| 100 የቱርክ ባለሀብቶች... |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
100 የቱርክ ባለሀብቶች በቡራዩ ሊያለሙ ተስማሙ
ከአንድ መቶ በላይ የቱርክ ባለሀብቶች በቡራዩ ከተማ በኢንቨስትመንት ሥራ ለመሠማራት መስማማታቸውን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳባ ደበሌ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ አቶ ዳባ እንዳስታወቁት የቱርክ ባለሀብቶች በቡራዩ ከተማ ለኢንቨስትመንት በተከለለ ቦታ ለማልማት የተስማሙት በቱርክ ቢዮቼክሜሽ ከተማ ጋር የእህትማማችነት ስምምነት ከተደረገ በኋላ በተዘጋጀ ሥነስርዓት ነው፡፡ በቡራዩ ኢንቨስት ለማድረግ የተስማሙት የቱርክ ባለሀብቶች ከወር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡ ባለሀብቱ የቆዳ፣ የጨርቃጨርቅ፣ የፕላስቲክና የምግብ ማሸጊያ ፋብሪካዎችን እንደሚገነቡ የገለፁት ከንቲባው በአሁኑ ወቅት 30 ሚሊዮን ብር ካፒታል አንድ የፒቪሲ ፋብሪካ ለመክፈት እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡ የሁለትዮሽ ስምምነቱን አስመልክቶ አቶ ዳባ ሲያስረዱ በከተማዋ የኢንቨስትመንት ዞን አከላለሉ ለአገራችን ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ከአራት የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞችና ከሁለት ባለሀብቶች ጋር ጉብኝት እንዳደረጉ አቶ ዳባ የከተማዋ የኢንዱስትሪ ዞን እኛ አገር እንደሚታየው የተደበላለቀ አይደለም፡፡ ሁሉም የኢንዱስትሪ ዓይነቶች ተለይተው ለየብቻ በየዞኑ እንደሚቀመጡ የገለፁት ከንቲባው በታጠቅ የኢንቨስትመንት ዞን ተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባት ወስነናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ፖሊሲና የኢንቨስተሮች እንክብካቤ በመቀበል ባለሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት መስማማታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን የከተማዋ ከንቲባ በቅርቡ እንደሚመጡ አቶ ዳባ አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በቡራዩ የኢንቨስትመንት ሠርተፊኬት ጥያቄ ከሁለት ሰዓታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንደሚስተናገድ አቶ ዳባ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ዳባ ገለፃ አሰራሩ ከተሻሻለ በኋላ በማዘጋጃ ቤቱ ከምልጃ፣ ከጉቦ፣ ከመቀራረብና ከደላሎች የፀዳ ሆኗል፡፡ በአዲሱ አሠራር መሀንዲሶችና ተገልጋዮች እንዲገናኙ ስለማይደረግ ቀደም ሲል የነበረውን የገንዘብ ትስስር ማስቀረት ተችሏል፡፡ የመሬት አሰጣጥ ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ ከማዘጋጃ ቤቱ እጅ እንዲወጣ መደረጉን የገለፁት አቶ ዳባ “መሬት ነዋሪዎች ራሳቸው በቀበሌያቸው አማካይነት በአደባባይ በቅደም ተከተላቸው በእጣ የሚከፋፈሉበት አሰራር ተመስርቷል፡፡ የማዘጋጃ ቤቱ ተግባር መሬት ማዘጋጀትና ካርታ መስጠት ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በቡራዩ መሬት ሳይዘጋጅ መሬት ፈላጊዎች ገንዘብ እንደሚከፍሉ፣ መሬታቸውን ሳያውቁ ዓመታት ይቆዩ እንደነበር የገለፁት አቶ ዳባ በአሁኑ ወቅት እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ሙሉ በሙሉ መቋረጡን አስታውቀዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |