| “ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው በኢትዮጵያ ሕግ... |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
“ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው በኢትዮጵያ ሕግ ለመሥራት ተስማምተን ነው” ሲኖ ሀይድሮ “ህግ መከበር አለበት” ገቢዎች ሚኒስቴር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በኢትዮጵያ ሕግ ለመሥራት በመሆኑ ኤምባሲያቸው ሕገወጥ እንዲሆኑ ፈቃድ እንደማይሰጣቸው የሲኖ ሀይድሮ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ምክትል ዳይሬክተር ሚ/ር ፔንግ ጋንግ አስታወቁ፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ህግ መከበር አለበት ብሏል፡፡
የሲኖ ሀይድሮ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ይህንን የተናገሩት ሲኖ ሀይድሮ ለኩሉ ናይል መንገድ ድልድይ ሥራ በሚል ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ ከተፈቀደለት ውጪ አስራ አንድ ኮንቴነር እቃ በናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ እንደተያዘ ተጠቅሶ በሪፖርተር ጋዜጣ መጋቢት 21 ቀን 2000 ዓ.ም የተፃፈውን ዜና ሲያስተባበብሉ ነው፡፡ ሲኖ ሀይድሮ መልካም ስም ያለው ኩባንያ መሆኑን የገለፁት ሚ/ር ፔንግ “በኮንቴነር የገቡት እቃዎች ሰነድ ሲዘጋጅላቸው ስህተት መሰራቱን እናምናለን” ብለዋል፡፡ ስህተቱ የተሰራው ግን ሆን ተብሎ እንዳልሆነ ለደንበኛቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና ለጉምሩክ ባለሥልጣን መግለፃቸውን አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚሰሩት ፕሮጀክት ብዛት በየጊዜው እየጨመረ ቢሄድም የሰው ኃይል ባለመጨመራቸው ምክንያት ችግሩ መከሰቱን ሚ/ር ፔንግ ተናግረዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሥራውን ሲሰሩት የነበሩት ሠራተኞች ለሥራው በቂ እውቀት የሌላቸው መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ የሰው ኃይል መጨመራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሚ/ር ፔንግ አጽንኦት ሰጥተው የገለፁት ከዜናው በስተጀርባ አለ ባሉት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ “የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት” ከዜናው በስተጀርባ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ “የሁለቱን አገራት ግንኙነት በጥርጣሬ የሚመለከቱ አካላት ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ እንደወሰዱት ተሰምቶናል” ያሉት ሚ/ር ፔንግ “የኢትዮጵያን እድገት የሚወድ ማንኛውም ዜጋ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የልማት እንቅስቃሴ እንዲደናቀፍ ሊፈቅዱ አይገባም” ብለዋል፡፡ “እቃዎቹ ሲገቡ ህግ ተላልፈን ከሆነ ቅጡን፡፡ በእኛ ጥፋት ግን የአገራችሁ ንብረት የሆነው ፕሮጀክት በስቲል ፎርም ብረቶች መያዝ አይስተጓጎል ነው እያልን ያለነው” የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ “ሚዲያዎችም ቢሆን የነገሮችን አዎንታዊ ጎን እንጂ አሉታዊ ጎን ሊይዙ አይገባም፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም ለአሉታዊ ጎናችን ትኩረት አይስጥ” ሲሉ በጋዜጣው ዘገባ ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልፀዋል፡፡ የቻይና ኤምባሲ ጣልቃ በመግባት ለጉምሩክ ጽፏል ስለተባለው ደብዳቤ “የቻይና ኤምባሲ ሥራው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል፣ ጎን ለጎን ህጋዊ ማጣራቱ እንዲቀጥል ከመጠየቁ ውጪ አንዳንድ አካላት እንደሚሉት ለጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጥ አልጠየቀም” ሲሉ ሚ/ር ፔንግ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም “ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው በኢትዮጵያ ህግ ልንገዛ ተስማምተን በመሆኑ ኤምባሲያችን ህገወጥ እንድንሆን በፍፁም አይፈቅድም” ብለዋል፡፡ ከስቲል ፎርሞቹ ጋር የምግብ ሸቀጦች ለምን ተገኙ ለተባለው ..ምናልባት ተቀላቅሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የምግብ ሸቀጣሸቀጦችን የማስገባት ፈቃድ አለን.. በማለት መልሰዋል፡፡ ከተፈቀደው መጠን በላይ ኮንቴነሮች ስለማስገባታቸው ተጠይቀው በሠራተኞች ብቃት ምክንያት ችግር መፈጠሩን ሚ/ር ፔንግ ገልፀው እቃዎቹ ባለመለቀቃቸው ሥራው መቋረጡን አመልክተዋል፡፡ በገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ ጉዳዮች ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተዘራ ወዳጆ “ሕግን የመተላለፍ ጥያቄ በአስተዳደራዊ ጉዳይ አይፈታም” ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ህግ መከበር አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ከቀረጥ ነፃ የማስገባት መብት እንዳለው ያመለከቱት አቶ ተዘራ የተያዘው እቃ ለፕሮጀክት የመጣ ቢሆንም ወደ አገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት አስፈላጊውን ሁሉ ሊያሟላ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተያዘውን ጥያቄ አስመልክቶ ጥያቄ ማቅረቡን እንደሚያውቁ የገለፁት አቶ ተዘራ ..የተያዘው እቃ የፖሊስን መረጃ በማፋለስ መልኩ እቃው ተለቆ ልማት ላይ ቢውል ቢደረግ ችግር አያመጣም.. በማለት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ሰራተኛ “እቃው እንዴት ያለ መረጃ ከጅቡቲ ናዝሬት ደረሰ? የሚለው ዋናና መጣራት ያለበት ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ጉምሩክ የፖሊስና የአቃቤ ሕግ ሥራ ስለሚሰራ በተጠቀሰው ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊመረምር ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራና ሰለሞን ጎሹ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |