Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ...
የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ... Print E-mail
Sunday, 13 April 2008
የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ተቃዋሚዎች አልተቀበሉትም

የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ሐሙስ እለት በተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው መደበኛ ስብሰባ ፀደቀ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ሕጉ ቁጥጥር ይበዛበታል በማለት እንደማይደግፉት ገልፀዋል፡፡

በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲን እንቅስቃሴ በመከታተል መረጃ እንዲይዝ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲን የገቢ ምንጭ የወጪ ዝርዝር እና ንብረት ይከታተላል፡፡ ይቆጣጠራል፡፡ ሕገ ወጥ ድርጊት ተፈጽሞ ሲያገኝም አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል፡፡ በየዓመቱ ወይም ቦርዱ በሚወስነው ጊዜ ፖለቲካ ፓርቲ በኦዲተር የተረጋገጠ የሀብት እዳና ሰነድ በፓርቲው መሪ ፊርማ የጽሁፍ ሪፖርት ለቦርዱ ይቀርባል፡፡

 በአዋጁ ላይ እንደተገለፀው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ መሪ ለቦርዱ በጽሁፍ ያሳወቀው ሃብትና እዳ ሀሰት ሆኖ ከተገኘ አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ ይጠይቃል፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በአዋጁ የተደነገጉ መረጃዎችን በቦርድ ሲጠየቅ በሰነድ የተረጋገጠ የጽሁፍ መረጃ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ ለቦርዱ እንዲያቀርብ የተደነገገውን አመታዊ የሥራ፣ የሂሳብ፣ ወይም ሌሎች ወቅታዊ ሪፖርቶች ሳያቀርብ የቀረ እንደሆነ፣ ለሁለት ተከታታይ አመታት የጠቅላላ ወይም የአካባቢ ምርጫ ውድድርን ሳይሳተፍ የቀረ እንደሆነ ምርጫ ቦርድ ከምዝገባ ሊሰርዘው እንደሚችል በአዋጁ ተቀምጧል፡፡

ስለፖለቲካ ፓርቲዎች የገቢ ምንጭ እና የንብረት ሁኔታ በተመለከተ ማሻሻያ አዋጆች ወጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት መንግሥት በፌደራልና በክልል ም/ቤቶች ውክልና ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ለፌደራል ወይም ለክልል ም/ቤቶች የምርጫ ተግባር የሚውል ድጋፍም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ይሰጣል፡፡

ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ከመንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ ከተመለከተው አላማ ውጭ ካዋለ ወይም በወቅቱ ሪፖርት ካላቀረበ ወይም የሀሰት የሂሳብ ሰነድ ያቀረበ እንደሆነ፣ ወይም ከሚሰጠው ድጋፍ ጋር በተያያዘ ግዴታውን ያልተወጣ እንደሆነ የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቋረጥ፣ ፓርቲው በወንጀል ሕግ መሰረት በገንዘብ እንዲቀጣ፣ እንዲታገድ ወይም እንዲፈርስ የፓርቲው ኃላፊ ወይም ኃላፊዎች በገንዘብ ወይም በእስር እንዲቀጡ ሊደረግ ይችላል፡፡

ተሻሽሎ የወጣውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውመውታል፡፡ አቶ ተመስገን ዘውዴ አዋጁን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት በምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ አንዳንድ የህዝብ ፓርቲዎች እውቅና እንዳያገኙ የሚያደርግና የአንድ ገዥ አምባገነናዊ ስርዓት እንዲጠናከርና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጠፋ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ በተመለከተ ፖርቲያቸው ከገዥው ፓርቲ ጋር ድርድር ማካሄዱን የጠቆሙት የኢዴአፓ መድህን ተወካይ አቶ መስፍን መንግሥቱ በድርድሩ ሂደት በብዙዎች ጉዳይ ላይ ስምምነት ያልደረሱበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ አቶ መስፍን እንዳሉት በተሻሻለው አዋጅ ላይ የቀረቡት አንዳንድ አንቀጾች በአንድ በርሜል ውሃ ላይ አንድ ብልቃጥ መርዝ ጨምሮ ውሃውን ከመበከል ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡

የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ተሻሽሎ እሰከቀረበበት ጊዜ ድረስ የመጀመሪያውን አዋጅ ለመተግበር እንቅስቃሴ የተደረገበት ሁኔታ አለመኖሩን የጠቆሙት አቶ መስፍን አፈፃፀምን በሚመለከት በአዋጁ ላይ ዝርዝር ሁኔታ ቢቀመጥ የተሻለ ይሆን እንደነበር  አመልክተዋል፡፡

በተሻሻለው አዋጅ ላይ መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለባቸውን የገንዘብ ችግር ያስወግዳል ብለው አቶ መስፍን ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ በፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ዘልቆ ጣልቃ መግባቱ አልተዋጠላቸውም፡፡ ለፓርቲዎች ገንዘብ የሰጠ ሰው በሙሉ ስሙ እንዲጠቀስ የሚፈለግበት ምክንያትም ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ኢዴአፓ መድህን ተወካይ እምነት የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ልዩነት በማይታወቅበት አገር ውስጥ እንደዚህ አይነት አዋጅ መውጣቱ በስልጣን ላይ ያለው ገዥው ፓርቲ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ መረጃ ላይ አላስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን የሚሰበስብበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
የኦፌዴኑ ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው አዋጁ ጨቋኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ ቁጥጥር እንደሚበዛ የጠቆሙት አቶ ቡልቻ አዋጁ ከምዕራቡ አገሮች የተወሰደ ነው የሚለው አገላለጽም የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሌሎች አገሮች ተወሰደ የተባለውም ሕግ የከፋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“በደርግ ጊዜ ‘ቁጥጥር’ የሚል ቃል ስለበዛ ብዙ ሰዎች ‘ቁጥጥር’ የሚል ቃል ከአማርኛ መዝገበ ቃላት ይውጣ ይሉ ነበር” ያሉት የኦፌዴኑ ሊቀመንበር በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ የታየው ሁኔታም ከደርግ ቁጥጥር ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አዋጁን በማስመልከት ኢህአዴግን ወክለው አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ሽፈራው ጃርሶ በአዋጁ ላይ የተጠቀሱት ቁጥጥሮች ህግን ከማስከበርና ዴሞክራሲን ከመገንባት አንፃር ታይተው የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

አንድ ህግ ሲረቀቅ ለገዥው ፓርቲ በሚጠቅም መልኩ ሳይሆን ለሁሉም ፓርቲዎች በሚሰራ መልኩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽፈራው ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚያካሂደው ቁጥጥርም ቢሆን ፓርቲዎችን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ፓርቲዎች ከውጭ አገር ባመጡት ገንዘብ ምክንያት እርስ በርሳቸው የተጋጩበትና ፓርቲያቸውም ህልውና እንዳይኖረው ያደረጉበት ሁኔታ መኖሩን እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የኢህአዴጉ ተወካይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፋይናንሳቸውን ለምርጫ ቦርድ ማስመዝገብ እንዲያብቡ የሚረዳቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “ሕጉ ጨቋኝ ነው” የሚለው አባባልም ትክክለኛ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኃይሌ ሙሉ
 
< Prev   Next >