| በብሔር ፖለቲካ የሚታመሱት ዩኒቨርሲቲዎቻችን |
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
ባለፉት ጥቂት ቀናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቡድን በመደባደባቸው የተነሳ ከባድ ሁከትና ግርግር እንደተፈጠረ ሲዘገብ ከርሟል፡፡ አገሪቱ በአካባቢዋ ያሉት አገራት ሰላሟን ለማደፍረስ ደፋ ቀና በሚሉበት፣ የውስጥ ዴሞክራሲያዊ የፉክክር መንፈስ በዋለበት እና አብዛኛው የአገሪቱ ነዋሪ በድህነት አዘቅት ውስጥ በሚራወጥበት በዚህ ጊዜ የአሁኑ ትውልድ በቡድን ለመደባደብ መቻሉ የአገሪቱን የመጭ ጊዜ ተስፋ በጥርጣሬ እንድናየው የሚያደርግ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቡድን (ለዚያውም ብሔርን መሰረት ያደረገ) ጥል ለምን ይሳተፋሉ? ይህ ጥያቄ ባለፉት ሦስትና አራት አመታት ተደጋግሞ ቢነሳም ጥናትና ምርምርም እንደተደረገበት ቢገለጽም ዛሬም ተማሪው ብሔርን መሰረት አድርጎ እየተጣላ ነው፡፡ ለምን? አሁንም የምንጠይቀውና በአስቸኳይ መመለስ ያለብን ጥያቄ ነው፡፡ ለጥያቄው ሦስቱ ትልልቅ ብሔሮች (ኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ) በየፊናቸው ለመመለስ ቢሞክሩም ሁሉን የሚያስማማ መልስ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ እንደሚሉት የተማሪዎች ግጭት የተነሳው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በነበሩት ምሁራን ነው፡፡ የዛኔዎቹ ምሁራን ያዳበሩት የለውጥ ሕልም ሦስት ዋና ዋና ገጽታዎች ነበሩ፡፡ እነርሱም ሥርዓታዊ አስተዳደር መዘርጋት፣ አርሶ አደሩን የምርቱ ባለቤት በማድረግ የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ሕይወት መቀየርና ፍትህና እኩልነትን ለማስፈን የሃይማኖትና የብሔረሰብ ጭቆና ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ የቅድመ ኢጣሊያ ወረራ ምሁር ዋና ዓላማ የሃይማኖት እኩልነትን ማስፈን፣ መንግስትን ከሃይማኖት መነጠል ሲሆን ለብሄረሰብ እኩልነት መታገል ቀርቶ ብዙዎቹ የብሔረሰብ ጭቆና መኖሩንም በውል መገንዘባቸው አጠራጣሪ ነበር፡፡ ባንፃሩ የድኅረ ወረራ ምሁራን በተለይም የተማሪው ንቅናቄ አቢይ አላማ የብሔረሰብ ጭቆናን አስወግዶ አሁን ተደጋግሞ እንደምንሰማው ..በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን መገንባት ነበር፡፡.. በ1987 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በፌደራል ስርዓት አማካይነት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ጭቆና ማብቃት በመግቢያው ላይ አስፍሯል፡፡ ይሁንና በአንቀጽ 39 የተሰጠውን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል በሚለው ላይ መግባባት ላይ ያልተደረሰ በመሆኑ፣ በቋንቋ አጠቃቀም ላይ ያለው አለመግባባትና በትክክለኛው የፌደራሊዝም ስርዓት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ልክ እንደ ፓርቲዎቻችን ሁሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንም አያግባባም፡፡ የኦሮሞ ተማሪዎች ሁሉም አንድ አይነት አመለካከት ባይኖራቸውም በመገንጠል ሀሳብና ዛሬም ቢሆን ትክክለኛ የነፃነትና የመብት ተጠቃሚዎች አይደለንም ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ ለዚህም በህዝብ ቁጥር ብዛትና በክልሉ ስፋት የተነሳ በማዕከላዊ መንግስት ያላቸውን ውክልና በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚመለከቱ ሲሆን የራስ ገዝ አስተዳደሩም በጫና ውስጥ እንዳለ የሚያስቡ ናቸው፡፡ የአማራ ተማሪዎች ደግሞ ዛሬም ቢሆን ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመፍጠር ሲሞክሩ የሚስተዋሉ የመኖራቸውን ያህል ትምክህተኛና የነባሩን ስርዓት ናፋቂዎችም እንዳሉ ይታመናል፡፡ በዚህም ኦሮሞውን ተገንጣይ በማለት አማራውን ደግሞ የአያትና የቅድመ አያቱን የጭቆና አገዛዝ መልሶ ለማምጣት የሚጥር በማለት ሽኩቻ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ትግራዋይ ደግሞ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለይቶ አለማየት ሲሆን የመንግስትን ስልጣን ለማስጠበቅ ሁሌም የሚጥር አካል አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ በመሆኑም በመንግስት ላይ ቅራኔ ያላቸውን በዚህ ብሄር ተወላጅ ላይ ይተነፍሱታል፡፡ እንግዲህ በሺህ የሚቆጠረውና ከተለያየ የአስተዳደግ ሁኔታ የመጣውን፣ የተለያየ ትምህርት የቀሰመውንና የተለያየ አመለካከት ያለውን በርካታ ቁጥር ያለውን ተማሪ በሦስት ቁጥር ኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ በማለት እየቧደኑ ከላይ ከተነሱት በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያትነት በየጊዜው ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ በራሳቸው ወይም ከጀርባቸው ባሉ ሃይሎች (ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህ ገዥውን ፓርቲም ይጨምራል) የሚደግፉ ተማሪዎች ለዚህ ግጭት ተጠያቂ ቢሆኑም በንፁህ ልቦና ለትምህርት ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የገቡት አብዛኛዎቹ ግን ያለስራቸው ስማቸውን እያጡ ነው፡፡ እርግጥም ወጣቶቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በግቢያቸው ላይ ተሰቅሎ የሚገኘውን ዩኒቲ ኢን ዳይቨርሲቲ የሚል አገላለጽ በጥልቀት መገንዘብ ይገባል፡፡ በፌደራሊዝም ጽንሰ ሃሳብም ሆነ በስነ አመንክዩ አንድነት ሲታሰብ ልዩነትን እያሳዩ ከሆነ ትልቅ ችግር ይከሰታል፡፡ ኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ ብዙ ጊዜ በግጭቱ ስለሚሳተፉ አነሳን እንጂ ለሁሉም ቢሆን በኢትዮጵያ አንድነት ስር ልዩነቶቻችንን በአንድ ጽንፍ ይዞ ሰላምና ነፃነትን ዴሞክራሲና ብልጽግናን በጋራ በአንድነት መዘመር አለብን፡፡ ሕዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ተብሎ በተከበረ በዓል ላይ የተከፈተ ሙዚቃ እየተመረጠ ሲጨፈርበት አይቼ ገርሞኝ ነበር፡፡ ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ነው፡፡ ሲዘመር ሲጨፈር ደስታም ሲገለጽ ዘፈን ለምን ይመረጣል? የምታቅፉትና የምትዘሉት ሰው መምረጡስ ምን አስፈለገ? አንድነትስ የት ነው የሚታየው? ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ ኅብረት፣ ኦፊዴን፣ ኢህአዴግ፣ ቅንጅት፣ ኦነግ. . . ሁሉም የብሔር ፖለቲካ ዋነኛ መሳሪያቸው ነው፡፡ የሰከነ ውይይት እንኳን ለማድረግ የቻሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ተወደደም ተጠላም ከ70 ሚሊዮን በላይ የሆነ ሕዝብ በሚኖርበት አገር ሁሉም የራሳቸው ደጋፊዎች አላቸው፡፡ የሚደግፉት የሚነቅፉት ሀሳብም አላቸው፡፡ ነገር ግን ነገሮች ላይ ያለን መግባባት ቀርቶ አለመግባባት ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ ሲማሩ ሲመራመሩና የአገሪቱን ችግር ተረድተው መፍትሄ ለማፈላለግ ከየክልሉ ተሰብስበው አብረው እንዲያጠኑትና እንዲወያዩ መልካም አጋጣሚ የተፈጠረላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መደበኛውን ስነ አምንክዮና ሳይንስ ሳይሆን ኢ-መደበኛው የፖለቲካ ውዥንብር የፈጠረውን ስሜታዊነት በመከተል እየተጫረሱ ነው፡፡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተቧድነው እንዲደባደቡባቸው ሳይሆን እንዲያቁባቸው፣ እውነትን እንዲፈልጉበትና የሚያኮሩና የሚያበለጽጉ መግባባትን እንዲፈጥሩባቸው ነው የተቋቋሙት፡፡ ታዲያ ምነው የብሔር ፖለቲካን ማስፋፊያ፣ ሰው በምግባሩ ሳይሆን በዘሩ የሚወደድባቸውና የሚጠሉባቸው መድረኮች ሆኑ? ችግሮቹ አስተዳደራዊ፣ የጀርባ ጫናዎች፣ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ያልዳበረ የፖለቲካ ባህል መንሰራፋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መንግስት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን መብት እንዳረጋገጠና ለዚህም ተግባራዊት ሕግ በማውጣት፣ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን በማደራጀት እየሰራ እንደሆነ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየገለፀ ነው፡፡ ከእነዚህ መስሪያ ቤቶች አንዱ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ባለፈው አራትና አምስት አመታት ተማሪው ሲበጣበጥ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮች የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? ሦስቱን ብሔሮች በአንድነት መፍትሄ እንዲያፈላልጉና ተቀራርበው እንዲወያዩ መርዳት ወይስ በተናጠል በመጠየቅ ጉዳዩን መደፋፈን? አስተዳደሮቹ ግጭት የፈጠረውን ወይም ጥቃት የደረሰበትን ብሔር አባላት ችግራቸው ምንድን ነው? ብሎ በመጠየቅ ከተሰጡት ጊዜያዊ መፍትሄ በዘለለ ዘላቂ መፍትሄ ሲሰጡ አልታዩም፡፡ ሁለተኛው ዋነኛ ሃሳቡ ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በሌሎች አካሎች የደረሰ ተጽዕኖ ነው፡፡ ፓርቲዎች አምነውበትም ሆነ ለስልጣንና ለቆይታ ተጠቅመውበት የተማሪዎቹ አመለካከት ጽንፈኛ እንዲሆን የጥላቻ ፖለቲካ እንድንሰራፋ መተማመን እንዲጠፋና ጥርጣሬ እንዲጎላ አድርገዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስልጣን ለመያዝ የብሔር ፖለቲካን ዋነኛ መሳሪያ እንዳደረጉት ሁሉ ገዥው ፓርቲም ስልጣኑ ላይ ጥርጣሬና እምነት ማጣት እንዳይከሰትበት ይህንኑ የብሔር ፖለቲካን በግልጽም ባይሆን በእጅ አዙር ይጠቀሙበታል፡፡ በፌደራል አወቃቀር ላይ በተለይም ከታሪክ፣ ኢኮኖሚና ቀልጣፋ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የተነሱትን ጥያቄዎች፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ላይ የተነሱ ጥያቄዎች፣ በመንግስት ስልጣን ላይ ከህዝቡ የተነሳው ጥያቄ በአግባቡ አለመመለሱ. . . በአጠቃላይ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ተማሪው ሲጠይቀ አለመግባባቶች ለግጭት መንስኤ የሆኑበትም አጋጣሚ አለ፡፡ በመጨረሻም የፖለቲካ ባህላችን የተሸፋፈነ በመሆኑና የዳበረ የፖለቲካ ባህል የሌለን ግልጽነት ያልሰፈነበት ስርዓት ነው ያለን፡፡ ትንሽዬ አለመግባባቶችን ወደማያባራ ግጭት እንዲያመራ የምናደርገው ትግስተኛና በምክንያት የሚያምን ልዩነትን እንደ ውበት ካልሆነም እንደ ተፈጥሯዊ ሂደት ያለማየት ችግር ነው፡፡ ከላይ የገለጽናቸው ምሁርን ያነሱዋው ሃሳቦች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለግጭት እንደ መንስኤ የሚያነሷቸው ..ሰበብ.. ወይም ምክንያት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ የአገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ ይወስን የነበረ በአለም አቀፍ፣ አህጉራዊና አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ጥያቄ ያነሳ የነበረ ነው፡፡ ዛሬ የሚነሱ የብሔር አለመግባባቶች በሰከነ ሁኔታ በነፃነት ሀሳብ ያለመለዋወጥ ሂደት ነው፡፡ መንግስት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ኅብረተሰቡ በአጠቃላይ በግልጽ ያሉ ችግሮችን የመወያየትና በሰከነ ሁኔታ ሃሳብ የመለዋወጥ ባህል አላዳበረም፡፡ በደፈናው የብሔር ችግር ከማለት የኦሮሞ፣ የአማራና የትግራይ ብሔር የሚያነሷችው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? አንዱ ለአንዱ ያለው በጎ ያልሆነ አመለካከት ምክንያቱ ምንድን ነው? እንዴት ሊቀረፍ ይችላል? በሚለው ጉዳይ ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ መንግስት ፖሊሲ ስትራቴጂ ሊያወጣ ህዝቡንም የመፍትሄ አካል ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የተነሱት ጉዳዮች ግን የመስማማትም ሆነ ያለመስማማት መንስኤ ናቸው፡፡ በግለሰባዊነት ክብር መጠበቅም ግጭቱ ቢነሳም ለትልልቆቹ ጥያቄዎች ግልጽ የሆነ መግባቢያ መልስ ባለመኖሩ ነገሮች በእውነትና በማስረጃ ሳይሆን በፈጠራ ወሬም ግጭቶቹ በቀላሉ እንደ ሰደድ እሳት እየተነሱ በመሆናቸው የሁሉንም ርብርብ ይሻሉ እንላለን፡፡ በሰለሞን ጎሹ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |