| የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን... |
|
|
| Sunday, 13 April 2008 | |
|
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የነዳጅ አጠቃቀም ለስርቆት የተጋለጠ ነው
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የነዳጅ አጠቃቀም ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን የፌዴራል የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በየካቲት 2ዐዐዐ ዓ.ም. ያወጣው ጥናት አመለከተ፡፡ ነዳጅ ከባእድ ነገር ጋር እየተቀላቀለ ይቀርባል፡፡ በኮሚሽኑ ጥናት መሠረት በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም በተመለከተ የሚታመን ሪፖርት አይቀርብም፡፡ በየዲስትሪክቶች ሥራ ላይ የዋለው የነዳጅ ወጪ በተግባር ከተሰራው ሥራ እየተነፃፀረ ኢኮኖሚያዊ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ የማረጋገጥ ሥራ አይከናወንም፡፡ በዚህም በነዳጅ አጠቃቀም ላይ ያለው የቁጥጥር ስርዓት ጥብቅ አለመሆኑ ለሙስና የተመቻቸ መሆኑን የኮሚሽኑ ጥናት ያመለክታል፡፡ የነዳጅ አቅራቢዎች ለባለሥልጣኑ የሚያቀርቡት ነዳጅ ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም ጥናቱ አመልክቷል፡፡ የባለሥልጣኑ የመኪና አሽከርካሪዎች የተወሰነ የነዳጅ መጠን ከቦቴ ላይ በማጉደል በጎደለው መጠን ባዕድ ነገር በመጨመር ወይም ከመነሻው በነዳጅ ቦቴ ውስጥ ባዕድ ነገር በመቀላቀል ማጭበርበር እንደሚፈፅሙ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም በነዳጅ ጥራት ላይ ችግር መፈጠሩንና በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡ በዲስትሪክቶች፣ ሴክሽኖች እንዲሁም በባለሥልጣኑ የተለያዩ የሥራ ኘሮጀክቶች ከነዳጅ አቅራቢዎች ርክክብ የሚፈፀመው በአንድ ሠራተኛ ብቻ በመሆኑ የነዳጅ ርክክቡ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የነዳጅ ስርጭቱ የሚከናወነው ባልታሸገና መቆጣጠሪያ በሌለው የነዳጅ ቦቴ በመሆኑና ነዳጅ የሚራገፍበትም የነዳጅ ታንከር የነዳጅ መጠኑን የሚያሳይ መቆጣጠሪያ የሌለው በመሆኑ ነዳጅ በየመንገዱ ለግል ጥቅም እንዲሸጥ ክፍተት መፍጠሩን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ጥናቱ የባለሥልጣኑ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከሮች በባለሙያ ተጠንተው የተዘጋጁ ባለመሆኑ የነዳጅ ገቢ ወጪ የቁጥጥር ስርዓቱ ለመስና የተጋለጠ መሆኑን አብራርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለማሽነሪዎችና ለሌሎች ተሽከርካሪዎች ነዳጅ በግራም ባልዲዎች የሚታደልበት ሁኔታ መኖሩንና የእደላ ሥራው የሚከናወነው በጎዳና ላይ በመሆኑ ከእደላው የሚተርፈው ነዳጅ ለግለሰቦች ጥቅም ለሽያጭ እንደሚውል ተጠቅሷል፡፡ በባለሥልጣኑ በአንዳንድ ዲስትሪክቶች በየጊዜው ገቢና ወጪ የሚሆነው ነዳጅ እንዲሁም ከወጪ ቀሪ ሚዛን ክትትል እየተደረገ የማይመዘገብበት ሁኔታ መኖሩንም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ ያለኃላፊው ፈቃድ ነዳጅ ወጪ ተደርጐ የሚታደልበት አሰራር መኖሩም ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ የባለሥልጣኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገውን የእቃ ልውውጥ ሂደት ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ በዚህም በባለሥልጣኑ ዲስትሪክቶች ከባለስልጣኑ እውቅና ውጪ ከአንድ ተሽከርካሪ ወደ ሌላ ተሽከርካሪ የመለዋወጫ እቃ የማቀያየር ተግባር የሚፈፀምበትና የተሽከርካሪ አካል የማጉደል ሁኔታ መኖሩን አስታውቋል፡፡ በዚህም በባለሥልጣኑ የተሽከርካሪ የእቃ ልውውጥን በተመለከተ ጥቅል መስፈርት እንዲሁም የሥራ ሂደትንና አፈፃፀም ማመልከቻ ቅፅና ዝርዝር መመሪያ አለመኖሩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በስራ ላይ ያልዋሉ የተሟላ ሰነድ የሌላቸው በርካታ ማሽነሪዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች በመኖራቸው በሽያጭ የማስወገድ ሂደት ላይ ተፅእኖ እንዳለው ጥናቱ አትቷል፡፡ ጥናቱ በባለሥልጣኑ ያለውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ክፍተት የሚታይበትን ሂደት አስመልክቶ ችግሩን ለመፍታት የመፍትሄ አማራጮችንና አሰራሮችን አብራርቷል፡፡ በተያያዘ ዜና ኮሚሽኑ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የአሰራር ስርዓት ዙሪያ መስከረም 2ዐዐዐ ዓ.ም. ባወጣው ጥናት፤ ባለሥልጣኑ የሚያደርገው የካሳ ክፍያ ግምትና አፈፃፀም በዘልማድ የሚከናወንና ለግለሰቦች አመለካከት የተጋለጠ መሆኑን መጠቆሙ ይታወሳል፡፡ በዚህም የካሣ ግምትና አፈፃፀም ስርዓቱ ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በዚህ መሠረት ባለሥልጣኑ በመንገድ ግንባታ ክልልና ከግንባታው ጋር ለተያያዘ አገልግሎት በሚፈለግበት ቦታ ክልል ውስጥ ለሚገቡና ለገቡ የገጠርና የከተማ ይዞታዎች፤ የመንግሥትና የግለሰብ ንብረቶች የሚሰጠው የካሳ ክፍያ ወጥነት የጎደለው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከዚህ አንፃር ባለሥልጣኑ በተለያዩ ክልሎች በሚከፋፍላቸው ነባርና አዳዲስ የመንገድ ግንባታና ኘሮጀክቶች ከክልልና ከግንባታ ጋር ተያያዥነት ላላቸው አገልግሎቶች በሚፈለጉበት ቦታዎች ውስጥ የገቡ የግለሰቦችና የመንግሥት ንብረቶች የካሳ ክፍያ አፈፃፀም ስርዓት ላይ በርካታ ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጡ ሂደቶች መታየታቸውን ማስገንዘቡ ታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ በጥናቱ አማራጭ የመፍትሔ የአሰራር ሂደት አስቀምጧል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |