| ፍ/ቤት የወሰነላቸው የጉምሩክ... |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
ፍ/ቤት የወሰነላቸው የጉምሩክ ፖሊሶች ወደሥራቸው አልተመለሱም
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ከሰኔ 15 ቀን 1999 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ ያሰናበታቸውን 88 የፖሊስ አባላት ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቢወስንም እስካሁን ወደ ምድብ ሥራቸው አለመመለሳቸውን ፖሊሶቹ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ ፍርድ ቤቱ የፖሊስ አባላቱ ወደነበሩበት የሥራ መደብ እንዲመለሱ የወሰነው በጉምሩክ ፖሊስ መተዳደሪያ የገቢዎች ሚኒስቴር መመሪያ ቁጥር 4/96 መሠረት የጉምሩክ ፖሊስ አገልግሎት የሚቋረጥባቸው ምክንያቶች ከመረመረ በኋላ ነው፡፡ በታምሩ ጽጌ በዚህ መሠረት ፍ/ቤቱ በገዛ ፈቃድ ከሥራ መልቀቅ፣ በሕመም ምክንያት ለሥራ ብቁ ሆኖ አለመገኘት (የችሎታ ማነስ..፣ በዲሲፕሊን ቅጣት ከሥራ መሰናበትና በዕድሜ ምክንያት አገልግሎት መቋረጥ ሲሆኑ፣ ጉምሩክ የፖሊስ አባላቱን ያሰናበተበት ምክንያት አንዱንም እንደማያሟላ፣ በአዋጅ ቁጥር 368/1995 አንቀጽ 6/2ሐ/ መሰረት የፖሊስ አባላቱን ለማሰናበት ሥልጣን የለውም፡፡ የፖሊስ አባላቱ እንዳመለከቱት፣ “እኛን አሰናብቶ ሌሎች አንድ ሺ አባላትን ለማሰልጠን መጠየቁ መስሪያ ቤቱ በኛ ላይ የፃፈው ደብዳቤ ሕጋዊ ስልጣን ሳይኖረው ያስተላለፈው በመሆኑ ሕገወጥ መሆኑን ፍ/ቤቱ ተመልክቶ እንዲመለሱ እንዲወስንላቸው በጠየቁት መሰረት ውሣኔ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጉምሩክ ባለሥልጣን የፖሊስ አባላቱን ክስ በመቃወም የመከላከያ መልስ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን ውድቅ መደረጉንና አብሮ ተከሶ የነበረው የገቢዎች ሚኒስቴርም ከክሱ መሰናበቱን የፖሊስ አባላቱ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ወገን (የፖሊስ አባላቱንና ጉምሩክን) ያደረጉትን ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ፍርድ የጉምሩክ ባለሥልጣን የፖሊስ አባላቱን ለማሰናበት የፃፈው ደብዳቤ ከሕግ ውጪ በመሆኑ አግባብነት እንደሌለው ገልፆ የፖሊስ አባላቱ በፊት በነበሩበት የሥራ መደብና ደመወዝ ላይ እንዲመልሳቸው፣ ያወጡትንም ወጪ እንዲተካ ሲል ቢወስንም እስካሁን ተፈፃሚ ባለመሆኑ በችግር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን የፍርድ ውሳኔና ትዕዛዝ ተግባራዊ ባለማድረጉ የፍርድ አፈፃፀም በማውጣት በውሳኔው መሰረት ፈጽሞ እንዲቀርብ ወይም በውሳኔው መሰረት የማይፈጽምበትን ምክንያት ሚያዚያ 13 ቀን 2000 ዓ.ም ቀርቦ እንዲያስረዳ ማዘዙን የፖሊስ አባላቱ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ለምን ተፈፃሚ እንዳላደረገ ማብራሪያ እንዲሰጡን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተርን ለማነጋገር ቢሯቸው ድረስ ብንሄድም “ማመልከቻ ጽፋችሁ በመዝገብ ቤት በኩል ካላስገባችሁ እሳቸውን ማነጋገር አይቻልም” የሚል ምላሽ በፀሐፊያቸው በኩል ተሰጥቶን ተመልሰናል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |