| በሚኒስትሮች ም/ቤት ውሣኔ |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
![]() አርከበ እቁባይ የግንባታ ዕቃዎችና ማሽነሪዎች እጥረትን ለመፍታት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለቻይና ሁለት ኩባንያዎች በቅርቡ የአስመጪነት ፈቃድ መስጠቱን የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ አርከበ እቁባይ ገለፁ፡፡ አቶ አርከብ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ሲ.አር.ቢሲ እና ሲ.ጂ.ሲ የተባሉት ሁለት ኩባንያዎች ፈቃዱን ሊያገኙ የቻሉት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ በተሰጣቸው የአስመጪነት ፈቃድ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ያስገባሉ፡፡ በዚሁ መሰረት የወሎ ሰፈር ጎተራንና የቀለበት መንገድ የገነባው ሲ.አር.ቢ.ሲ የተባለው ድርጅት 100 ሎደሮችን ለማስገባት ከስምምነት ተደርሷል፡፡ አቶ አርከበ እንዳሉት የቻይናው ኩባንያ አንድ ሎደር በ40ሺ ዶላር ለማስገባት ሲስማማ የካተርፒላር አስመጪ ለአንድ ሎደር 200ሺ ዶላር ጠይቋል፡፡ ይህም አምስት እጥፍ ነው ብለዋል፡፡ “ሲ.አር.ቢ.ሲ ሎደሮቹን ሲያስገባ ክፍያው የሚከናወነው በኢትዮጵያ ብር በመሆኑ ተጠቃሚ ያደርገናል” ብለዋል አቶ አርከበ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በኢትዮጵያ ብር ክፍያ ሲጂሲ የሚባለው ኩባንያ 2ሺ ሲኖትራኮችን ያስገባል፡፡ 100 ዘመናዊ የድንጋይ መፍጫ ክራሸሮችም እንዲገቡ መንግሥት ወስኗል፡፡ ሁለቱም ኩባንያዎች ማሽነሪዎቹን ከማስመጣት በተጨማሪ የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጡም ታውቋል፡፡ የግንባታ እቃዎች አቅርቦት ዋጋ መናርና የአቅርቦት ችግር በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ችግር መፍጠሩን ሚኒስትር ደኤታው አመልክተዋል፡፡ መስታወትን እንደ ምሳሌ የሰጡት ሚኒስትሩ መስተዋት ከውጪ ለማስመጣት በዓመት መንግሥት 100ሺ የአሜሪካን ዶላር ወጪ ያደርጋል፡፡ ሲጂሲ የገነባው የመስታወት ፋብሪካ በሰኔ ሲጀምር የአገሪቱን የውጪ ምንዛሪ ይቀንሳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የግንባታ እቃዎችን እጥረት በተመለከተ ከፋፍለው ያስረዱት አቶ አርከበ በፌደራል ደረጃ በቤቶች ልማት ፕሮጀክት 145ሺ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን በማስታወስ ለግንባታዎቹ 1.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንደሚያስፈልግ፣ አስታውቀዋል፡፡ ለአዲስ አበባ ብቻ 750ሺህ ቶን ሲሚንቶ እንደሚያስፈልግ የሙገር ሲሚንቶ የማምረት አቅም በዓመት 830ሺህ ቶን ብቻ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አርከበ ችግሩን ለመፍታት ለውጪ አገር ሥራ ተቋራጮች ሲሚንቶ ከውጪ የሚገባበት ሁኔታ መንግሥት ማመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡ ሦስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ አሸዋና የተመረጠ የግንባታ አፈር እንደሚያስፈልግ የብረት እጥረት ከፍተኛ መሆኑን፣ ሦስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ጠጠር ለፕሮጀክቶቹ የሥራ ማከናወኛ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ አርከበ “በእንዲህ ያለ የግንባታ እቃ እጥረት ውስጥ የሚካሄድ ፕሮጀክት መሆኑ እየታወቀ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ሥራ አጓተቱ በሚል ሊወቀሱ አይገባም” በማለት “በፕሮጀክቶች መጓተት ይታያል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለቤቶች ልማት ፕሮጀክት ሥራ ጋር በተያያዘ ከ1ሺ በላይ ኮንትራክተሮችና 3ሺህ 500 ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መኖራቸውን፣ ጨረታ አውጥቶ ከመጋበዝ ይልቅ በውስን ዋጋ (ቁርጥ ዋጋ) ማስተናገዱ እንደሚመረጥ የገለፁት አቶ አርከበ ይህ አሰራር ለሙስና ሙሉ በሙሉ የተዘጋ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ ለፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ እቃ እንደሚቀርብላቸው ያመለከቱት ሚኒስትር ደኤታው በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ሙስና ይታያል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ..ሥራ ሲበዛ የሙስና ችግር ይኖራል፡፡ ሙሰናን ሙሉ በሙሉ መከላከል አይቻልም፡፡ ሙስናን መከላከል የሚቻልበት ትልቁና ዋነኛ ዘዴ ሥራን ሙሉ በሙሉ ማቆም ነው፡፡ ለፕሮጀክት የቀረበ ሲሚንቶ የሚሸጡ አሉ ብለን ፕሮጀክት እንዝጋ? በማለት የጠየቁት አቶ አርከበ ሙስናን መከላከል እንጂ ማጥፋት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |