Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የወጣት ተማሪዎች የልምድ ልውውጥ
የወጣት ተማሪዎች የልምድ ልውውጥ Print E-mail
Wednesday, 09 April 2008
Image
ኤልቤት አልታዬ
መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው አለም አቀፍ ትምህርት ኔትዎርክ (Education and resource network) አካል በሆነው የወጣት ተማሪዎች ልውውጥ ፕሮግራም (youth exchange study) በዚህ ዓመት ማብቂያ ላይ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ተማሪዎችን በማስመልከት አርብ መጋቢት 26 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ግቢ ውስጥ በተደረገው ፕሮግራም ላይ ተገኝተን ነበር፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑ ወጣት ተማሪዎች ለልምድ ልውውጥ ወደ አሜሪካ ለመሄድ የተመረጡ ስምንት ታዳጊዎች ከነወላጆቻቸው፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ ተወካዮች እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶን ጨምሮ የፕሮግራሙ ኮርዲኔተርና የአሜሪካ ኤምባሲ የባህል ልውውጥ ፕሮግራም ተወካይ ተገኝተዋል፡፡

የወጣት ተማሪዎች የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም የተጀመረው በ2002 ላይ ሲሆን ወጪው በግማሽ የሚሸፈነው በአሜሪካ መንግሥት ነው፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን በዚህ ዓመት ሦስት ተማሪዎች ወደ አሜሪካ ሄደዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ ማሊና ሴኔጋል ከአፍሪካ፣ ፓኪስታንና ባንግላዴሽ ደግሞ ከእስያ በፕሮግራሙ የታቀፉ አገሮች ናቸው፡፡

የወጣት ተማሪዎች ልውውጥ ፕሮግራም፣ ተማሪዎችን አወዳድሮ በመምረጥ ሂደት ውስጥ ትምህርት ቤቶችን ከመምረጥ ጀምሮ አሸናፊ ተማሪዎችን ወደ አሜሪካ እስከ መላክ ባለው ሂደት ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ እንደሚሰራ የወጣት ተማሪዎች ልውውጥ ፕሮግራም ኮኦርዲኔተር አቶ ግርማ ምትኩ ገልፀዋል፡፡

አቶ ግርማ እንዳሉት፣ ባለፈው ዓመት በዚህ ፕሮግራም ከኢትዮጵያ የሄዱት ወጣት ተማሪዎች በኮሎራዶ፣ ቴክሳስና ቨርጂኒያ ስቴት ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎቹ ተመርጠው የሄዱት አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ሲሆን በዚህ ዓመት በፕሮግራሙ ወደ አሜሪካ የሚሄዱት ተማሪዎችን ለመምረጥ የአባድር፣ አወሊያ፣ ቦሌ፣ ኮከበ ጽባህ፣ ባልቻ አባነፍሶና ጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እንደተጠቆሙ ገልጸውልናል፡፡


በወጣቶች ልውውጥ ፕሮግራም ወደ አሜሪካ የሚሄዱት ወጣት ተማሪዎች በአሜሪካ የሚቆዩት ለአንድ ዓመት ሲሆን በቆይታቸው ትምህርታቸውን በሚቀጥሉበት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአገራቸውን ባህልና እሴት የሚያስተዋውቁበት ሁኔታ እንደሚመቻችላቸው ከአቶ ግርማ ንግግር ለመረዳት ችለናል፡፡ በዚህ ዓመት ወደ አሜሪካ ለመሄድ የተመረጡት ስምንት ተማሪዎች እድሜያቸው አስራ አምስትና ከዚያ በላይ ሲሆን ሁለቱ ግን አሥራ አምስት ዓመት ሊሞላቸው ጥቂት ወራት ስለሚቀራቸው በሚቀጥለው ዓመት እንዲሄዱ መወሰኑን ነግረውናል፡፡

ሐምሌ መጨረሻ ላይ ወደ አሜሪካ የሚጓዙት ወጣቶች ሦስት ሴትና ሦስት ወንድ ተማሪዎች ናቸው፡፡ "በፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማካተት ተሞክሯል፡፡ በቀጣይ ደግሞ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች ተቻችለው የሚኖሩባቸውን ከተሞች ለማቀፍ እቅድ ተይዟል፡፡ በእቅዱ መሠረትም ድሬዳዋ፣ ሐረር ወሎና ባህርዳር እንደሚካተቱ ይጠበቃል" ብለዋል አቶ ግርማ፡፡

የወጣት ተማሪዎች የልውውጥ ፕሮግራም ቢሆንም እስከ አሁን ባለው ሂደት ወጣት ኢትዮጵያዊ ተማሪዎች ወደ አሜሪካ ቢሄዱም የአሜሪካ ወጣት ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ሁኔታ አለመኖሩን አቶ ግርማ አልደበቁም፡፡ ፕሮግራሙን በተግባር የወጣቶች የልውውጥ ፕሮግራም ለማድረግ ወጣት አሜሪካዊ ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ሁኔታ ላይ እያሰቡበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ እስከዚያው ግን ኢትዮጵያዊ ወጣት ተማሪዎቹ በአሜሪካ የኢትዮጵያን ባህልና እሴት ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የአሜሪካን ባህልና እሴት የማስተዋወቅ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡

ኤልቤት አልታዬ የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ በወጣት ተማሪዎች የልውውጥ ፕሮግራም ወደ አሜሪካ ለመሄድ እንዴት ልትወዳደሪ ቻልሽ? ስንል ጠየቅናት፡፡ "በውድድሩ ለመሳተፍ በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሰማንያ ነጥብ በላይ ማምጣት ይጠይቅ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ 97.7 ነበር ያመጣሁት፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው የጽሁፍና የቃል ፈተና ከባድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ተሳታፊ የነበሩት ተማሪዎች በጣም ተፎካካሪዎች ስለ ነበሩ" በማለት መልሳልናለች፡፡

ለጽሑፍ ፈተና የቀረቡት ተማሪዎች ሠላሳ ስምንት ሲሆኑ በውጤቱ አስራ ስድስት ቀርተዋል፡፡ ከቃል ፈተና በኋላ ደግሞ አሁን ወደ አሜሪካ ለመሄድ የተመረጡት ስምንት ታዳጊዎች ብቻ ሊመረጡ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ሄደው ትምህርታቸውን በሚቀጥሉበት ትምህርት ቤት ከሚኖረው የትምህርት አሰጣጥ ጋር በቀላሉ መላመድ እንዲችሉና የሚኖሩበትን ስቴት አኗኗር ሳይቸገሩ እንዲለምዱ ቋንቋን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን ያካተተ ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነ ኤልቤት ገልፃልናለች፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸውን ለማዳበር በአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ የቋንቋ ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸውን የምትናገረው ኤልቤት የኢትዮጵያን ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ እንዲችሉ ታሪካዊና ባህላዊ ቦታዎችንና በእነዚህ ዙሪያ የተሰሩ ጥናታዊ ፊልሞችን መመልከትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥልጠና መውሰድ ከመሄዳቸው በፊት የሚደረጉ ዝግጅቶች መሆናቸውን አመልክታለች፡፡

የመመዘኛ ፈተናዎቹ በተለይም የጽሁፍ ፈተናው የእንግሊዝኛ ሰዋሰው ብቃትን ይመዘናል፡፡ የቃል ፈተናው ባህልንና ባህላዊ እሴቶችን በማወቅና በምን መልኩ ለሌሎች ማስተዋወቅ ይቻላል በሚል ዙሪያ የሚያጠነጥን ነበር፡፡   

የዚህ ዓመት ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚሄዱ ሲሆን ከአሜሪካ ሲመለሱ ያለምንም መስተጓጎል ትምህርታቸውን መቀጠል የሚችሉበት ሁኔታ ላይ የአሜሪካ ኤምባሲና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በምሕረት አስቻለው
 
< Prev   Next >