Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ለንግድ ባንክ ሰራተኞች...
ለንግድ ባንክ ሰራተኞች... Print E-mail
Sunday, 13 April 2008
ለንግድ ባንክ ሰራተኞች የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ቅሬታ አስነሳ

የኑሮ ውድነቱን አስመልክቶ ለንግድ ባንክ ሰራተኞች የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ውዝግብ አስነሳ፡፡ ቁጥራቸው አምስት መቶ የሚሆኑ የባንኩ ሰራተኞች በጭማሪው አለመካተታቸውን በመግለፅ ቅሬታ ማቅረባቸው ተሠማ፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማኔጅመንትና የሥራ አመራር ቦርድ፣ ለመንግሥት ፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲ አቅርበው ባስወሰኑት መሠረት የኑሮ ውድነቱን አስመልክቶ ካለፈው ኅዳር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ የደመወዝ ማሻሻያ ጭማሪ አምስት መቶ ገደማ ሰራተኞችን አለማካተቱ ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የደመወዝ ጭማሪው ወጥነት በሌለው ስኬል መካሄዱን በመጥቀስ ሰራተኞች ኢፍትሀዊ ጭማሪ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ሰራተኞቹ በጭማሪው አለመካተታቸውን ነገር ግን ባንኩ ለሠራተኞቹ በሙሉ ጭማሪ እንዳደረገ የሚገልፅ መግለጫ መስጠቱ ከእውነት የራቀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በሰራተኞቹ ገለፃ መሠረት ጭማሪው የባንኩ የበላይ አመራር አካላትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የተለያየ የጭማሪ ስኬል ቀመር ተደርጓል በማለት የባንኩን አመራር ወቅሰዋል፡፡

መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የደመወዝ ጭማሪ በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት፣ ዲስትሪክት ፅህፈት ቤቶችና ቅርንጫፎች የሚገኙ ሠራተኞችን የሚያጠቃልል ጭማሪ ቢያደረግም፤ የባንኩ አመራር የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችንና መስፈርቶችን በማውጣት ጭማሪው ፍትሀዊ እንዳይሆን ማድረጉን ሠራተኞቹ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ምንም ዓይነት ጭማሪ ያልተደረገላቸው የባንኩ ሠራተኞች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሠራተኞቹ የደመወዝ ጭማሪ ቅሬታቸውን በተመለከተ የሰራተኛ የቅሬታ መግለጫ ፊርማ ማሰባሰብ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

የባንኩ የማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ቸርነት በደመወዝ ጭማሪ ያልተካተተ ሰራተኛ አለመኖሩን ገልፀዋል፡፡ ጭማሪው መንግሥት በሰጠው መመሪያ መሠረት መከናወኑን ገልፀዋል፡፡ በዚህም መመሪያ መሰረት የባንኩ ሰራተኞች ከአንድ እርከንና ከዚያ በላይ ጭማሪ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

አቶ አየለ ጤንነት ችግር ያለባቸው የባንኩ ሠራተኞችን ጨምሮ ጭማሪ መደረጉንና በጭማሪው ያልተካተቱ ሰራተኞች አለመኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡ በጭማሪው ያልተካተቱ የባንኩ ሠራተኞች ስለመኖራቸው የቀረበው ቅሬታ በተመለከተ “ከእውነት የራቀ ውንጀላ” ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የባንኩ የሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ምንተስኖት ጥበበ፤ የባንኩ ሠራተኞችን አቤቱታ ያውቁታል ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

በተሾመ ንቁ
 
< Prev   Next >