠለትን ምስጢር በሙያው ላይ ላለም ሆነ ሥራውን ከለቀቀ በኋላ የገለፀ እንደሆነ እንደሚቀጣ ይታወቃል፡፡ የሚቀጣው በሙያው መለማመጃ ትምህርት ምክንያት ሊያውቅ የቻለውን ምስጢር የገለፀ ተማሪ፣ በሙከራ ላይ ያለ ሰራተኛ ወይም ተለማማጅ ሠራተኛ ጭምር ነው፡፡ ሆን ብሎና አማረልን ብሎ ብቻ ሳይሆን በቸልተኝነት ምስጢር መግለጽም ያው ወንጀል መሆኑን ሕግ መደንገጉን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እነዚህ የታክሲ ውስጥ ባለ ታሪክ ሴቶች በተለይም ቀንደኛዋ ባለ ታሪክ፣ ታክሲ ውስጥ ተገድደንና “ታግተን” በቆየንበት ከ20 ደቂቃ በማያንስ ጊዜ ውስጥ አደባባይ አውጥተው የደፉት ጉዳይ ምስጢር ነው አይደለም የሚል የሕግ ጥያቄ ሊነሳ፣ የተነሳውም ጥያቄ ሊያከራክርና ሊያወዛግብ ይችል ይሆናል፡፡ ታክሲ ውስጥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለተሳፈሩት ከዚያም በኋላ በየቦታው እየተንጠባጠቡ ወርደው በእነሱ ቦታ ለተተኩት አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ያች ራሷን ነርስ ብላ የምትጠራው ወይም ነርስ ተብዬዋ ስለምታወራላቸው ሰዎች አያውቁም፡፡ ልናውቅም አንችልም፡፡ የሚወራባቸው ግን እዚያ ያሉት የነርስ ተብዬዋ ባልደረቦች አሳምረውና ለይተው ያውቃሉ፡፡ ወሬውም የደራው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ያ ሰውዬ እየተባባሉ ነው፡፡ ጥያቄው ምስጢርን የመግለጽ የወንጀል ተግባር ወይም አስተዳደራዊ እርምጃ የሚያስወስድ በሙያ ምክንያት ያገኙትን ምስጢር የመግለጽ ድርጊት ብቻ አይደለም፡፡ ሥነምግባር ግብረ ገብነትና ነውር የሚባል ነገር ቀረ እንዴ? በእኔ እምነት ይህች ደጋግሜ ነርስ ተብዬ የምላት ተሳፋሪና የሥራ ባልደረቦቿ ነውር የሚባል ነገር ለማወቅ የግድ ነርስ፣ የግድ ሴት መሆን ሳያስፈልጋት ሰው መሆኗ ብቻ በበቃት ነበር፡፡ እንደ ሰው በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ የሚያውቁት ሰው ኖረም አልኖረም “መሰተር” የጨዋ ልጅ (ባለጌ ያልሆነ) ወግ ነው፡፡ ከሌላው ሰው መብት ወይም ሰላምና መረጋጋት አኳያም የግድ አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡ ለታደሉና የማኅበራዊ ኑሮ ሽግግር ተራ ሙቀት ለሚሰማቸው ሰዎች እንኳንስ የአስር ሺዎች (የመቶ ሺዎች) ሀብትና ገንዘብ ጉዳይ በአደባባይ ማውራት ቀርቶ ጥቂት ጠቀም ካለ ወይም ከአንድ በላይ ከሆኑ ባለ 50ና 100 ብር ኖቶች ጋር አውጥቶ የታክሲ ሂሳብ መክፈል የሚከብዳቸው አሉ፡፡ ሰው ማክበር ብቻ ሳይሆን ለራስ ጥንቃቄም ጭምር ነው፡፡ የሕክምና ሙያ ከሙያዎች ሁሉ ከቀደሙት መካከል አንዱ ነው፡፡ የታወቀ የሥራ መጀመሪያ መሃላም አለው፡፡ አቤት ነርስ ያደረግኸኝ ጌታ ብሎ ፈጣሪውን “አጉል” ቦታ ስለጣለው የሚያማርር ሰው በዚያ ስም ይጠራ ዘንድ የሚገባው አይመስለኝም፡፡ ሕፃናት፣ ታዳጊ ወጣቶችና ከዚያም ከፍ ያሉ ተማሪዎች እንደሚያውቁት ትምህርት ቤት ውስጥ ከዚያም መልስ በየቤቱ ስለትምህርት ቤት፣ ስለመማሪያ ክፍል፣ ስለ ክፍል ኃላፊው (ሞኒተሩ)፣ ስለ አስተማሪው ወዘተ. ማውራት “ማማት” የየዕለቱን ውሎና ሁኔታ እያነሱ ለቤተሰብ መተረክ “የተለመደ” ነው፡፡ የአሳዳጊ ሚና የሚመጣው በጨዋታ ውስጥ በቁም ነገር መካከልም ቢሆን ነውሩና ነውር ያልሆነው የሚለየው ያን ጊዜ ነው፡፡ የፆታ ልዩነት ሳይደረግ ሴትም ሆነች ወንድ ነርስ ታካሚው ወይም በነሱ ቋንቋ በሽተኛው ወንድ ወይም ሴት መሆኑ ልዩነት ሳያመጣ ልብስ የሚያወልቅላቸው “ሀፍረቱን” ገልጦ የሚያሳያቸው ነርሶች ይህንን የሕክምና ሙያና አገልግሎት አስፈላጊ ያደረገውን እውቀታቸውን የአደባባይ የታክሲ ወሬ ሲያደርጉት መስማትን የመሰለ አስደንጋጭና አሳፋሪ ጉዳይ የለም፡፡ ልጆቹ የደረሱበት ዝቅጠት አሳፋሪ ነው፡፡ ሙያው (ሙያው ላይ የተቀባ፣ ጤናማ ገላ ላይ የታየ የሚፀዳ ጥላሸት ነው ካልተባለ በስተቀር) የደረሰበት የ”እድገት” ደረጃም እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ አሳዳጊ የበደላቸው ናቸው ወይስ አስተዳዳሪ ወይስ እነሱንም ለዚህ ያበቋቸው እኛንም ለዚህ የዳረጉን ሁለቱም ተጋግዘው ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ይህንን አስደንጋጭና አሳፋሪ ጉዳይ ታክሲ ውስጥ በሰማሁበት በመጋቢት ወር ውስጥ የተደመጠውና አውሮፓ ሰማይ ላይ ተፈፃሚ የሚሆን አንድ አዲስ ዜና አለ፡፡ ይህም ሞባይል ቴሌፎን አውሮፕላን ላይ ሊሰራና ሊፈቀድ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ እኛና እነዚያ ነርሶች ከተፈጠርንበት ምድር ከፍ ስንል እንዳለንና እንደተፈጠርን ሆነን እስከ ዛሬ ድረስ አይሰራም ነበር እንዴ? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ ባለጉዳዮችንና መብቱ ያላቸው ሰዎችን ግን ያሳሰባቸው የዚህ ጥያቄ መልስ አይደለም፡፡ የሰማይ ላይ የሞባይል አጠቃቀም ኮድ(ደንብ) ካልወጣ በስተቀር ሞባይል ቴሌፎን አውሮፕላን ውስጥ ሊፈቀድ አይገባውም እያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን “ነርሶች” አውሮፕላን ውስጥ አስቧቸው፡፡ ሞባይላቸው የሚያሰማውን ድምጽ (ሪንግ ቶን)፣ የንግግራቸውን ይዘት (አዲስ አበባ ታክሲ ውስጥ) የምትሰሙትን ዓይነት ይገምቱ፡፡ የሰማ ሰውስ ምን ይላል? አሳዳጊ ወይስ አስተዳደር የበደለው? እኛም ሰምተን ዝም ብለናል፡፡ ለምን? አንድም መጀመሪያ እንኳንስ ምስጢርና የሰው ገበና አደባባይ ወጥቶ ሲደፋ ተራና ሌላ የባጡን የቆጡን የሚያወሩበት ጉዳይም ቢሆን ያለመረበሽ መብት እንዳለን መብታችን መሆኑን አናውቅም፡፡ እናውቃለን ብለን ትንሽ መከር ቢያደርገን ምን አገባህ የሚል ይመጣል ብለን እንፈራለን፡፡ መብታችንን ማስረዳት መከላከል ይገደናል፣ ያስቸግረናል፡፡ ከጣራ በላይ እየጮህን ሰው የምንረብሽበት ሞባይላችን፣ የተለየ ትኩረት የሚስብ “ሪንግ ቶን” የምናደርግበት ሞባይላችን፣ የሌላውን ተናጋሪ ድምጽ ጭምር እንዲያሰማ አድርገን የምንከፍተው ሞባይላችን ወዘተ. የእነዚያን “ነርሶች” ምስል ማንሳት ንግግራቸውን መቅዳት ይቻል ነበር፡፡ አላደረግነውም፡፡ ማስረጃ መሰብሰቢያና ማጠናከሪያ አልሆነንም፡፡ ከነገሩ ጦም እደሩ ብለን “ነርሶችን” ፈርተን ሌላው አይተባበረንም ወይም ይተናኮለናል ብለን አለፍን፡፡ ያልፈጠራቸው፣ አስፈንጥሮ ያልጣላቸው “መልካም አስተዳደር” አይታደገንም፣ አለዚያም ምን አገባችሁ ይሉናል ወይም መልሰው ያጉላሉናል ብለን አላደረግነውም፡፡ የእኛው የራሳችን የአስተዳደጋችንና የአስተዳደራችን ውጤት ነውና፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |